Wednesday, April 17, 2024

ማገገም በጀመረው የአፍሪካ ቀንድ የኃያላኖች ፍላጎትና የኢትዮጵያ ሥጋት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ፈረንሣይ በምሥራቁ የአኅጉሪቷ ክፍል ያን ያህል ስፋት ያለው ሚና ባይኖራትም በአፍሪካ ቀንድ በምትገኘው ትንሿ ጂቡቲ ውስጥ ያላት መሠረት ግን የማይናወጥ የሚባል ዓይነት ነው፡፡ ቢሆንም በዚህች ትንሽ አገር አሜሪካም ብትሆን ያላት መሠረት ቀላል የማይባል ነው፡፡ ለኃያሏ አገር በመላው ዓለም ከሚገኙ ዋና ዋና ለፔንታጎን ወይም ለአሜሪካ የባህር ኃይል ስትራቴጂካዊና ወታደራዊ ቀጣናዎቹ በዋናነት ከሚጠቀሱ የጂኦ ፖለቲካል ሥፍራዎች አንዱ ነው፡፡

በቅርቡ ደግሞ የፈረንሣይ ወይም የባላንጣዋን አሜሪካ ዓይነት የወታደራዊ ቀጣና ተስፋፊነት በማሳየት፣ በአኅጉሪቱ ቀንድ በተለይም በጂቡቲ የራሷን ወታደራዊ ቀጣና በመገንባት የተቀላቀለችው ቻይና ነች፡፡

ድንገተኛው የሳዑዲ ዓረቢያና አጋሮቿ በየመን የሚንቀሳቀሱትን የሁቲ አማፅያን ለመደብደብ በኤርትራ መክተምና ለዓመታት ከዓለም ተገልሎ በተጣለበት ማዕቀብ እየተሽመደመደ ይገኝ ለነበረው በኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት፣ ያልታሰበ ሲሳይ በማምጣት ተደፍቶ የቆየውን አንገቱን ቀና እንዲያደርግ ረድቶታል፡፡

በሌላ በኩል የኢራን ኩባንያ የአሰብን ወደብ በኪራይ ወደ ግል ይዞታ ለማድረግ የነበረው ሙከራ ሊጠቀስ የሚችልና የዓረብ አገሮችን ወደ አፍሪካ ቀንድ የሚደረግ የመስፋፋት እንቅስቃሴ የሚያሳይ ነው፡፡

እንዲሁም ከዚሁ ክፍለ አኅጉር ተመሳሳይ የመስፋፋት እንቅስቃሴን ከሚያሳዩ ዋቢዎች ሌላኛው፣ የዱባይ ኩባንያ በኤርትራ ግዛት ውስጥ ያለውን የምፅዋ ወደብ የማስተዳደሩ እንቅስቃሴ አንዱ ነው፡፡

የአፍሪካ ቀንድ በዘመናት በጦርነት መታመሱና የአክራሪነት የመስፋፋት አባዜነትን ተከትሎ የሽብርተኛ መፍለቂያ በመሆኑ፣ የተለያዩ የምዕራባውያንና ሌሎች አገሮችን ቀልብ ይዞ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

በተለይ ከ1990ዎቹ ጀምሮ መንግሥት አልባ በመሆን በጦርነት ስትደቆስ የቆየችው ሶማሊያ ከጎረቤት አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ እንዲሁም እስከ አሜሪካና የአውሮፓ አገሮች ድረስ የትኩረት መስህብ ሆና አሳልፋለች፡፡

በተለይም ከኢስላማዊ አክራሪነትና ከዓለም አቀፍ አሸባሪነት ጋር ተያይዞ የሶማሊያን ሰላም ለማስፈንና ማዕከላዊ መንግሥትን ለማቋቋም ኢትዮጵያ ትልቁን ኃላፊነትና መስዋዕትነት ለመክፈል መገደዷ ይታወቃል፡፡ የአፍሪካ ኅብረትም ቢሆን የራሱን ጥረት ለማሳየት ሲሞክር ይታያል፡፡

