Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የደለል ክምችትና የግድቦች ሥጋት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከጅማ ከተማ ጥቂት ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው የቡልቡል አካባቢ ነዋሪዎች ህልውና የተመሠረተው በግብርና ላይ ነው፡፡ በአካባቢው ያለውን ለስላሳና ቀይ አፈር የተመለከተ ግብርና የነዋሪዎቹ ዓይነተኛ መተዳደሪያ መሆኑን ይገምታል፡፡ ነገር ግን ይህ ከግምት ያልዘለለ መሆኑን የአርሶ አደሮቹን ችግር የተመለከተ ማወቅ ይቻላል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ የጐርፍ አደጋዎችና የመሬት መንሸራተት ቦታው ቦረቦረማ ሆኗል፡፡ የረባ አዝርዕትም አልያዘም፡፡

የ45 ዓመቱ አቶ ቢያ አባ ሞጋ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው፡፡ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ናቸው፡፡ ኑሮአቸውን የሚመሩት በግብርና ነው፡፡ በቆሎ፣ ማሽላና ጤፍ የሚያመርቱበት አንድ ተኩል ሔክታር መሬት አላቸው፡፡

መሬቱ በቂ የሚባል ቢሆንም አጥጋቢ ምርት ማግኘት ዘበት ነው፡፡ ሲያውቁት ጀምሮ አካባቢው በጐርፍ ይጠቃል፡፡ የአፈር ለምነቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ ቀንሷል፡፡ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የቀረው ለም አፈር ታጥቦ እንዳይጠፋ ይጥራሉ፡፡ ቢሆንም ግን የተፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት አልተቻለም፡፡

የአፈር መሸርሸሩ እንደ አቶ ቢያ ባሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች ምርት ላይ ከሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ ባሻገር ሌላ የጐንዮሽ ችግር መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ይኸውም ከአካባቢው ተጠርጐ የሚሄደው ለም አፈር በጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የጊቤ አንድ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ላይ የሚፈጥረው የደለል ክምችት የግድቡ ዕድሜ ላይ ጥላ ማጥላቱ ነው፡፡

የአገሪቱን 30 በመቶ የሚሆነውን ኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የሚነገርለት ግልገል ጊቤ አንድ ግድብ የተገነባው በ1996 ዓ.ም. ነበር፡፡ ግድቡም ከ50 እስከ 70 ዓመታት ድረስ እንዲያገለግል ታስቦ የተሠራ ነው፡፡ በአገሪቱ ከሚገኙ ሌሎች ግድቦች በተሻለ ዙሪያ ገባው በዕፅዋት የተሸፈነ በመሆኑ፣ ግድቡን አደጋ ላይ ከሚጥል የደለል ችግር ነፃ እንደሚያደርገው ታምኖ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ከዓመታት በፊት በግድቡ ዙሪያ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ የግድቡ ዙሪያ በዕፅዋት የተሸፈነ ቢመስልም በአካባቢው በርካታ ቦረቦራማ ቦታዎች መኖራቸው በቀላሉ አፈር እንዲሸረሸርና ወደ ግድቡ እንዳይገባ አላገደውም፡፡ ሁኔታው አፋጣኝ መፍትሔ ካልተገኘለትና በዚሁ ከቀጠለ የሚፈጠረው የደለል ክምችት የግድቡን ዕድሜ በግማሽ እንደሚቀንስ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

