[ክቡር ሚኒስትሩ የአለቃቸው ልጅ ልታገባ መሆኑን ሰምተው፣ በራሳቸው ተነሳሽነት ሠርጉን የሚያስፈጽም ኮሚቴ ሊያዋቅሩ ተዘጋጅተዋል፡፡ አማካሪያቸውም በአፋጣኝ ወደ ቢሯቸው እንዲመጣ አደረጉት]
- ምነው በአፋጣኝ ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- አንገብጋቢ ጉዳይ መጥቶ ነው፡፡
- የምን አንገብጋቢ ጉዳይ?
- ትልቅ አዲስ አገራዊ ፕሮጀክት ከፊታችን ተደቅኗል፡፡
- አዲስ አገራዊ ፕሮጀክት?
- አዎን አዲስ አገራዊ ፕሮጀክት፡፡
- ግድብ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የጀመርነውን ሳንጨርስ ሌላ ግድብ አማረህ?
- ታዲያ የባቡር ፕሮጀክት ነው?
- እሱንማ አጠናቀቅን፡፡
- የስኳር ፕሮጀክት ነው?
- የስኳር ፕሮጀክት ነበረን ለካ?
- የማዳበሪያ ፕሮጀክት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- አንተ በዚህ ከቀጠልክ የሞቱ ዘመዶቼን ልታስታውሰኝ ትችላለህ፡፡
- የምን ፕሮጀክት ነው ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
- ትልቅ ልማታዊ ሠርግ ከፊታችን ተደቅኗል፡፡
- ልጅዎት ልታገባ ነው እንዴ?
- እኔ የልጄን ሠርግ እንደ ትልቅ ፕሮጀክት የምቆጥረው ይመስልሃል?
- ታዲያ የማን ሠርግ ነው?
- የአለቃዬ፡፡
- አለቃዎት ሊያገቡ ነው?
- የለም ልጃቸው ልታገባ ነው፡፡
- ግን ክቡር ሚኒስትር …
- የምን ግን ነው?
- ሠርጉ እኮ የቤተሰቡ የግል ጉዳይ ነው፡፡
- ጤነኛ ነህ ግን አንተ?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ከዚህ የበለጠ የአገር ጉዳይ አለ?
- ኧረ የለም፡፡
- ከተማችን ውስጥ ተደግሶ የማያውቅ ድል ያለ ሠርግ ነው የምንደግሰው፡፡
- አለቃዎት ያውቃሉ ግን?
- ሰርፕራይዝ ነው፡፡
- አይ ፈርቼ ነው እኮ፡፡
- ምንድን ነው የፈራኸው?
- ሰርፕራይዙ እርስዎን ራስዎትን ሰርፕራይዝ እንዳያደርግዎት፡፡
- ስለእሱ አታስብ ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ፡፡
- ስለዚህ ምን ይደረግ?
- ኮሚቴ መቋቋም አለበት፡፡
- ምን የሚሉት?
- በራስ ተነሳሽነት ሠርጉን የሚያስፈጽም ኮሚቴ፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እዚህ ላይ ትኩረት እንዲሰጣቸው የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ፡፡
- ምንድን ናቸው ክቡር ሚኒስትር?
- በመጀመሪያ ይህ ፕሮጀክት ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ነው፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሲቀጥል ይህን ፕሮጀክት እንደ ማሳያ መጠቀም ስለምንፈልግ ከፍተኛ ርብርብ እንዲደረግበት እፈልጋለሁ፡፡
- ይቀጥሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ ፕሮጀክቱን ከግብ ለማድረስ ሁላችንም ቀን ተሌት ደከመን ሰለቸን ሳንል መሥራት አለብን፡፡
- ነጥቦቹን ይዣቼዋለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ከዚህ ባለፈ ማድረግ ያለብን ነገሮች አሉ፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- በዋናው ኮሚቴ ሥር ሦስት ንዑስ ኮሚቴዎች መዋቀር አለባቸው፡፡
- ምን ዓይነት ኮሚቴዎች?
- የመጀመሪያው የከብት አፈላላጊ ኮሚቴ ነው፡፡
- ሁለተኛውስ?
- የከብት ግዢ ኮሚቴ ነው፡፡
- የመጨረሻው ምንድን ነው?
- ሦስተኛው የከብት አራጅ ኮሚቴ ነው፡፡
- እነዚህ ኮሚቴዎች ያስፈልጋሉ ግን?
- ስማ ይህ ፕሮጀክት ፍጹም ከሙስና የፀዳ መሆን አለበት፡፡
- ለዚህ ነው ኮሚቴዎቹ የበዙት?