በአንፃራዊነት ዛሬ ሶማሊያ ከዓመታት አንገብጋቢው የጦርነት ወላፈን ትንሽ ፋታ ያገኘች ይመስላል፡፡ ለዚህም ደግሞ የኢትዮጵያ እገዛና ድርሻ ቁልፍ ቦታ ሲኖረው፣ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የፀረ ሽብርተኝነት የአካባቢያዊ ወታደራዊ አጋርነትን በጠንካራ የጋራ ትስስር በተግባር ያሳየ መሆኑም፣ የሁለቱም አገሮች መንግሥታት በተደጋጋሚ የሚመሰክሩለት ነው፡፡

በአጠቃላይ ቀጣናው አፍሪካን ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር የሚያገናኘው የኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ የተዘረጋው የቀይ ባህር መገኛ በመሆኑ፣ እንደ ዋነኛ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ እንዲሁም ቁልፍ የወታደራዊ ስትራቴጂካዊ መስመር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ይህ ደግሞ የተለያዩ አገሮችን ቀልብ መሳብ መቻሉ ግልጽ ነው፡፡ በተለይ የቀይ ባህር አፍሪካን ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከእስያ እንዲሁም በሜዲትራኒያን በኩል ከአውሮፓ አገሮች ጋር በማስተሳሰሩ እንደ ቁልፍ የንግድ ኮሪደር በመሆን ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አንፃር፣ የተለያዩ አገሮችን በሽሚያና የየራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ወደ ተቀራማችነት እያንደረደረ ይገኛል፡፡

ይህ ደግሞ የተለያዩ የመካከለኛው ምሥራቅንና የአውሮፓ አገሮችን መንግሥታት ከተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መንግሥታት ጋር በጋራና በግል ጥቅም ለማስተሳሰር የሚደረገው ፉክክር፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመነደገ መምጣቱ ይስተዋላል፡፡

ለዚህ ደግሞ በሳዑዲ ዓረቢያ አውራነት ኩዌትና ኳታርን ጨምሮ የየመን አማፅያንን ለመውጋት በኤርትራ የመሠረቱት የወታደራዊ እንቅስቃሴ አንዱ ማረጋገጫ ነው፡፡ እንዲሁም ቱርክ ከ20 ዓመታት በኋላ በሶማሊያ ውስጥ ወታደራዊ እንቅስቃሴን በመተግበር የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች፡፡ አንዳንዶች የዚህ ዓይነቱ አዲስ ጅምር ደግሞ ለኤርትራም ሆነ ለሶማሊያ መንግሥታት ወይም ለሌሎች አስተናጋጅ አገሮች የራሱ የሆነ ተጠቃሚነትን የሚያመጣ ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ሌሎች ደግሞ የሥጋት ምንጭ በመሆኑ በጥርጣሬና በጎጂ ገጽታው ሊታይ እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ በኩልም ቢሆን የዚህ ዓይነቱ ከኃያላን አገሮች ጋር የተፈጠረው ትስስር ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረጉ ግልጽ ቢሆንም፣ በተለይ ለኢትዮጵያ ለራሷ ሉዓላዊነትም ሆነ ለቀጣናው ሥጋት እንዳለው የሚጠቁሙ አልጠፉም፡፡ በተለይ በዓይነ ቁራኛ ለምታየው አንዳንዴም ጦር የሚያማዝዛት የሻዕቢያ መንግሥት ከሌሎች አገሮች ጋር የፈጠረው ወታደራዊ አጋርነት ሥጋት መሆኑን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና በመንግሥታቸው በግልጽ ተሰምሮበታል፡፡

በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ሌሎች አገሮችና ተንታኞች ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት የኢኮኖሚያዊና የፖለቲካዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት እያደገ መጥቷል በሚባልበት በአሁኑ ወቅት፣ በጎረቤት አገሮች የሌሎች አገሮች ፖለቲካዊና ወታደራዊ ትስስር መስፋፋት መታየቱ የኢትዮጵያ መንግሥትን በሥጋት እንዲመለከት ከማንቃቱ ባሻገር፣ አዲስ ሥልትና አቅጣጫ እንዲቀይስ ቆም ብሎ እንዲያስብ ሊያደርገው ይገባል የሚሉ ሐሳቦች ከወዲሁ እየተጠቆሙ ይገኛሉ፡፡