ይህንንም መነሻ በማድረግ ጥናቱ ምን ያህል እውነት መሆኑን እንዲሁም የተባለው ችግር በእርግጥም ኖሮ ከሆነ መፍትሔ አመላካች የሆነ አጸፋ ጥናት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርናና እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ መምህር አቶ አያሌው ታለማ ጥናት ተደርጓል፡፡ ጥናቱን ከጀመሩ አራት ዓመት እንደሞላቸው የሚናገሩት አቶ አያሌው፣ በጥናታቸው አካባቢው በመሬት መንሸራተት የተፈጠሩ ሸለቆዋማና ቦረቦራማ ቦታዎች መኖራቸውን፣ ቦታዎቹ ገላጣና ዕፅዋት ማብቀል አለመቻላቸውን፣ ይህም አፈር በቀላሉ ተሸርሽሮ ወደ ግድቡ እንዲገባና ግድቡ በደለል እንዲሞላ ማድረጉን በእርግጥም ችግሩ መኖሩን በጥናታቸው አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም የመሬት መንሸራተት ችግሮችን እንዲሁም በአካባቢው ጐልቶ የሚታየውን የመሬት መሸርሸር ማቆም የሚችሉ ልዩ ልዩ ሥራዎችን መሥራት ግድ ነበር፡፡ ‹‹ማንኛውም ዕፅዋት መሬት በመንከባከብ ለአፈር መሸርሸር ዘለቄታዊ መፍትሔ ይሰጣል፤›› የሚሉት አቶ አያሌው፣ የተፈለገውን ውጤት ማስገኘት እንደሚችሉ የታመነባቸው 18 ዓይነት ዕፅዋት ቢተክሉም፣ የአካባቢው የአፈር ለምነት ታጥቦ በማለቁ ዕፅዋቶቹ ሥር መያዝ እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሙከራውን ያደረኩት ቀርሳ ወረዳ ውስጥ ቡልቡል ቀበሌ ላይ ነው፡፡ በጥናቱ እንዳረጋገጥኩት ቦታው ለ70 ዓመታት ያህል ዕፅዋት ማብቀል የማይችል የተራቆተ ነው፡፡ በዙሪያው ሌሎች መሰል ለእርሻ፣ ለከብት ግጦሽም ሆነ ለሌላ ነገር የማይውሉ፤ ነገር ግን የደለል ምንጭ የሆኑ ቦታዎች ብዙ ናቸው፤›› በማለት የተተከሉት ዕፅዋት መሬቱ በመራቆቱ መብቀል እንዳልቻሉ ያስታውሳሉ፡፡

በተገኘው ውጤት ተስፋ ባለመቁረጥ ለመብቀል ብዙ ንጥረ ነገር የማይፈልጉ እንደ ሳር ያሉ የዕፅዋት ዝርያዎችን ሞክረዋል፡፡ በዚህም አበረታች ለውጦችን ማግኘት መቻሉን፣ አካባቢው ከመሸርሸር ከማዳን ባሻገር የአፈር ለምነቱን እንደሚመልሰው ይናገራሉ፡፡

አቶ አያሌው በቡልቡል አካባቢ የሠሩት ጥናትና ሙከራ በብዙዎቹ የግድቡ አካባቢዎች ላይ በበቂ ሁኔታ ተግባራዊ አልሆኑም፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች የተለያዩ ጥረቶች ቢኖሩም እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ አቶ አያሌው እንደሚሉት ጥናታቸው በግልገል ጊቤ አንድ የኃይል ማመንጫ ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ ካለው የዕፅዋት ስርጭት አንፃር በደለል ከሚጠቁ ግድቦች ግልገል ጊቤ የመጨረሻውን ድርሻ ይይዛል፡፡ የሌሎቹን ግድቦች ያህል የደለል ሥጋት የለበትም፡፡

