Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የሚከሰሰውን ለመክሰስ የሚቀጣውን ለመቅጣት ቁርጠኝነት ይኑር!

በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ በዋና ችግርነት የሚጠቀሱት የመልካም አስተዳደር መጥፋት፣ የፍትሕ አለመኖርና የሙስና መንሰራፋት ናቸው፡፡ እነዚህን ችግሮች በተባበረ ክንድ ለመደቆስ የሚቻለው የመንግሥት ቁርጠኝነት ሲኖርና መላውን የአገሪቱን ሕዝብ ዳር እስከ ዳር ማንቀሳቀስ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ለአገሪቱም ሆነ ለሕዝቡ ጠንቅ የሆኑ አስከፊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሹማምንትን ሕግ ፊት አቅርቦ በመክሰስና በማስቀጣት ብቻ ነው፡፡ መንግሥት በተደጋጋሚ እነዚህን አገር አጥፊ ችግሮች ከሥራቸው ነቅሎ ለመጣል ቢዝትም፣ በተግባር የተረጋገጠ ወሳኝ ዕርምጃ ሲወስድ አይታይም፡፡ በአመራሮችና በተዋረድ ባሉ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ፍተሻ ማድረግ መጀመሩን ቢናገርም፣ በግልጽ የሚታይ ነገር የለም፡፡ ቁርጠኝነቱ የታለ?

እርግጥ ነው በአንድ ጊዜ የሚፈታ ችግር ባይኖርም፣ መላ ሕዝቡ ተሳትፎ የሚያደርግበትና ከዲስኩር የዘለለ ተግባራዊ ዕርምጃ ጭላንጭሉ መታየት አለበት፡፡ ይህንን ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ ለማንሳት መንስዔ የሚሆኑ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ መጓደልና በሙስና መንሰራፋት ሳቢያ የተጠራቀሙ ብሶቶች ገንፍለው ሲወጡ ለአገር ሰላምና መረጋጋት ጠንቅ እየሆኑ ነው፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ በተዋረድ ሥልጣን ላይ የሚገኙ ራስ ወዳድ ግለሰቦች የሚፈጥሯቸው ችግሮች ሰሚና ተመልካች በማጣታቸው የሕዝቡ ምሬት ጣሪያ ነክቷል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች አስተዳደራዊ በደሎች በመፈጸም፣ ሥልጣንን ያላግባብ በመገልገል፣ ፍትሕ በማጓደልና የሕዝብ ሀብት በመዝረፍ የፈጸሟቸው ጥፋቶች ዛሬ አገሪቱን ዋጋ እያስከፈሉ ናቸው፡፡

በፌዴራል ደረጃ የአገልግሎት መስጫ መንግሥታዊ ተቋማት የሕዝቡ ምሬት ዋነኛ መቀስቀሻ እየሆኑ ነው፡፡ በየተቋማቱ ውስጥ የተሰገሰጉ ራስ ወዳዶችና ብቃት አልባዎች ተገቢውን አገልግሎት ለግብር ከፋዩ ሕዝብ ከመስጠት ይልቅ፣ ማንገላታት የተለመደ ተግባራቸው ነው፡፡ በዚህም በሕገወጥ መንገድ ለመክበር የሚያስችሏቸውን ዘዴዎች በማቀናበር፣ ዜጎች መብቶቻቸው የሆኑ አገልግሎቶችን በገንዘባቸው እንዲገዙ ያደርጋሉ፡፡ የእነሱ ተላላኪ በሆኑ ደላሎችና ጉዳይ አስፈጻሚዎች አማካይነት የሙስና ኔትወርክ በመፍጠር ሕዝቡን ይዘርፉታል፡፡ ሕዝቡ በአግባቡ አገልግሎት ለማግኘት የሚሄድባቸው ተቋማት ውስጥ በአገልጋይነት መንፈስ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ዜጎች ወደ ጎን ተገፍተው፣ ሕዝብን የሚያስመርሩና ለአመፅ የሚያነሳሱ እየበዙ ነው፡፡ ከራሳቸው ጥቅምና ከቡድን ፍላጎት ውጪ ማየት የሚሳናቸውን ተይዞ እስከ መቼ ይዘለቃል?

በክልል ደረጃ መሬት እየሸነሸነ ከሚሸጠው ጀምሮ አገራዊውን ራዕይ የሚያጠፋው ቁጥሩ ብዙ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ዋስትና የተሰጠበትን የዜጎች መዘዋወር፣ መሥራትና ሀብት የማፍራት መብት በመጋፋት በገዛ አገራቸው ባይተዋርነት እንዲሰማቸው ማድረግ፣ ንብረታቸውን መቀማት፣ ማፈናቀልና ማባረር የሚፈጽሙ አሉ፡፡ በተጨማሪም ጥቂቶች የአገር ሀብት እየዘረፉ ወይም በኔትወርካቸው አማካይነት ያለ ጨረታና ያለ ውድድር የሚገኙ ጥቅሞችን እያጋበሱ፣ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ወገኖችን ምሬት ይጨምራሉ፡፡ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ በአንድ ጀንበር የሚፈጠሩ ሚሊየነሮች እየታዩ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው ዕምነት ቢሸረሸር ምን ይደንቃል? እነዚህን ከሥርዓተ መዋቅሩ ውስጥ መንጥሮ አውጥቶ ለሕግ ማቅረብስ ለምን ያቅታል?

እነዚህ ወገኖች በሕዝቡ ውስጥ አንድነትን ከመስበክ ይልቅ ልዩነትን፣ በሕዝቦቿ መፈቃቀድና መፈላለግ ላይ የተመሠረች አንዲት ጠንካራ አገር እንድትኖር ከመፈለግ ይልቅ መበታተንን፣ ከኅብረ ብሔራዊነት ይልቅ ክልላዊነትን፣ ለሕዝቦቿ ተስፋ የሆነች ዴሞክራሲያዊትና የበለፀገች አገር ከመናፈቅ ይልቅ ጥበትን፣ ወዘተ የሚያራምዱ በመሆናቸው በሕዝቡ ውስጥ አለመተማመን እንዲኖር ተግተው ይሠራሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ወጥቶ ባለፉት ሃያ ዓመታት በሕዝቦቿ መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተች ፌዴላራዊት አገር አለች ቢባልም፣ ከጠበበ አመለካከት መውጣት የተሳናቸውና ራዕይ አልባ የሆኑ ራስ ወዳዶች እንቅፋት እየሆኑ ነው፡፡ መልካም አስተዳደርን እያጠፉ፣ ፍትሕን እየደረመሱ፣ ሙስናን እያስፋፉ የአገራዊ አንድነት ማገሮችን ይሰባብራሉ፡፡ ከሕዝቡ ፍላጎት በተቃራኒ በመሆን የአገርን ህልውና ይፈታተናሉ፡፡ እነዚህ እስከ መቼ እንዲህ እያመሱ ይቀጥላሉ?

የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የፍትሕ መጓደልና የሙስና መንሰራፋት የሚያመጡት ምሬት ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ጠንቅ ነው ሲባል እንዲሁ አይደለም፡፡ መንግሥት በአግባቡ ሕዝብን ማስተዳደር ሲያቅተው፣ ፍትሕ ሲጓደል፣ ሙስና እንደ ሰደድ እሳት አገር ሲለበልብ ውጤቱ ቀውስ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው አመፅ አንድ ማሳያ መሆን አለበት፡፡ ፀረ ሰላም ኃይሎች የሚባሉም ሆኑ ሌሎች ከአመፁ ጀርባ እጃቸውን ቢከቱ እንኳን፣ በአገር ውስጥ ያሉ እጃቸው ንፁኅ ያልሆነና ሕዝብ ሲያስመርሩ የነበሩ ኃይሎች ጭምር አሉበት፡፡ የሕዝቡን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ወደማይፈለግ አቅጣጫ በመንዳት ለሰው ሕይወት ማለፍ፣ ለአካል መጉደልና ለንብረት ውድመት የዳረጉ አሉ፡፡ ይህንን ለመካድ መሞከር በራስ ላይ መቀለድ ነው፡፡ ሕዝብ ምሬቱ ከመጠን በላይ ሆኖ ክትሩን ሲጥስ ከሚፈጥረው ጫና በተጨማሪ፣ የእነዚህ ወገኖች አሉታዊ ሚናም ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህንስ ማን ነው የሚያቆመው?

ተወደደም ተጠላም ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተሻለ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ አገሪቱ ሁሉንም ዓይነት አመለካከቶች የምታስተናግድ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያ መብቶች የሚከበሩባት፣ ከአንድ ወገን ወይም ጎራ ጥቅም ይልቅ የሕዝብ የሚቀድምባት፣ ልዩነቶች በነፃነት የሚንፀባረቁባት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በተግባር የሚከበርባት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ተግባራዊ የሚደረግባት፣ ሕግ የሚከበርባት፣ ሕገወጦች አደብ የሚገዙባት፣ የሥልጣን ባለቤት የሆነው ሕዝብ የሚከበርባት፣ ወዘተ መሆን አለባት፡፡ እነዚህ ሁሉ ለአገር ህልውና የሚጠቅሙ ተግባራት በተግባር ሲረጋገጡ ሰላም ይሰፍናል፡፡ መረጋጋት አስተማማኝ ይሆናል፡፡

ሁሌም እንደምንለው የሕግ የበላይነት መከበር አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር ተጠያቂነት አለ፡፡ ተጠያቂነት ከሌለ ደግሞ ሕገወጥነት ይሰፍናል፡፡ ሕገወጥነት ባለበት መልካም አስተዳደር አይኖርም፡፡ ፍትሕ አይሰፍንም፡፡ ሙስና ሕዝብ ላይ ይፈነጫል፡፡ የሕግ የበላይነት እንዲኖር ግን ሕገ መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ መከበር አለበት፡፡ የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ዋስትና ያገኙት በሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ትልቁ ኃላፊነት ያለው ደግሞ መንግሥት ላይ ነው፡፡ መንግሥት ሥልጣኑን ብቻ ለማስከበር የሚሯሯጥ ከሆነ፣ በየሥርቻው ያሉ የሹም ዶሮዎች ሕዝቡን ያስመርራሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ለአገር ሰላምና መረጋጋት ጠንቅ ይሆናሉ፡፡ መንግሥት አሠራሩን ግልጽ ያድርግ፡፡ ተጠያቂነት እንዳለበትም ይወቅ፡፡ ከዲስኩር ወጥቶ ተግባራዊ ይሁን፡፡ የሚከሰሱትን ይክሰስ፣ የሚቀጡትን ያስቀጣ፣ ቁርጠኛ ይሁን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...