Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያጋጠሙትን ማነቆዎች ለፓርላማው አሳወቀ

ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያጋጠሙትን ማነቆዎች ለፓርላማው አሳወቀ

ቀን:

  • ክልሎች መሬት የማዘጋጀትና መረጃ የመስጠት ችግር አለባቸው አለ
  • የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ፈቃድ ኪራይ መሰብሰብ ላይ መሰማራታቸውን ገለጸ
  • የመንግሥት ባንኮች ብድር የማቅረብ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ አይደሉም አለ

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኮሚሽን ደረጃ ተዋቅሮ ኃላፊነቱን ለመወጣት እያደረገ ባለው ዘርፈ ብዙ ተግባሮች ውስጥ የገጠሙትን ማነቆዎች፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ በሚባል ስያሜ ተደራጅቶ የነበረውና በ2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተብሎ የተዋቀረው ተቋም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሚመራውም በቦርድ እንዲሆንና የቦርዱ ሰብሳቢም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ከተደረገ ከ2007 ዓ.ም. በኋላ፣ ሰኞ ጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ዘርፉን በመምራት ረገድ የገጠሙትን ማነቆዎች ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ግልጽ አድርጓል፡፡

የኢንቨስትመንት ቦርዱ ሰብሳቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በአባልነት ያካተተና የኢንቨስትመንት ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ አካል ቢሆንም፣ በተለያዩ አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች በመጠመድ በመደበኛነት መገናኘት ባለመቻሉ በርካታ የቦርዱን ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮች ውሳኔ ማግኘት ሳይችሉ መቆየታቸውን፣ የኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍፁም አረጋ ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በኮሚሽኑ በኩል አሉ ያሏቸውን ድክመቶችም ለቋሚ ኮሚቴው የገለጹ ሲሆን፣ ባለሀብቶች ለሚያቀርቧቸው የመሬትና የኤሌክትሪክ ኃይል ጥያቄ አፋጣኝ መፍትሔ ማስገኘት አለመቻል፣ ባለሀብቶችን ሊደግፍ የሚችል ፈጣን የፍርድ ሥርዓት ወይም የግልግል ዳኝነት በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲመሠረት ክትትል አለማድረግ፣ ወደ ተግባር ያልገቡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እንዲሰረዙና ከመንግሥት ያገኙትን ማበረታቻዎች እንዲመልሱ አለማድረግ የተወሰኑት ናቸው፡፡

ኢንቨስትመንትን በሚፈለገው ሁኔታ ለማስፋፋት ተገቢ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ማለትም የመሬት የፋይናንስና የመሳሰሉት ተቀናጅተው መቅረብ ያሉባቸው ቢሆንም፣ የመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ተገቢ ምላሽ ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ የተደራጁ አለመሆናቸው ተገልጿል፡፡ የመሬት አስተዳደር አካላት ለማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሬት በማዘጋጀት ላይ አለመሆናቸውንና መረጃ ለመስጠትም ፈቃደኛ ሆነው አለመገኘታቸውን አቶ ፍፁም ገልጸዋል፡፡

የዚህ ምክንያቱ ካሳ ለመክፈልና ለማልማት በቂ በጀት በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ስለማይመደብላቸው ወይም ተከታትለው ስለማያስመድቡ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ለኢንቨስትመንት ተዘጋጅቷል የተባለ መሬት ካሳ አልተከፈለበትም፣ ማሳው አልተነሳም፣ የፍርድ ቤት ክርክር አለበት፣ ለሌላ ሥራ ተፈልጓል፣ ወዘተ በሚሉ ሰበቦች ለረጅም ጊዜ ልማት ላይ ሳይውል እንደሚቆይ ገልጸዋል፡፡

የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ዳያስፖራውን ጨምሮ ብዙም እሴት በማይጨምሩና ከፍተኛ ትርፍ በሚያስገኙ በአገልግሎት ዘርፎች ማለትም በመሣሪያዎች ኪራይ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በተለይም በሪል ስቴት፣ በንግድና በመሳሰሉት ዘርፎች ላይ መሰማራትን እንደቀጠሉበት ጠቁመዋል፡፡ እነዚህም ዘርፎች ሕግን ተከትሎ ከመሥራት ይልቅ የቀረጥ ነፃ መብቶችን ከዓላማው ውጪ መጠቀም ላይ እንደሚያተኩሩ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ለአንድ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት የወሰዱትን ብድር ላልተገባ ዓላማ ማዋል፣ ለልማት የተወሰደን መሬት ለረጅም ጊዜ አጥሮ ማቆየት በሚል ማታለል ማበረታቻዎችን እንደሚወስዱ ጠቁመዋል፡፡

አንዳንድ የውጭ ባለሀብቶች ክፍተቶችን በመጠቀም ሰፋፊ የግብርና መሬቶችን ይዞ ወደ ልማት አለመግባትና ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች በተከለሉ የሥራ መስኮች ለምሳሌ በብሎኬት ምርት ላይ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ብድር አቅራቢ ተቋማትን በተመለከተ መንግሥት የመረጣቸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢንቨስትመንት ዴስኮችን በኮሚሽኑ ሕንፃ ውስጥ አቋቁመው ለባለሀብቶች አገልግሎት መስጠት ጀምረናል ቢሉም፣ ከብድር አንፃር ምንም ውጤት አለማሳየታቸውን አቶ ፍፁም አስረድተዋል፡፡

‹‹በተለይ ለባለሀብቶች የካፒታል ብድር እንደሚያቀርብ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለአንድ የውጭ ባለሀብት ብቻ ብድር መስጠቱ ሲታይ ባንኩ ከአሥር ያላነሱ ሠራተኞችን በኮሚሽኑ ሕንፃ ውስጥ መድቦ የኢንቨስትመንት ዴስክ የማቋቋሙን ፋይዳ ጥያቄ ውስጥ እንደከተተው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በ2008 በጀት ዓመት ኮሚሽኑ የለያቸውን ችግሮች በማስተካከል፣ ጎን ለጎንም የኢንዱስትሪ ፓርክ ደንብን፣ የኢንዱስትሪ ፓርክና የኢንቨስትመንት መመርያዎችንና ማንዋሎችን ፈጥኖ ሥራ ላይ ለማዋል ማቀዱን ገልጸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ባለሥልጣኑ መለየቱን ያደነቀ ቢሆንም፣ የተለዩትን ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የተሄደበት ፍጥነት አዝጋሚ መሆኑን በመጠቆም በፍጥነት ወደ መፍትሔ እንዲገባ መመርያ ሰጥቷል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...