51 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው የግልገል ጊቤ አንድ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ 838 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ይይዛል፡፡ ከዚህ ውስጥ ለኃይል ማመንጫነት የሚውለው 671 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚሆነው ነው፡፡ ከኃይል ማመንጫ ካናል ሥር ያለው 171 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚሆነው ቀሪ ውኃ ደግሞ ለደለል ማከማቻነት የተተወ ነው፡፡ ግድቡ 184 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዳለው የሚናገሩት የግልገል ጊቤ አንድ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሀብታሙ ሰሙ ናቸው፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ ደለል ሥጋት መሆኑን የሚጠቁም ጥናት ይፋ ከሆነ  በኋላ የግድቡን ደኅንነት የሚጠብቁ የተለያዩ ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ‹‹ደለል ተፈጥሯዊ ነው፡፡ በየትኛውም ግድብ ውስጥ ይገባል፡፡ ችግር የሚሆነው ግን በብዛት ሲገባ ብቻ ነው፤›› የሚሉት ኢንጂነሩ፣ በቅድሚያ በግድቡ ስለሚገኝ የደለል መጠን መጠናቱን፣ ግኝቱም በጥናቱ በተገለጸው መጠን ባይሆንም ሥጋት እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም ጣቢያው በግድቡ ዙሪያ የሚገኙ ስድስት ወረዳዎችን በተለይም ደግሞ ሰኮሩ፣ አሞናዳና ጢሮአፈታ ከተባሉ ወረዳዎች ጋር የተለያዩ ደለል መከላከል ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን በጋራ ሲሠሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የደለል ጉዳይ እኛ ጋር በደንብ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው፡፡ በዚህም ጥሩ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል፤›› ቢሉም፣ ሪፖርተርን ጨምሮ ሌሎች የሚዲያ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በአካባቢው ባደረጉት ጉብኝት የተባለውን ያህል አለመሠራቱን አሁንም ብዙ እንደሚቀር ማወቅ ተችሏል፡፡ ይህንን ተከትሎም የተባለውን ለውጥ በመስክ ጉብኝት አለመታየቱን፤ ይህ ከምን የመነጨ ስለመሆኑ ለሥራ አስኪያጁ በቀረበው ጥያቄ፣ ‹‹ያስጎበኘነው ብዙም ያልተሠራባቸውን አካባቢዎች ነው፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ የተሠሩ ሥራዎች አሉ፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የአየር መዛባት ትልቅ ሥጋት በፈጠረበት በዚህ ወቅት የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ ልዩ ልዩ ሥራዎች እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡ እንደ ንፋስ ኃይል፣ የፀሐይ ሙቀት፣ የከርሰ ምድር ውኃና ወንዞችን በመገደብ ከሚገኝ የውኃ ኃይል ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ማጐልበትና ሙቀት አማቂ ጋዞች ምንጭ የሆኑ ኃይሎችን ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማድረግ የአየር ንብረትን ከመጠበቅ አኳያ ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል ነው፡፡

በዚህ ረገድ ተስፋ የተጣለባት አፍሪካ ነች፡፡ እንደ አንድ አፍሪካዊ አገርም ኢትዮጵያ የበኩሏን እየሠራች ትገኛለች፡፡ የተለያዩ ታዳሽ የኃይል ምንጮች በሥራ ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማጐልበትም የተለያዩ ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የዓለም መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ለመሆን የበቃው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ይጠቀሳል፡፡ ግልገል ጊቤ፣ ቆቃና ተከዜ የመሳሰሉት ግድቦች ደግሞ ቀደም ብለው የተገነቡና አገሪቱ ለሚያስፈልጋት ኃይል ምንጭ ሆነው በማገልገል ላይ ያሉ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ሥራ ላይ ከማዋል አኳያ የቤት ሥራዋን እያቀላጠፈች ትገኛለች፡፡ ጅምሩም ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ነገር ግን በኃይድሮ ኤሌክትሪክ በኩል እያሳየች ያለችውን ለውጥ ሥጋት ላይ የሚጥል ክስተት ታይቷል፡፡ ይኸውም ግድቦቹ ረጅም ጊዜ እንዲያገለግሉ ተደርገው የተሠሩ ቢሆንም፣ ትኩረት የተነፈገው የደለል ችግር ለግድቦቹ ዕድሜ ማጠር ምክንያት መሆኑ ነው፡፡  

የደለል ክምችት በዋዛ የሚታይ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለሐሮማያ ሐይቅ መድረቅ ምክንያት የነበረው ደለል ነው፣ በተመሳሳይ ችግር በእጅጉ በመጠቃት ላይ የሚገኙት የቆቃና የተከዜ ወንዝም አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያሻቸው የሚናገሩት አቶ አያሌው፣ ካለው የመልከዓ ምድር አቀማመጥ እንዲሁም የዕፅዋት ሥርጭት እጥረት አንፃር የህዳሴው ግድብም እንዲሁ ለደለል ክምችት የተጋለጠ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

‹‹ወንዞቻችን እየሸረሸሩ ወደ ውጭ ከሚወስዱት ለም አፈር በተጨማሪ ኃይል ለማመንጨት በገደብናቸው ግድቦች ዙሪያ ደለል በመሙላት የምናገኘውን የኃይል መጠን እየቀነሱብን ይገኛሉ፤›› የሚሉት የፖፑሌሽን ኸልዝ ኢንቫይሮመንት ኢትዮጵያ ኮንሰርቲየም ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ የቻሪትስ ኤንድ ሶሳይቲ ዋና ሰብሳቢ አቶ ነጋሽ ተክሉ ናቸው፡፡

