Friday, March 1, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ራሱን ይፈትሽ

በዋቅቶሌ ኦልቀባ

የዛሬ ሁለት ሳምንት በወጣው የሪፖርተር ጋዜጣ የቆይታ ዓምድ ላይ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ መነሻ በማድረግ የሚከተሉትን አስተያየቶች ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በአገራችን ቀደምትና በአገራችን አሉ ከሚባሉ በጥሩ መሠረት ላይ ከቆሙ ተቋማት አንዱ ነው፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት አገሪቱ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ የምታከናውነውን የመንገድና የድልድይ ዘርፍ በበላይነት የሚመራ አካልም ነው፡፡ እንደ ትኩረት አቅጣጫውም ብዙ መዋዕለ ንዋይ ወጥቶበታል፡፡ ባለሥልጣኑም ይህንን ተግባሩን በሚገባ ለማረጋገጥ ራሱን በሚገባ ማደራጀትና ጠንካራ ቴክኒካዊ የቁጥጥር ሥልቶችን በመቀየስ፣ በባለድርሻ አካላት ላይ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ከላይ በአጭሩ የተገለጸውን ተግባራዊ ለማድረግም በአብዛኛው በቃለ ምልልሱ እንደተካተተው የጨረታ ሒደቶች፣ የዲዛይንና የግንባታ ጥራቶች፣ የተቋራጮችና የአማካሪ መሐንዲሶች ድክመቶችና ገንቢ ጎኖች መፈተሽና መመርመር አለባቸው፡፡ በእነኚህ መሠረታዊ ነጥቦች በዝርዝር እንደ ተጨማሪም ባለሥልጣኑ የራሱን ተቋም፣ አደረጃጀት፣ የሠራተኞቹን የሙያ ክህሎትና ሥነ ምግባር በቅጡ መፈተሽ አለብን፡፡

በግንባታ ዘርፉ ተሳታፊ የሆኑት የውጭ በተለይ የቻይናና ጥቂት የማይባሉ የአገር ውስጥ ተቋራጮች ናቸው፡፡ እነኚህ ኩባንያዎች በአብዛኛው ተደራራቢ ፕሮጀክቶችን ያከናውናሉ፡፡ ከጥቂቶቹም በስተቀር በአብዛኛው ግንባታውን የሚያጠናቅቁት ባለሥልጣኑ ከሰጠው ጊዜ ውጪ እጅግ በተራዘመ ጊዜ ነው፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚቀርበው የወሰን ማስከበር ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ችግር እንዳለ እንኳን ሆኖ በተወሰነ የፕሮጀክቱ አካባቢ ላይ ያለ ችግር ሙሉ ግንባታው እንዲጓተት ያደርጋል፡፡ በአብዛኛው እነኚህ ተቋራጮች አደረጃጀታቸው (በሥራ አመራር፣ በሰው ኃይል በመሣሪያና በመሳሰሉት) የፋይናንስ አጠቃቀማቸው እጅግ የተዳከመ ሲሆን፣ ለሥራው የተመረጡበት መሥፈርት ራሱ አጠያያቂ ነው፡፡ በእነዚህ ላይ ባለሥልጣኑ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ፣ እንዲሁም ለወደፊቱ የጨረታ መሥፈርቱን መከለስ ይገባዋል፡፡ የግንባታ መጓተት መንገዱ ለሚፈለገው ዓላማ በሚፈለገው ጊዜ እንዳይደርስ ከማድረጉም በላይ፣ አገሪቱን እጅግ ለከፍተኛ ወጪ ይዳርጋታል፡፡

ሌላው የግንባታው ዘርፍ ባለድርሻ የሆኑት አማካሪ መሐንዲሶች ናቸው፡፡ እነኚህ አካላት ከዲዛይን እስከ ግንባታ ድረስ የራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ ከእነኚህም አማካሪዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ድርሻቸውን በአግባቡ መወጣት የተሳናቸውና ኃላፊነት የጐደላቸው ናቸው፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ ባለፉት ዓመታት ባለሙያ የሠራቸው መሆናቸው እስከሚያጠራጥሩ ድረስ ከፍተኛ ግድፈቶች ታይተዋል፡፡ በከተሞች በሚያቋርጡ አውራ ጐዳናዎች ትልልቅ የቆረጣ ሥራዎች እንዲካሄዱ ዲዛይን ከማድረግ እስከ ትልልቅ ድልድዮችን አለማካተት ድረስ ይዘልቃል፡፡

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በተቋማቱ ብቁ ባለሙያ አለመኖር፣ በድርጅቶቹ በክፍያና በጥቅማ ጥቅም ምክንያት ባለሙያዎችን ለመያዝ አለመፍቀድ፣ ወደ መስክ የሚሰማሩ ባለሙያዎችን በዲዛይን ወቅት ሳይቱን በሚገባ ተንቀሳቅሶ ከማየት ይልቅ በአቅራቢያው በሚገኝ ከተማ በመቀመጥ፣ በመለስተኛ ደረጃ ባለሙያዎችና ሌሎች በሙያ ውስጥ የሌሎች ሰዎች ወደ መስክ በመላክ የመረጃና ሌሎች ግብዓቶችን ማሠራቱ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡

በተጨማሪም በዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ በመስክ ግንባታና ቁጥጥር ወቅት የባለሙያዎች በመስክ ሥራ ላይ አለመገኘት የተጠቀሰው ትክክል ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ የባሥልጣኑ የክትትል መላላትም አስተዋጽኦ አለበት፡፡ ለዚህ እንደ አብነት ለመጥቀስ ራሱ ባለሥልጣኑ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በሚያካሂደው የማስተርስ ፕሮግራም ተሳታፊ የሆኑ ተማሪ መሐንዲሶች አዲስ አበባ ቁጭ ብለው እየተማሩ፣ በየወሩ በስማቸው ወርኃዊ የክንውንና የክፍያ ማረጋገጫ እየተፈረመ ሲቀርብ ዝም ብሎ ይረከባል፡፡

ሌላውና መጠቀስ ያለበት አንኳር ነጥብ ደግሞ እነዚህ አማካሪ መሐንዲሶች ወደ ሥራው የሚያሰማሩዋቸው ልምድና ዕውቀት የሌላቸው ባለሙያዎችን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚመነጨው እነዚህ ባለሙያዎች በሚጠይቁት ዝቅተኛ ክፍያና ጥቅማ ጥቅም ምክንያት ነው፡፡ ይህ መሠረታዊ ነጥብ ደግሞ በብዙዎቹ ፕሮጀክቶች ለሚታየው የጥራት ችግር መሠረታዊ መነሻ ነው፡፡ የአማካሪ መሐንዲሶች ባለሙያዎቹ ዕውቀትና ክህሎት ማነስ የሚፈጥረው በራስ መተማመን ማጣት፣ ዲዛይንና ስፔሲፊኬሽኖችን አለመረዳት፣ በየወቅቱ በሥራ ላይ ለሚፈጠሩ ድንገቴዎች መፍትሔ መስጠት አለመቻልና የመሳሰሉት ለጥራቱ መውረድ መንገድ ይከፍታሉ፡፡

የሌሎቹን ባለድርሻዎችና የባለሥልጣኑን ሠራተኞች ደግሞ በአጭሩ እንመልከት፡፡ ባለሥልጣኑ ለፕሮጀክቶች በቀጥታ የሚመድባቸው ባለሙያዎች አሉ፡፡ እነዚህ በአብዛኛው ተቀማጭነታቸው በዋናው መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ከእነዚህም ጥቂት የማይባሉ ከተቋራጮች ጋር በመመሳጠር የባለሥልጣኑን ሥራ ከማከናወን ይልቅ በሥራ ተቋራጩ የጉዳይ አስፈጻሚነት ሚና ይጫወታሉ፡፡ ለዚሁም ደግሞ ከወርኃዊ ደመወዝ እስከ ልዩ ጥቅማ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ ይህም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

ባለሥልጣኑ የሠራተኞቹን ሥነ ምግባር በደንብ ይፈትሽ፡፡ ባለፉት ዓመታት ከባለሥልጣኑ ዝቅተኛ ሠራተኞች እስከ አንዳንድ የኮንትራት አስተዳደር መሐንዲሶች ድረስ ዛሬ የከተማችን ቱጃር ሆነዋል፡፡ ሕዝብ ከየት መጣ እያለ ይጠይቃል፡፡ በእነዚህ ጥቂት ዓመታት እነዚህ ሰዎች የሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ባለቤት፣ የትልልቅ ሆቴሎች ባለቤትና ትልልቅ ኮንትራክተሮች፣ የመሣሪያ አከራዮች፣ ወዘተ. ሆነዋል፡፡ ጓደኞቻቸው እዚያው አሉ፡፡ ይህ ሁሉ በመንግሥት ደመወዝ ነው? ይህ የሚያገባው ካለ ያጣራ፡፡ የከተማው ወሬ ነው፡፡ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ መንግሥትም ለራሱ ሲል የማጣራት ኃላፊነት አለበት!!

ከላይ በጥቂቱ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ዘርፉ በበርካታ ችግሮች ተተብትቧል፡፡ ይህንንም ለመበጣጠስ ብዙ መሥራትና ቆራጥነት ከባለሥልጣኑና ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡      

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Previous article
Next article
spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles