– የባንኮችን ቅርንጫፎች ቁጥር ይወስናል
– አዲስ የቼክ አገልግሎት መመርያ ያወጣል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ ተፈጻሚ የሆኑ አዳዲስ መመርያዎች እየተዘጋጁ ነው፡፡ በቅርቡም ይፋ ያደርጋቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ መመርያዎች ውስጥ አንዱ፣ ባንኮች ሲቋቋሙ ምን ያህል ቅርንጫፎችን ይዘው መነሳት እንዳለባቸው የሚደነግገው መመርያ እንደሚገኝበት ታውቋል፡፡
እስካሁን ባለው አሠራር በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ውስጥ አንድ ባንክ ሲቋቋም ይህንን ያህል ቅርንጫፎች ይኖሩታል ተብሎ የተቀመጠ አንቀጽ አልነበረም፡፡ ይህ ይወጣል የተባለው መመርያ ግን ከዚህ በኋላ ለሚቋቋሙ ባንኮች ብቻ ሳይሆን፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉ ባንኮችን የሚመለከት እንደሚሆን የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ዝርዝር ማብራሪያ አይስጡበት እንጂ፣ ይህንኑ ጉዳይ ጠቆም ያደርጉ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አቶ ተክለ ወልድ ‹‹በአንድ ቅርንጫፍ ብቻ መሥራት አይቻልም፤›› ብለው ነበር፡፡ ይህ መመርያ የባንኮቹ ዝቅተኛ ቅርንጫፎች ቁጥር ምን ያህል መሆን እንዳለበት ብቻ የሚደነግግ ሳይሆን፣ ባንኮቹ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ምን ያህል ቅርንጫፎች መክፈት እንደሚኖርባቸውም የሚያመለክት ነው፡፡
አሁን በሥራ ላይ ካሉት ባንኮች ውስጥ ወደ ሥራ ሲገባ አንድ ቅርንጫፍ በመክፈት የሚታወቀው ዘመን ባንክ ነው፡፡ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት በአንድ ቅርንጫፍ ብቻ እሠራለሁ ብሎ የተነሳው ዘመን ባንክ፣ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ መመርያ አሠራሩን እንዲለውጥ እንደሚያደርገውም የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ባለፈው ዓመት መጨረሻ አንድ ባንክ በየዓመቱ የቅርንጫፎቹን ቁጥር በ25 በመቶ ማሳደግ እንዳለበት መደንገጉ የሚታወስ ሲሆን፣ አዲስ የሚወጣው መመርያም ከዚህ ጋር የተሳሰረ እንደሚሆን ታውቋል፡፡
ብሔራዊ ባንክ ከዚህ መመርያ ተጨማሪ በቅርቡ ተግባራዊ ያደርጋቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ መመርያዎች ውስጥ፣ የግል ባንኮች ከሚሰጡት ብድር ላይ 27 በመቶ ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ ከሚደነግገው መመርያ ጋር የተገናኙ እንደሚካተቱ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ተሻሽሎ ይወጣል የተባለው ይህ መመርያ ከባንኮች ውጭ ያሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ሌሎች ተቋማት በቦንድ ግዥው ተሳታፊ የሚሆኑበትን አሠራር ለመተግበር የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ ከ27 በመቶ የቦንድ ግዥ ጋር ተያይዞ የሚሻሻለው መመርያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚካተቱበት ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ ፈንድ የሚያሰባስቡ ተቋማትም በዚሁ የቦንድ ግዥ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያስችላል የተባለው ይህ መመርያ ለመንግሥት ቀርቦ ውሳኔ እየጠበቀ ነው፡፡
ከአገሪቱ የቼክ አገልግሎት ጋር በተያያዘም አዲስ መመርያ እንደሚወጣም ታውቋል፡፡ በቅርቡ ይፋ የተደረገውን አዲሱን የቼክ አገልግሎት ለማስተዋወቅ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ እንደተገለጸው፣ ከቼክ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለማስቀረት ይረዳል የተባለ መመርያ ይወጣል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ጌታሁን ናና ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡም፣ አሁን ከቼክ አሠራር ጋር በተያያዘ በሥራ ላይ ያለውን የሚያሻሽል መመርያ የሚወጣ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ይህ መመርያ ከቼክ አሠራር ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ማጭበርበሮችን ለመቆጣጠርና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነም ከነበረው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