ወንዞች ለግብርናችን ምርታማነት እንዲሁም ለኃይል ምንጫችን ቀጣይነት ወሳኝ ናቸው የሚሉት አቶ ነጋሽ፣ ተገቢውን ትኩረት ያላገኘው የደለል ክምችት ለግብርናም ሆነ ለኃይል እንቅፋት እየሆነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በደለል ክምችት የደረቀውን የሐሮማያን ሐይቅን ጠቅሰው አብያታ ሐይቅም 50 በመቶ የሚሆነው የውኃ ክፍል በዚሁ በደለል ክምችት መሸሹንና ሥጋት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኤልኒኖ ምክንያት ኃይል ማመንጨት የተሳነው የተከዜ ወንዝም ኤልኒኖ ካሳደረበት የኃይል እጥረት ጐን ለጐን በግድቡ የተከማቸው ደለል የራሱን ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተከዜ ተፋሰሶች ከትግራይና ከአማራ አካባቢ የሚመጡ ገባር ወንዞች ናቸው፡፡ ወንዞቹ የሚመጡበት ቦታ ተሸርሽሮ መሬቱ ገጧል፡፡ ድንጋያማም ሆኗል፡፡ እየጠረገ የሚመጣው አሸዋም ግድቡን የደለል ክምችት አድርጎታል፤›› በማለት ችግሩ በተከዜ ዙሪያ ጐልቶ እንደሚታይ ያብራራሉ፡፡

ያሉትን ተፋሰሶች ህልውና ከመጠበቅ አኳያ የባለድርሻ አካላት ተጣምሮ የመሥራቱ ሁኔታ ክፍተት ይታይበታል የሚሉት አቶ ጌትነት ወርቁ፣ በአካባቢው ደንና የአየር ንብረት ሚኒስቴር በአካባቢ ሁኔታና ለውጥ ዝግጅት ዳይሬክቶሬት የአካባቢ ማኔጅመንትና አናሊስስ ሲኒየር ኤክስፐርት ናቸው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ተራራማ መልከዓ ምድር ያላት አገሪቱ 12 ወንዞች አሏት፡፡ ወንዞቹ በፍጥነት የሚሄዱ እንዲሁም ከተራራማ ቦታዎች በከፍተኛ ኃይል የሚወረወሩ ናቸው፡፡ ይህም የታችኛው የመሬት ክፍል እንዲቦረቦርና አፈር እንዲታጠብ የሚያደርግ ነው፡፡ በፍጥነት የሚጓዙት ወንዞችም ተሸክመው የሚወስዱት አፈር ግድቦችን የሚሞላና ያለ ዕድሜአቸው እንዲጠፉ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህም ልማትን ከማደናቀፍ ባሻገር መጪው ትውልድ የሚገባውን ጥቅም እንዳያገኝ ያግዳል፡፡ ጥቅም ላይ የሚውሉ ልዩ ልዩ የተፈጥሮ ሀብቶች የመጪው ትውልድ ሀብቶች ናቸው፡፡ ዛሬ እየተገደቡ የኃይል ምንጭ የሚሆኑ ወንዞችም እንደዚሁ፡፡ በመሆኑም ግድቦቹ ኢንጂነሪንግ ጥራታቸውን ጠብቀው ለረጅም ዓመት እንዲያገለግሉ ተደርገው መሠራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡   

ይሁንና ተገቢው ጥንቃቄ ሳይደረግላቸው የተሠሩ የቆቃ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ግድቦች በደለል ክምችት እየተጠቁ ይገኛሉ፡፡ ተከዜ፣ የባሌ መልከዋቀና ግድብ በደለል ከተጠቁት መካከል ናቸው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍም በተፋሰሶች አካባቢ የሚገኙ ቦታዎችን በዕፅዋት መሸፈን ግድ ይላል፡፡ ይህም ለም አፈር እንዳይታጠብ ከመርዳት ባሻገር የደለል ክምችትን በመከላከል የግድቦችን ዕድሜ ለማስረዘም ይረዳል፡፡ አብዛኛው ሥራ የሚሠራውም በአርሶ አደሩ ቢሆንም፣ ባለው ተቀናጅቶ የመሥራት ችግር ዋጋ እያስከፈለ እንደሚገኝ ያብራራሉ፡፡