በተለይ በኤርትራና በዓረብ አገሮች መንግሥታት የሚደረገው እንቅስቃሴ ችላ ሊባል የማይችል የደኅንነት ጉዳይ ሲሆን፣ ይህንንም በተመለከተ በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ጉዳዩ ወደ ጎን ተብሎ አንዲት ሌሊት እንኳ ችላ ተብሎ የማያድርና መንግሥት በቀላሉ እንዳልተመለከተው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ከኤርትራ በስተቀር ከሁሉም የጎረቤት አገሮች ጋር ኢትዮጵያ የጋራ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና የደኅንነት ትብብርና የስምምነት መስመር መዘርጋቷን የሚናገረው መንግሥት፣ በቀጣናው ሰላምንና ደኅንነትን እንዲሁም መረጋጋትን በመፍጠር ስኬታማ አስተዋጽኦ በማበርከት የዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ ከቀጣናው አገሮችና ከፍ ባለ ማማ መቀመጥ መቻሉን ይገልጻል፡፡

የጂቡቲንም ሆነ የኬንያንና የታንዛኒያን ያህል ብዛት ያላቸው የአሜሪካን ወታደሮች ባይሰፍሩባትም፣ ኢትዮጵያ ለፔንታጎን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ማስኬጃ አነስተኛ የዕዝ ጣቢያ በመሆን የአሜሪካን አጋርነት በማሳየት ላይ ነች፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ የአልሸባብን የሽብር ጥቃት በማክሰም የአሜሪካ ጦር የአርባ ምንጭን የአውሮፕላን ማረፊያ የሰው አልባ የጦር አውሮፕላን (Drone) መንደርደሪያ በቅርቡ ቢዘጋም፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ያላትን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ይጠቀሳል፡፡

ይህ መሰሉ የፀረ ሽብርተኝነትና የጋራ ወታደራዊ አጋርነት ኢትዮጵያ የራሴም ሥጋት ነው ብላ የምትቆጥረውን ወደ መረጋጋትና ሰላማዊ ቀጣናነትን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት ካለው እገዛ በላይ፣ አገሪቱ ከአሜሪካ መንግሥት ያስገኘላት ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ (የገንዘብና የጦር መሣሪያ ቁሳዊ ዕርዳታ) ቀላል አይደለም፡፡

የዚህ ዓይነቱ ዕርዳታ ደግሞ ኢትዮጵያ በቀጣናው የበላይነት እንዲኖራት ከማድረጉም በላይ፣ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከአሜሪካ ትልቁን ዕርዳታ ከሚያገኙ አገሮች ከእስራኤል፣ ከግብፅ፣ ከፓኪስታንና ከአፍጋኒስታን ቀጥሎ በአምስተኛነት እንድትቆጠር አድርጓታል፡፡

እንደ አሜሪካ ሁሉ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ትልቋ የንግድና ኢንቨስትመንት ሽርኳ የሆነችው ቻይናም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምሥራቅ አፍሪካ ወታደራዊ ተስፋፊነት እያሳየች መሆኑ ይነገራል፡፡ በተለይም በጂቡቲ የራሷን የባህር ኃይሏን በማስፈር ቀጣናውን መቀላቀሏ ለዚህ እንደ አብነት ይጠቀሳል፡፡ ምንም እንኳ የቻይና ጦር በጂቡቲም ሆነ በቀጣናው መሥፈር ለኢትዮጵያ መንግሥት ለጊዜው ካላቸው ወዳጅነት አንፃር ይህ ነው የሚባል ሥጋት ባይፈጥርም፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው ካላት ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ትኩረት አያሻውም ተብሎ ሊተው አይችልም፡፡

