– ከነዳጅ ሽያጭ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለማሳደግ ታስቧል
ለመንገድ ጥገናዎች የሚውል ፈንድ የማሰባሰብና የማሠራጨት ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ መንገድ ጽሕፈት ቤት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣውን የመንገድ ጥገና በጀት ጥያቄን ለመመለስ ያስችላል ያላቸውን አዳዲስ የገቢ ማግኛ አሠራሮችን ለመንግሥት ማቅረቡ ተጠቆመ፡፡ ከነዳጅ ሽያጭ ላይ የሚሰበሰበውን የመንገድ ጥገና የፈንድ መጠን ለማሳደግም ታቅዷል፡፡
ከኢትዮጵያ መንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በጽሕፈት ቤቱ ተጠንቶ ለመንግሥት ቀርቦ ውሳኔ እየጠበቀ ካለው ሌላ በ2008 በጀት ዓመት ከእያንዳንዱ ተሽከርካሪ ለመንገድ ጥገና የሚውል ዓመታዊ መዋጮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ረሺድ መሐመድ እንደገለጹት፣ ለመንገድ ጥገና የሚውለውን ፈንድ ለማሳደግ ለመንግሥት ከቀረቡ ጥያቄዎች አንዱ ለመንገድ ጥገና ተብሎ ከነዳጅ ሽያጭ የሚሰበሰበውን መጠን ማሳደግ የሚለው ነው፡፡
ጽሕፈት ቤቱ እስካሁን በየዓመቱ በመንገድ ጥገና ከነዳጅ ሽያጭ ላይ የሚሰበሰበው ፈንድ ከአንድ ሊትር ሽያጭ ከ10 ሳንቲም ያነሰ ገቢ የሚያገኝበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህም በዓመት ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ ለፌደራል፣ ለክልልና ለከተሞች የመንገድ ጥገና የሚሆን በጀት ሲያከፋፍል ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ለመንገድ ጥገና የሚፈለገው በጀት በእጅጉ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ከነዳጅ ሽያጭ ብቻ የሚሰበሰበው ፈንድ በቂ ሊሆን ባለመቻሉ ተጨማሪ የገቢ ምንጮች የሚያስገኙ አሠራሮች ተግባራዊ መሆኑ ግድ ሆኗል፡፡ ጽሕፈት ቤቱም ለመንግሥት ያቀረበው ጥያቄ መነሻም ይኸው መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አርዓያ ግርማይ እንደሚገልጹት፣ በአሁኑ ወቅት ካለው ከፍተኛ የመንገድ ጥገና ፍላጐት አንፃር የመንገድ ፈንድ እየሰበሰበ ያለው ፈንድ በቂ ባለመሆኑ፣ ፈንዱ የገቢ ምንጮች ሊያድጉ ይገባል፡፡ ከመንገድ ጥገና ፍላጐት አንፃር ከመንገድ ፈንድ እየተመደበ ያለው በጀት አነስተኛ መሆኑን አቶ አርዓያ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት የሚገኘው በጀት፣ በዓመት ከሚያስፈልገው የጥገና ወጪ የሚሸፍነው ከአንድ ሦስተኛ በታች የሚሆነውን ብቻ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌም፣ ከመንገድ ፈንድ የሚገኘው ዓመታዊ በጀት አነስተኛ መሆኑ ከመጠቆማቸውም በላይ የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ለአዲስ አበባ መንገዶች ጥገና የሚበጅተውም በጀት በየዓመቱ ለጥገና ከሚፈለገው በጀት 50 በመቶውን እንኳን አይደርስም ይላሉ፡፡ በመንገድ ጥገና የሚፈለገው ገንዘብ ደግሞ እየጨመረ በመምጣቱ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝበት መንገድ መመቻቸት እንደሚኖርበትም ያምናሉ፡፡ እንደ ምሳሌ የቀረበውም በአዲስ አበባ ከተማ በ2008 በጀት ዓመት ለመንገድ ጥገና የሚፈለገው በጀት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ቢሆንም፣ ጽሕፈት ቤቱ የመደበለት ግን 47 ሚሊዮን ብር ነው፡፡
አሁን እየታየ ካለው ከፍተኛ ኔትወርክ አንፃር የጥገና በጀቱ ሊያድግ እንደሚገባ የገለጹት ኢንጂነር ፍቃዱ፣ የፈንድ መገኛ ምንጩም መስፋት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት በ1990 ዓ.ም. ሲቋቋም ታሳቢ ያደረገው በወቅቱ ያለውን የመንገድ ኔትወርክ ነው፡፡ በወቅቱ በአዲስ አበባ ከተማ ጠጠርና የአስፓልት መንገዶችን ጨምሮ 1050 ኪሎ ሜትር ብቻ እንደነበር ያስታወሱት ኢንጂነር ፍቃዱ፣ አሁን ግን የከተማው የመንገድ ሽፋን ከአምስት ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ በመድረሱ በዚሁ ልክ የጥገና በጀቱም ሊያድግ ይገባል ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን እየታየ ያለው ግን ከመንገድ ጥገና ፍላጐቱ ጋር የተጣጣመ አይደለም፡፡ አንድ መንገድ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት በጥሩ ሁኔታ ካገለገለ በኋላ ጥገና ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ዕድሜውን ለማራዘሙም ጥገና እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ከሚያሰባስበው ገንዘብ ውስጥ 65 በመቶውን ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ 25 በመቶውን ለክልሎች፣ 10 በመቶውን ደግሞ ለከተሞች ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ እንደ አቶ አርዓያ ገለጻ ከሆነ፣ ከመንገድ ፈንድ ለፌዴራል መንገዶች ጥገና የሚገኘው በጀት ከፍላጐቱ ከአንድ ሦስተኛ በታች በመሆኑ፣ ጉድለቱን ከካፒታል በጀት ላይ እየሞላ ለፌዴራል መንገድ ጥገና ሥራ ያውላል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ አዲስ ባሰናዳው ዕቅድ መሠረት ከነዳጅ የሚሰበሰበውን የገንዘብ መጠን ከፍ ለማድረግ ሲያስብም፣ ማይክሮ ኢኮኖሚውን በማይጐዳ መንገድ የሚከናወን ይሆናል የሚል እምነት አለው፡፡
በዚህ ዓመትም ጽሕፈት ቤቱ የሚሰበሰበውን የገንዘብ መጠን ለማሳደግ እያንዳንዱ ተሽከርካሪ ላይ የመንገድ ጥገና ክፍያ እንዲከፈል የሚያስችል አሠራር ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ይህ አሠራር በ2008 በጀት ዓመት ተግባራዊ እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ተሽከርካሪ ቦሎ ሲያሳድስ እንደ መኪናው ዓይነት ከ125 እስከ 2500 ብር በየዓመቱ ለመንገድ ጥገና ክፍያ እንዲፈጸም ይደረጋል፡፡
ከዚህ አዲስ አሠራር የሚገኘው ዓመታዊ ገቢ ከ100 እስከ 200 ሚሊዮን ብር ሊሆን ይችላል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ሌሎች ፈንዱን ሊያሳድጉ የሚችሉ አሠራሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ በጥናቱ የተመለከተ ሲሆን፣ ለመንገድ ጥገና የሚፈለገውን ገንዘብ ለማሳደግ የሌሎች አገሮች ምርት ተሞክሮ እየታየ ተግባራዊ እንደሚደረግም የአቶ ረሺድ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡
በአገሪቱ ውስጥ እየተገነባ ካለው መንገድ አንፃር ጥገና ትኩረት የሚሰጠው መሆን እንዳለበት በመታወቁ፣ ከጽሕፈት ቤቱ በየዓመቱ ከሚመደበው ገንዘብ ሌላ መንግሥት ለመንገድ ጥገና ራሱን የቻለ በጀት እየመደበ ነው ተብሏል፡፡ በተለይ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ዘመን የመንገድ ጥገና ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ፣ በቀጥታ ለመንገድ ጥገና ራሱን የቻለ በጀት እየተመደበ ነው፡፡
በ2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አንድ ቢሊዮን ብር በጀት እንደተመደበለት በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣንም ከመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት የሚመደብለት ዓመታዊ በጀት ከመንገድ ጥገናው ፍላጐት ጋር የማይጣጣም በመሆኑ አስተዳደሩ ለጥገና በጀት እየመደበለት ነው፡፡ በ2008 በጀት ዓመትም የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ከመደበው 47 ሚሊዮን ብር ሌላ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዳደሩ መድቦለታል፡፡
