Saturday, February 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የመዋቅር ማሻሻያ ሊያደርግ ነው

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የመዋቅር ማሻሻያ ሊያደርግ ነው

ቀን:

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ኃላፊነቱን በሚፈለገው ደረጃ እንዳይወጣ ማነቆ የሆነበትን ነባሩን የመዋቅር ክፍተት የሚያሻሽል፣ በአንፃሩ ደግሞ አኅጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታዎች ያገናዘበ አዲስ መዋቅር ለመዘርጋት የመነሻ ጥናት አካሄደ፡፡ የውጭ አገሮችን ልምድና ተሞክሮ ባካተተ መልኩ የቀረበው የመነሻ ጥናት ጉዳዩ በሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ታይቶ በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አቶ ታረቀኝ ገረሱ የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ እንደገለጹት፣ የኤጀንሲው ከፍተኛ አመራሮችን፣ የሥራ ክፍል ኃላፊዎችን፣ የዕውቅና አሰጣጥና የጥራት ኦዲት ከፍተኛ ባለሙያዎችን ጨምሮ በዘጠኝ አባላት በተዋቀረው ኮሚቴ የተዘጋጀው ይኸው የመነሻ ጥናት ባካተተው አዲስ መዋቅር፣ ከአሁን በፊት የሌሉ አዳዲስ የሥራ ክፍሎች ይፈጠራሉ፡፡ ክፍተት የታየበት ነባሩ መዋቅር የሚሻሻልበትን የመፍትሔ አቅጣጫም አስቀምጧል፡፡

አዲሱ መዋቅር ከሚያቅፋቸው አዳዲስ የሥራ ክፍሎች መካከል የጥናትና ምርምር፤ እንዲሁም አቅም ማጎልበትና ክትትል ሥራን የሚያከናውኑ ክፍሎች ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህም መካከል የጥናትና ምርምር ክፍል አገሪቱ ከተያያዘችው የቴክኖሎጂ ሽግግር አኳያና የልማት አቅጣጫ አንፃር በቂ ዕውቀት፣ ክህሎትና ልምዱ ባላቸው ተመራማሪዎች ይመራል፡፡

የአቅም ማጎልበትና ክትትል ሥራን የሚያከናውነው ሌላው ክፍል ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነትን መከታተል ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ የአቅም ግንባታ ሥራውን ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚያከናውነውም አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ልምዶችን ባገናዘበና በዳሰሰ ሁኔታ ላይ ትኩረት ያደረገ መደበኛ ሥልጠናዎችን በመስጠት ይሆናል፡፡

አስፈላጊ በሆኑ የክልል ከተሞች ክትትልና ድጋፍ ለመስጠት የሚችሉና ተጠሪነታቸው ለኤጀንሲው የሆኑ ማዕከላትን ማቋቋም በአዲሱ መዋቅር ከተካተቱት የሥራ ክፍሎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የዕውቅና ፈቃድ እየተሰጣቸው ያሉ ተቋማት ብዛት ካምፓሶቻቸውን ወይም ቅርንጫፎቻቸውን ሳይጨምር በተቋም ደረጃ ከ100 በላይ ደርሷል፡፡ እነዚህን ተቋማት አዲስ አበባ ብቻ በተቋቋመው የኤጀንሲው አንድ ማዕከል ሲከታተል የቆየ ቢሆንም፣ የሚፈጠሩ ችግሮችን በሚፈለገው ደረጃ ሊቀርፍ አልቻለም፡፡

በተለይ የዕውቅና ፈቃድና የዕውቅና ፈቃድ ዕድሳት ሳይሰጣቸው የቅበላ መስፈርት መመሪያን ሳያከብሩና ተያያዥ የሕግ ጥሰት እየፈጸሙ ተማሪ ተቀብለው በማስተማር በኅብረተሰቡና በትምህርት ጥራቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ተቋማትን ለመቆጣጠርም ሆነ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ለመስጠት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በመሆኑም ቅርንጫፍ ማቋቋም እንደ አንድ መፍትሔ ተቀምጧል፡፡

አሁን ባለው የኤጀንሲው አደረጃጀት፣ የሙያ ስብጥርን ያካተተ የሰው ኃይል ባለመኖሩ የሥራ ክፍሎች ተደራራቢ ሥራዎችን በአንድ ላይ እንