የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውይይት የደረሰበት ደረጃን አስመልክቶ፣ ከአገሪቱ የመስኖና የመከላከያ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ፡፡
ጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሚኒስትሮቻቸው ጋር አደረጉት ስለተባለው ውይይት የአገሪቱ ሚዲያዎች በዝርዝር ያሉት ነገር የለም፡፡ በዚህ ውይይት ላይ ከተነሱት ነጥቦች የተገለጸው፣ ኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን ባለሥልጣናትን የግድቡ ቦታ ድረስ ጉብኝት እንዲያደርጉ መጋበዟ ብቻ ነው፡፡
ዝርዝር ውይይቱ በአገሪቱ ሚዲያዎች ባይገለጽም ግብፅ የዓባይን ጉዳይ ከጥንት ጀምሮ የምትከታተለው በደኅንነት ተቋማቷ መሆኑን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይናገራሉ፡፡
ግድቡን በተመለከተ ውይይት በሚደረግበት ወቅት በኢትዮጵያ በኩል ከስድስት የማይበልጡ ተወያዮች ሲላኩ፣ ከግብፅ ግን ከ20 በላይ እንደሚመጡና አብዛኞቹም የዘርፉ ባለሙያዎች አለመሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ግብፅ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ ወደ መፍትሔ መምጣት እንደምትፈልግ ገልጸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሒም ጋንደር ጋር በሁለቱ አገሮች ጉዳዮች ዙሪያ እሑድ ጥር 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በተወያዩበት ወቅት መሆኑን የግብፅ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
አልሲሲ፣ ‹‹ዓባይ ለግብፅ ብቸኛ የውኃ ምንጭ በመሆኑ መግባባትና መፍትሔ ላይ መድረስ ወሳኝ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በመሪዎች ደረጃ የፈረሙት የመርህ መገለጫ ስምምነት ተግባራዊነት ተጨባጭ እንዲሆን የመንግሥታቱ ፍላጎት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ግብፅ የተጓዙት የሁለቱ መንግሥታት የጋራ ኮሚሽን ጉባዔ የሚመቻችበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ቢሆንም፣ ሁለቱ አገሮች ለመቅረፍ ከሚፈልጉት የጋራ ድንበር ውዝግብ በላይ የህዳሴው ግድብ ጎልቶ መውጣቱን ከአገሪቱ ሚዲያዎች ዘገባ መረዳት ተችሏል፡፡
የህዳሴው ግድብ የደኅንነት ሁኔታ ያልተረጋገጠ በመሆኑ ሱዳንን ሊያጠፋ ይችላል የሚል ጥያቄ በማንሳት፣ የግብፅ ሚዲያ ዘጋቢዎች የሚኒስትሩን ስሜት ለማወቅ ሞክረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ግን የህዳሴው ግድብን በተመለከተ ሱዳን አወያይ ሳይሆን ተዋናይ ናት ብለዋል፡፡ የህዳሴው ግድብ ታዋቂ በሆነ ዓለም አቀፍ ኩባንያ የሚገነባ መሆኑን በመጥቀስ ሥጋት እንደሌለባቸው አስታውቀዋል፡፡