ሌላኛው ትልቅ የትኩረት አቅጣጫ የሆነው በሶማሊያ ውስጥ ያለው የሰላምና መረጋጋት ጉዳይ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአልሸባብ መዳከምና በአንፃሩ በአፍሪካ ኅብረትና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እየተደገፈ ያለው የሶማሊያ መንግሥት እየተጠናከረ መምጣቱ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ለጊዜው ለኢትዮጵያ ቀድሞ ከነበሩት የሶማሊያ አክራሪ አንጃዎችና ጂሃዲስቶች የሽብር ሥጋት በመጠኑ የመቀነስ አዝማሚያ እየታየ ነው፡፡ በተለይ በ1998 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ‹‹ግልጽና ያፈጠጠ ሥጋት›› ተጋርጧል በማለት የመከላከያ ሠራዊት የሶማሊያን ድንበር ጥሶ በመግባት በወቅቱ የሥጋት ኃይል የነበረውን የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኃይል ሙሉ ለሙሉ ደምስሶ፣ ከሦስት ዓመታት በኋላ ተመልሷል፡፡

ነገር ግን ከእስላማዊ ፍርድ ቤቶች መደምሰስ በኋላ የኢትዮጵያ ጦር መውጣቱን ተከትሎ፣ የወጣቶች ክንፍ የነበሩ ኃያሎች አልሸባብ በሚል ስያሜ ለዳግም ትርምስ መነሳት ለኢትዮጵያም ሆነ ለቀጣናው ሌላኛው ሥጋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡

ቢሆንም ይህንን አልሸባብ የተሰኘውን የሽብር ቡድን ለማጥፋት ኢትዮጵያ ዳግም ጦር ማዝመቷ ባለመፈለጉ፣ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር (አሚሶም) አቋቁሞ ከተለያዩ አባል አገሮች የተውጣጣ ጦር ላከ፡፡ ነገር ግን የኅብረቱ ጦር ተልዕኮውን በታሰበው መንገድ ለማውጣት ካለመቻሉም በላይ ያለው ሚና የሶማሊያን መንግሥት በሞቃዲሾ ከመከላከል አልዘለለም፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ በኅብረቱ በቀረበ ጥያቄ መሠረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እ.ኤ.አ. በ2013፣ 4,200 ጦር ለመላክ መገደዱን መንግሥት በወቅቱ መግለጹ ይታወሳል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ጦር አልሸባብን ከማዕከላዊ የሶማሊያ አካባቢዎች በማፅዳት ወደ ጠረፍ አካባቢዎች እንዲሸሽ ለማድረግ ብዙም ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ አሁን የአልሸባብ የደፈጣ ጥቃትና የቦምብ ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ባይቆምም፣ ሶማሊያ የተሻለ አንፃራዊ ሰላም ማግኘት እንድትችል የኢትዮጵያ ሚና ትልቁን ድርሻ መያዙን፣ የሶማሊያም መንግሥት ሆኑ ሌሎች ይገልጻሉ፡፡ እንዲሁም ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ቡሩንዲና የአፍሪካ ኅብረትም ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለዛሬዋ ሶማሊያ ደኅንነት የማይናቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ለዚህ መሻሻል ደግሞ እንደ አብነት ሊጠቀሱ ከሚችሉ ማሳያዎች አንዱ እ.ኤ.አ. በ2014 ለመጀመሪያ ጊዜ የቱርክ አየር መንገድ ወደ ሞቃዲሾ በመብረር፣ ከ25 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሞቃዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ ያረፈ ዓለም አቀፍ የበረራ ትራንስፖርት መሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለሶማሊያ ሰላም መስፈን ጦራቸውን በመላክ የሰላም ማረጋጋቱን ሥራ የተወጡ አገሮች እንኳ የየራሳቸው አየር መንገድ ሞቃዲሾ በመላክ ለማሳረፍ ከመሞከራቸው በፊት፣ የቱርክ አየር መንገድ ቀድሞ መሞከሩ በወቅቱ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ሆኖ ተነስቷል፡፡

የቱርክ መንግሥት ቀድሞ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያስደፈረው ድርጊት፣ ቱርክ በሶማሊያ ያላትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ፍላጎት ያሳያል ብለው ቀድመው የተነበዩም ነበሩ፡፡ ይህ ትንበያቸው ደግሞ ከሁለት ዓመታት በኋላ እውነታነት እንዳለው ሳያሳይ አልቀረም፡፡ ያም ደግሞ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ቱርክ በሶማሊያ የራሷን የጦር ማዘዣ ጣቢያ ለማቋቋም ማሰቧን ገልጻለች፡፡

ሌላ ቅርምት በቀጣናው

በሶማሊያ ውስጥ ለዘመናት የቆየው የእርስ በርስ ጦርነት ከራሷ ሶማሊያ አልፎ ለአካባቢው ሰላም መናጋት እንደነበረው ከሚጠቀሰው ሥጋት በተጨማሪ፣ በቀጣናው የባህር ትራንስፖርትን በማወክ የሶማሊያ የባህር ላይ ዘራፊዎች ከህንድ ውቅያኖስ እስከ ሜዲትራንያን ባህር ድረስ የተዘረጋው የባህር ላይ ውንብድና ሌላው ሊዘነጋ የማይችል የቀጣናው ጠባሳ ነበር፡፡ በተለይ የዚህ የባህር ላይ ዘረፋ በአካባቢው ካሉ አገሮች ባልተናነሰ ከጃፓን እስከ አሜሪካ፣ ከእንግሊዝ እስከ ህንድና ሩሲያን ጨምሮ የተለያዩ ኃያላን አገሮች መንግሥታታን ያሳሰበ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ አገሮቹ የባህር ኃይላቸውን በማሰማራት በዘራፊዎች ላይ ወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወስዱ አስገድዷል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዕርምጃ ደግሞ አጠቃላይ ቀጣናው ምን ያህል የብዙኃን ኃያላን አገሮችን ቀልብ የሚስብ እንደሆነ ጎልቶ የሚታይ እውነታ ነው በማለት የሚከራከሩም አሉ፡፡

የቀጣናው አገሮች እርስ በርሳቸው፣ በተናጠልና በጋራ ካሉዋቸው ስትራቴጂካዊ ግንኙነቶችንና አጋርነትን በመመሥረት ማንኛውም አገር የግሉንም የሆነ የጋራ ጥቅሞችን በዘላቂነት ለመጠበቅና የማስከበር ንቁ ተሳትፎ ማስፈለጉ የሚሰመርበት ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በዚሁ ጉዳይ ኢትዮጵያም በቀጣናው የሁልጊዜም ወቅታዊ ጉዳዮችንና ዕርምጃዎችን ሁሉ በንቃት መከታተል፣ ከነባራዊ እውነታዎች እኩል መንቀሳቀስና መከታተል እንደሚኖርባት የሚያስገድዱ ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች አሏት፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ የዶክትሬት ተማሪ የሆኑት አቶ ዳርእስከዳር ታዬ በአፍሪካ ቀንድ ባሉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጥናት አካሂዋል፡፡ በቅርቡ በሳዑዲ ዓረቢያ ጥምረት በሚመራውና በየመን አማፂዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችለው ከኤርትራ ጋር የተካሄደውን ስምምነት በሥጋት ይመለከቱታል፡፡ ምሁሩ እንደሚሉት የሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ቀጣናው መጠጋት ለኤርትራ መልካም አጋጣሚ ያበረከተላት በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ በኩል ጥንቃቄ የተሞላበት ትኩረት እንደሚያሻ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ትልልቅ አገሮች ወደ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ ፊታቸውን ማዞራቸው እየታየ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መነሻው በመካከለኛው የምሥራቅ የዓረብ አገሮች ተቃውሞ ወይም አመፅ (Arab Spring) ከተከሰተ በኋላ ነገሮች ሁሉ ውስብስብ መሆናቸው ነው፡፡ አካባቢው የዓለም የኃይል ምንጭ መገኛ ማዕከል ቢሆንም፣ አሁን ያለበት ሁኔታ ግን መረጋጋት አይታይበትም፡፡ ስለዚህ ይህንን የኢነርጂ ፍላጎታቸውን ለማሟላት በዓረብ አገሮች ያለውን አለመረጋጋት እንዲቀጥል በኃያላን አገሮች በኩል አይፈለግም፡፡ በዚህ የተነሳ የማሪታይም ሴኩሪቲን ለማጠናከር ሲሉ ወደ አፍሪካ ቀንድ እያመሩ ነው፤›› ሲሉም ምሁሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ቀጣና የኢራንና የሳዑዲ ዓረቢያ መጫወቻ እንዲሆንም ስለማይፈልጉ ነው ይላሉ፡፡