- ነገርኩህ እኮ፣ እያንዳንዱ የሥራ ሒደት ግልጽ በሆነ መንገድ መካሄድ አለበት፡፡
- ስለዚህ ኮሚቴዎቹ እንዴት ይዋቀሩ?
- የምታዋቅርበትን መንገድ አሁን እነግርሃለሁ፡፡
- ይቀጥሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በኮሚቴዎቹ የብሔር ስብጥር የተመጣጠነ መሆን አለበት፡፡
- ጥሩ ነጥብ ነው ያነሱት፡፡
- ሲቀጥል አባላቶቹ መመረጥ ያለባቸው ከፎረሞቹ ነው፡፡
- ከየትኞቹ ፎረሞች?
- ከሴቶች ፎረም፡፡
- እሺ፡፡
- ከወጣቶች ፎረም፡፡
- ሌላስ?
- ከነጋዴዎች ፎረም፡፡
- የደላሎች ፎረምስ ይግቡበት?
- ምን ነክቶሃል?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ደላሎችን ለማጥፋት ቆርጠን በተነሳንበት ወቅት ጭራሽ ኮሚቴ ውስጥ ደላላ ልታስገባልኝ?
- አይ ክቡር ሚኒስትር የከብት ገበያው እኮ በደላላ ነው የሚመራው ብዬ ነው፡፡
- ቢሆንስ ታዲያ?
- እነሱን ካልያዝን ይህን ፕሮጀክት በድል መወጣት አንችልም ብዬ ነው፡፡
- ለነገሩ ልክ ብለሃል፡፡
- አዲሱን አባባል አልሰሙም እንዴ?
- ምን የሚለውን?
- ለማንኛውም ድል፣ ያስፈልጋል ደላላ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ሚኒስትር ጋ ስልክ ደወሉ]
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ይኸው በአዲሱ ፕሮጀክት ተወጥረናል፡፡
- የምን አዲስ ፕሮጀክት መጣ?
- አገራዊ ፋይዳ ያለው ታላቁ ፕሮጀክት ነዋ፡፡
- ስለግድቡ ነው የሚያወሩት?
- ሰው ሁሉ ከግድቡ ሌላ የሚያውቀው ነገር የለም እንዴ?
- ታዲያ ስለየቱ ፕሮጀክት ነው የሚያወሩት?
- ስለ አለቃችን ልጅ ሠርግ ፕሮጀክት ነዋ፡፡
- እርስዎ እኮ አስተዋሽ ነዎት፡፡
- ለዚህ አይደል እንዴ እኔ የማስፈልገው፡፡
- ምን እየታሰበ ነው ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
- አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ በውስጡ ሦስት ንዑስ ኮሚቴዎች ተዋቅረዋል፡፡
- ታዲያ እኔ ምን ልርዳዎት?
- ኮሚቴው የሚንቀሳቀስበት በጀት ያስፈልገዋል፡፡
- ታዲያ ተጨማሪ በጀት በፓርላማ እናስፈቅድ?
- እሱ አንድ አማራጭ ነው፡፡
- ካልሆነ ከሠራተኞች ደመወዝ ተቆራጭ ማድረግ ይቻላል፡፡
- ይኼንንም እንደ ሌላ አማራጭ ማየት እንችላለን፡፡
- ከዚህ ባለፈ ደግሞ ቦንድ መሸጥ እንችላለን፡፡
- የአገር ውስጥ ወይስ የውጭ?
- ግዢው የሚፈጸመው በውጭ ምንዛሪ ከሆነ የዩሮ ቦንድ ሽያጭ ማድረግ እንችላለን፡፡
- ይሄ የተሻለ ሐሳብ ሳይሆን አልቀረም፡፡
- ስለዚህ ዩሮ ቦንድ ይሁን?
- በቃ ዩሮ ቦንድ!
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]
- ሦስቱም ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፡፡
- በጣም ጥሩ፡፡
- የኮሚቴዎቹ ሰብሳቢዎችም እዚህ ስላሉ ቢያናግሯቸው ጥሩ ነው፡፡
- አስገባቸው፡፡
[የኮሚቴዎቹ ሰብሳቢዎች የክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገቡ፡፡ ከከብት አፈላላጊ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጋር ውይይታቸ ውን ቀጠሉ]
- በመጀመሪያ ክቡር ሚኒስትር የዚህ ኮሚቴ ሰብሳቢ አድርገው ስለሾሙኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
- ሹመት ቀላል ነገር አይደለም፣ ኃላፊነትም አለበት፡፡
- አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ዋናው ሥራህ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
- እሱን ከእርስዎ ለመቀበል ነው የመጣሁት፡፡
- ያው የኮሚቴው ስም እንደሚገልጸው፣ ዋናው ሥራህ ከብት ማፈላለግ ነው፡፡
- መፍትሔ የማፈላለግ ሥራ ነው ያሉኝ?