የትኛውም ግድብ ሲገነባ የደለል ክምችትን ከመከላከል አኳያ የሚቀመጡ አሠራሮች ቢኖሩም፣ ተግባራዊ ሳይሆኑ ቆይተዋል የሚሉት በውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የተፋሰስ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስማማው ቁሜ ናቸው፡፡   

አቶ አስማማው እንደሚሉት፣ የኃይድሮ ፓወርና ትላልቅ የመስኖ ግድቦች ጥናት ሲደረግ የወተር ሼድ እንዲሁም የካችመንት ኤሪያ ሁኔታ በጥናቱ ይካተታል፡፡ ይሁን እንጂ ከወረቀት ባለፈ በተግባር ሲውል አይታይም፡፡ በዓለም አቀፍ አሠራር መሠረት ግን አንድ ግድብ ከመገንባቱ አስቀድሞ የሚሠራው የካችመንት ኤሪያና የወተር ሼድ ሥራ ላይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ በአገሪቱ ተግባራዊ አልነበረም፡፡

‹‹ግድቦቻችን ተጋላጭ ቦታ ላይ ይገኛሉ፤›› የሚሉት አቶ አስማማው፣ የገበሬው ማሳ ከተራቆተ፣ ግድቦች በደለል ከተሞሉ በኋላ የሚደረጉ ጥረቶች አላስፈላጊ ድካም መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ አስቀድመው ደለልን ታሳቢ አድርገው በሚሠሩ ግድቦች የግድቡን ዕድሜ የአፈር መሸርሸርን ከመታደግ ባሻገር የከርሰ ምድር ውኃን ለማጐልበትና ለሌሎችም ይረዳል ይላሉ፡፡ ችግሮቹን ለመፍታትም ጥብቅ የሆኑ ክልሎች ሊኖሩ እንደሚገቡ፣ በሚከለሉ ጥብቅ ቦታዎች አርሶ አደሩ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች የሚያገኝበት አሠራር ሊኖር እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ባሻገርም ደለሉን መቆጣጠር የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚገቡ አሳስበዋል፡፡

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ወደ ግድቦች የሚገቡ ደለሎችን የመከላከል ሥራዎች ተግባራዊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ወደ ግድቦች የሚገቡ ደለሎችን ለማስቀረት የተለያዩ ሥራዎች በወንዞች ዳርቻ ላይ እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ በግልገል ጊቤ አንድ ላይ የሐይቁ ጥግ ላይ ከቦረቦራማ ቦታዎች የሚነሱ ግንዳግንዶችና መሰል የደለል ምንጮች ወደ ሐይቁ እንዳይገቡ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ ሐይቆች ላይም ተመሳሳይ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በጣና ሐይቅ ዙሪያም እንደዚሁ፡፡ በዘንድሮ ዓመት በመልከዋቀና ግድብ ላይ የተጀመረው ሥራም በጊዳቦ አባያም በተመሳሳይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የተፋሰስ ባለሥልጣናት በሌሉባቸው አካባቢዎች የወተር ሼድ ሥራዎች የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይሠራል፡፡

አገሪቱ ካላት የወንዞች ቁጥርና እምቅ የከርሰ ምድር ኃይል አንፃር 45,000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ቢኖራትም፣ አገሪቱ ከተለያዩ የኃይል ምንጮች ማግኘት የተቻለው 2,300 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ ዓመት ላይ ቁጥሩን ወደ 17,000 ሜጋ ዋት የማሳደግ ዕቅድ ተይዟል፡፡ ይህንን ለማሳካትም ግድቦች የሚከማች የደለል መጠን ላይ ሊታሰብበትና እንደ አቶ ቢያ ያሉ አርሶ አደሮችን በልማት በማካተት ለውጥ ማስመዝገብን ያካተተ መሆን ይገባዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች