የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን የተሰኘ የመንግሥት የልማት ድርጅት በ15 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል እንዲቋቋም ወሰነ፡፡
ምክር ቤቱ ከወር በፊት እንዲቋቋም የወሰነውን ኮርፖሬሽን የማደራጀት ሥራ መጀመሩን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የሚቋቋመው በነዳጅ፣ በማዕድንና በባዮፊውል ሥራዎች ውስጥ በቀጥታ በመሳተፍ የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት በተገቢ ሁኔታ በማልማት የበለጠ ተጠቃሚ እንድትሆን ማስቻል መሆኑን በታኅሳስ ወር ይፋ የሆነው ማቋቋሚያ ደንብ ያስረዳል፡፡
ራሱ ወይም እንደ ሁኔታው ከሌሎች ጋር በመሆን በማዕድን፣ በነዳጅና በባዮፊውል ሥራዎች ኢንቨስትመንት ላይ መሳተፍ፣ ማልማትና ማምረት፣ በሌሎች ባለሀብቶች የሚካሄዱ ሥራዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሌሎች ኃላፊነቶቹ ናቸው፡፡
የነዳጅ ሥራ ማለት ከ‘ኦይል ሼል’ ወይም ከ‘ታር ሳንድ’ የተገኘውን ኃይድሮ ካርቦን ጨምሮ የነዳጅ ድፍድፍ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ ሲሆን ከሼል ጋዝ፣ ከድንጋይ ከሰልና ከባዮፊዩል ሥራዎች የሚመረቱ ተመሳሳይ ምርቶችን እንደሚያካትት ደንቡ ይገልጻል፡፡
‹‹የነዳጅ ሥራዎች›› ማለት ደግሞ ድፍድፍ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ መፈለግ፣ ማልማት፣ ማውጣት፣ ማምረት፣ በመሰል መለያየት፣ ማዘጋጀት፣ ማከማቸት ወደ ውጭ አገር እስከሚላክበት ወይም ለአገር ውስጥ ፍጆታ ወደሚሠራጭበት ሥፍራ ማጓጓዝና ለገበያ ማቅረብ መሆኑን፣ ከተፈጥሮ ጋዝ የተለያዩ ምርቶችን ማውጣትና የነዳጅ ድፍድፍ ዘይት ማጣራትን እንደሚጨምር ይገልጻል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ተጠሪነት ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሲሆን፣ ከተፈቀደው 15 ቢሊዮን ብር ካፒታል ውስጥ 4.017 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ነው፡፡