- ከብት የማፈላለግ ሥራ፡፡
- ከየት ልጀምር ከካራ፣ ከሰበታ ወይስ ከቡራዩ?
- እንዲህ አቅልለህ አትየው፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ለፕሮጀክቱ አስፈላጊ ከሆነ ከአውሮፓም ሆነ ከእስያ አማርጠን ዓይተን ነው ከብቶቹን የምንገዛው፡፡
- ደስ ይለኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ ከብቶቹ ልማታችን በግልጽ የሚናገሩ መሆን አለባቸው፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በዛ ላይ አረንጓዴ ኢኮኖሚን የሚያመላክቱ መሆን አለባቸው፡፡
- አረንጓዴ ከብት አለ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ከፈለግህ አረንጓዴ ቀለም ቀባቸው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከከብት ገዢ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጋር መወያየት ጀመሩ]
- የአንተ ዋነኛ ሥራ በአፈላላጊ ኮሚቴው ሪኮመንዴሽን መሠረት የከብት ግዢውን መፈጸም ነው፡፡
- ምንም ችግር የለውም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ የግዥ ሥርዓቱ ግልጽና ከሙስና የፀዳ መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡
- ስለዚህ ግልጽ ጨረታ እናውጣ ማለት ነው?
- ግልጽ ይሁን ውስን የሚለው በኋላ የሚታይ ጉዳይ ይሆናል፡፡
- ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ወይስ ለውጭ ኩባንያዎች ይሰጥ?
- እሱ ከውጭ ምንዛሪ ጋር የሚያያዝ ስለሆነ በኋላ እንወስናለን፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከከብት አራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጋር መወያየት ጀመሩ]
- ሚኒስትር ጋ ስትመጣ እንኳን ፕሮቶኮልህን አትጠብቅም?
- ክቡር ሚኒስትር ያው ከተማ ውስጥ ብዙ የእርድ ሥራዋች ስለነበሩብኝ ነው፡፡
- የምን እርድ?
- እርድ እኮ በየቦታው ነው ያለው፤ ነጋዴው ያርዳል፣ ባለሥልጣኑ ያርዳል፣ ካድሬው ያርዳል፣ ብቻ ብዙ እርድ አለ፡፡
- ለማንኛውም ይህ የእርድ ኮሚቴ ዓለም ላይ አለ የተባለውን የእርድ ቴክኖሎጂ መጠቀም አለበት፡፡
- በደስታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እዚህ ላይ የዕውቀት ሽግግር መኖሩን ማረጋገጥ አለብን፡፡
- ልክ ብለዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እነዚህ ኮሚቴዎች ውስጥ ራሴ መግባት እፈልጋለሁ፡፡
- ስለዚህ ኮሚቴዎቹ ለእርስዎ ሪፖርት ያድርጉዋ፡፡
- ከዚያም ባለፈ ሥራዎቹ ላይ መሳተፍ እፈልጋለሁ፡፡
- ለምን?
- በቃ ፕሮጀክቱ እንዲደናቀፍ ስለማልፈልግ፣ ራሴው መግባት አለብኝ፡፡
- ስለዚህ ምን ላድርግልዎት?
- ለእኔና ለከብት አፈላላጊው የፕሌን ትኬት ግዛልን፡፡
- ወዴት ሊሄዱ?
- ወደ አውሮፓና እስያ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአውሮፓ ሆነው ለሚስታቸው ደወሉ]
- ምን ዓይነት ፕሮጀክት ገጥሞህ ነው እንዲህ የዘጋኸኝ?
- ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ይዤ ነው፡፡
- እኮ ምን?
- በስልክ አይወራም፡፡
- ለማንኛውም ባልሽ የት ሄዶ ጠፋ ብሎ ብዙ ሰው ጠየቀኝ፡፡
- ብዙ ሰው ደግሞ የት አግኝተሽ ነው?
- ሠርጉ ላይ ነዋ፡፡
- የማን ሠርግ?
- የአለቃህ ልጅ፡፡
- አለፈ እንዴ?