‹‹በተደጋጋሚ እንደምናየው ከዓረብ ስፕሪንግ በኋላ ችግሮች ከመሻሻል ይልቅ እየተስፋፉ ነው የሄዱት፡፡ ይኸው የዓረብ ስፕሪንግ በተለያዩ አገሮች የመንግሥት ለውጥ ቢያመጣም እንደ የመን ባሉ አገሮች ግን የተባባሰ ችግር እያመጣ ነው፤›› የሚሉት አቶ ዳርእስከዳር፣ ‹‹የየመን ቀውስ ደግሞ ለኢትዮጵያም የሥጋት ምንጭ መሆኑ የማይቀር ነው፤›› ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል የነኢራንና ሳዑዲ ዓረቢያ ፍጥጫን ተከትሎ ሌሎች አገሮች በጀርባ የመንቀሳቀስ ሁኔታ የሚያሳዩ ከሆነ፣ ለምሳሌ እንደ ሶማሊያና ጂቡቲ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚያጋድሉበት ሁኔታ በምሥራቅ አፍሪካ ሌላ ዓይነት ቀውስ እንዳይፈጥር ያሠጋል፡፡ ኃያላን አገሮች ደግሞ ያ ዓይነት ሁኔታ እንዲፈጥር ስለማይፈልጉ ነው ወታደራዊ ቅኝታቸውንና የባህር ኃይላቸውን በአፍሪካ ቀንድ ማጠናከር የሚፈልጉት ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

ሌላው ምሁሩ ያነሱት ጉዳይ ኤርትራ የሳዑዲ ዓረቢያን ድጋፍ የማግኘቷ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ይህ ለኤርትራ መልካም አጋጣሚ ሲሆንላት በቀጣናው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሻከረ ግንኙነት ወደ ሌላ ፍጥጫ እንዳይወስደው ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የኤርትራ መንግሥት ከጂቡቲ ጋር የሻከረ ግንኙነት ቢኖረውም፣ ሰሞኑን የጂቡቲ መንግሥትም ለሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ድጋፍ እየሰጠ መሆኑ ነው፡፡

ባለፈው ወር ከሪፖርተር ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በበኩላቸው፣ እነ ሳዑዲ ዓረቢያ ከኤርትራ ጋር ያደረጉት ስምምነትን መንግሥት በጥርጣሬ እንደሚመለከተው ገልጸው ነበር፡፡

‹‹በቅርቡ እኛ የምናውቀው ሁለቱ አገሮች በተለይ ደግሞ ዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ አሰብን ተጠቅማ የመን ላይ ያላቸውን ስትራትጂያዊ ጉዳይ ለማስታገስ፣ አውሮፕላናቸው የመን ላይ የኦፕሬሽን ሥራ እንደሚሠራ ይታወቃል፡፡ ይኼን ጉዳይ ነግረናቸዋል፡፡ ከሚመለከታቸው አካላትም ጋር በግልጽ ተወያይተናል፡፡ የኤርትራን መንግሥት ደግፈው ያልገቡ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ዋናው ዓላማቸው የመን ላይ ያለውን ስትራቴጂያዊ ጉዳያቸውን እዚያ ሆነው አውሮፕላን እየላኩ ለመደብደብ እንዲመቻቸው ነው፡፡ በቀይ ባህር በኩልም የሚደረገው ጉዞና ምልልስን በተመለከተ የቀይ ባህር ስምምነት አላቸው፤›› ሲሉ አቶ ኃይለ ማርያም ገልጸው ነበር፡፡