እንደ አቶ አርዓያ ገለጻ፣ የመንገድ ጥገና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ በተለይ እንደ ትልቅ ግብ የተያዘው የ‹‹ሮድ አሴት ማኔጅመንትን›› ማጠናከር ነው ያሉት አቶ አርዓያ፣ ይህንንም ለማጠናከር ዘመናዊ አሠራርን በመተግበር ‹‹ሮድ አሴት ማኔጅመንት›› ላይ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት የመንገዶች ኔትወርክ እየሰፋ ቢሆንም የመጠገን ዘዴያችንም አነስተኛ ነው፡፡ በተለይ የሚመደበው በጀት ‹‹በመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት›› ብቻ መሆኑም የራሱ ተፅዕኖ አለው፤›› ይላሉ፡፡ በቅርቡ ደግሞ በመከራ ደረጃ የተጀመረ ሥራ መኖሩን ያስታወሱት አቶ አርዓያ፣ አገር በቀል ኮንትራክተሮችም በመንገድ ጥገና ሥራ ላይ እንዲገቡ የሚያስችል ነው፡፡ እስካሁን የመንገድ ጥገና ሥራዎች የሚሠሩት ቀደም ብሎ በባለሥልጣኑና ከዚያም በኋላ በመንግሥታዊው የመንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ነበር ተብሏል፡፡
የመንገድ ጥገናን ለማጠናከር እየተሠሩ ነው ከተባሉት ውስጥ በፓኬጅ ደረጃ አፈጻጸምን መሠረት ያደረገ የጥገና ስትራቴጂን መከተል አንዱ ነው፡፡ ይሄ በፓኬጅ ደረጃ ይተገበራል የተባለው ዕቅድ፣ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይም እንደሚጀመርም አቶ አርዓያ ገልጸዋል፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችም ወደዚህ እንዲገቡና ከኢትዮጵያ መንገድ ኮርፖሬሽን ጋር በጥምረት እንዲሠሩም ይደረጋል የሚል እምነት አለ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በጥምረት ሥራን ማስተዳደር እንደሚያስችልና ለተወሰነ ዓመት ጥገናውን እየሠሩ ከዚያ በኋላ የጥገናውን ማኔጅመንት ጭምር እንዲይዙ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የመንገድ ጥገና ሥራ በአጠቃላይ ከዘመናዊነት አሠራር ጋር ታሳቢ ተደርጐ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ አርዓያ፣ ዋናው ነገር ግን የፋይናንስ አቅም ነው ብለዋል፡፡ ከመንገድ ፈንድ ውጪ ፋይናንስ የሚገኝበት ሁኔታ ወይም ከመንገድ ፈንድ ውጪ የመሰብሰብ አቅም መጨመር አለበት ይላሉ፡፡ ‹‹ይሄ ካልተደረገ አሁን ባለው የገንዘብ አቅም መንገዶቻችን ተፈላጊው ጥገና ሊያገኙ ይችላሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ስትራቴጂውን እያወጣን ያለነው ከዚህ በፊት የመንገድ ፈንድ መጨመር አለበት ሲባል በጥቂቱ አሁን ካለው የመንገድ ሀብት መጠን ከ2.5 እስከ 3 በመቶው መንገድ ጥገና መመደብ እንዳለበት ያመለክታል፡፡ በዚህ እሳቤ ለመንገድ ጥገና ከአምስት ቢሊዮን ብር ሊያስፈልገን ይችላል ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡
እንደ መፍትሔ ሊወሰዱ ይገባል የተባሉ የተለያዩ አሠራሮች ሊተገበሩ ይገባል የሚል አስተያየት ያላቸው ኢንጂነር ፍቃዱ፣ አንዱ ለጥገና የሚሆን በጀት ለማግኘት የክፍያ መንገዶችን ማስፋፋት ነው ይላሉ፡፡
በሌሎች አገሮች የመንገድ ጥገና ወጪያቸውን ለመሸፈን መንገዶቻቸው በክፍያ አገልግሎት እንዲሰጡ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ በአዲስ አበባም እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ካልተገበረ በቀር እያደገ የመጣውን የመንገድ ጥገና ወጪ ለመሸፈን ከባድ ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል ኢንጅነር ፍቃዱ፡፡ አቶ ረሽድ ደግሞ በጽሕፈት ቤቱ በኩል የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆኑ ቢታመንም፣ ከመንገድ ጥገና ፍላጐት አንፃር ፌዴራል መንገዶች ባለሥልጣንም ሆነ የክልልና ከተሞች ለመንገድ ጥገና የሚሆናቸው በጀት በቀጥታ እየተመደበላቸው ነው ብለዋል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመንም መንገድ ትኩረት የተሰጠው ነገር በመሆኑ ከመንገድ ፈንድ የሚመደበው በጀት ባይበቃቸው ከመንግሥት በቀጥታ የሚመደብላቸው በጀት ይኖራል፤ ይህም እየተደረገ ነው ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ከ5,063 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝማኔ ያላቸውን መንገዶች ከባድ ጥገና ለማከናወን ማቀዱ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ጥገና ሥራም ከመንገድ ፈንድ ብቻ ሰባት ቢሊዮን ብር ይፈልጋል፡፡