‹‹ዋናው ጉዳይ የኢትዮጵያ ፀጥታና ደኅንነትን በተመለከተ ምን ተፅዕኖ ያመጣል የሚለው ነው፡፡ በዚህ ላይ ከሁለቱም አገሮች ጋር ግልጽ ውይይት አድርገናል፡፡ እኛ የኢትዮጵያን ሰላም፣ አንድነት፣ ዕድገትና ልማት የሚያደናቅፍ አምስት ሳንቲም አንሠራም ብለዋል፡፡ ይሄ ታክቲክ የመን ላይ ላለን ኦፕሬሽን ቦታው ስለሚመቸን ብቻ ያደረግነው ነው ብለዋል፡፡ የሆኖ ሆኖ ይህን ኦፕሬሽን ቶሎ ፈጽመን ከዚያ አካባቢ ለመውጣት ዝግጁ ነን ብለው ነግረውናል፡፡ ነገር ግን እኛ አስጠንቅቀናቸዋል፡፡ እኛ በዚህ አካባቢ በምታደርጉት እንቅስቃሴ የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጋር ንክኪ ካለው የራሳችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር ስንል በምንወስደው ዕርምጃ ብትጐዱ እኛ ተጠያቂዎች አይደለንም፡፡ ምክንያቱም እኛ አስቀድመን ይኼን ጉዳይ ከእናንተ ጋር አልተመካከርንም፣፣ እኛንም አላማከራችሁንም፡፡ ፍላጐታችሁ ይገባናል፡፡ ነገር ግን እኛ ሉዓላዊ አገር እንደ መሆናችን መጠን የኤርትራ መንግሥት የተለየ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ከሆነ፣ ለዚያ እንቅስቃሴ አፀፋ ስንወስድ የእናንተ ፍላጐት ቢጐዳ የእኛ ችግር እንዳይደለ እንድትረዱ ብለናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ምንም እንኳ የኢትዮጵያና የጂቡቲ መንግሥታት ያላቸው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ከመሻሻል ባለፈ ወደ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለመግባት እየጣሩ ቢሆንም፣ በቀጣናው ያለውን ሁኔታ ግን በጥንቃቄና በብስለት የኢትዮጵያ መንግሥት ማየት እንዳለበት አቶ ዳርእስከዳር ያሳስባሉ፡፡

‹‹ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት አላት፡፡ በመሠረተ ልማት በጋራ እየተሳሰሩ የጋራ የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ለመገንባት እየሞከሩ ነው፡፡ በሌላ በኩል ጂቡቲ እንዲሁ ከነሳዑዲ ዓረቢያም ሆኑ ከሌሎች አገሮች ጋር የራሷ የሆነ ግንኙነት ሊኖራት ይችላል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ጋር ያላት ግንኙነት ለኢትዮጵያ ህልውናም ሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝነት አለው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ጋር ያላትን ግንኙነት በትክክልም ወደ ላቀ ትስስርና የኢኮኖሚው ውህደት ዕውን ማድረጉ አማራጭ የሌለው ዕርምጃ ነው፤›› ብለዋል አቶ ዳርእስከዳር፡፡

በሌላ በኩል ሁለቱ ኃያላን አገሮች አሜካና ቻይና በጂቡቲ መክተማቸው ለኢትዮጵያ ከሥጋት ይልቅ አዎንታዊ ጠቀሜታ እንደሚያመዝን ያምናሉ፡፡ ‹‹አሜሪካና ቻይና በየግላቸው የራሳቸው ውጥረትና ፉክክር ቢኖራቸውም፣ ሁለቱም ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት ስላላቸው የእነሱ በቀጣናው መኖር ኢትዮጵያን ሊያሠጋት ይችላል ብዬ አላስብም፤›› ብለዋል፡፡

በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጠራው ስብሰባ ላይ ሪፖርት ያቀረቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ከጂቡቲ ጋር እየተካሄደ ያለው ሁሉን አቀፍ የመሠረተ ልማት ትስስር ወደ ሙሉ የኢኮኖሚ ውህደት የሚስችለው ዕቅድ እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -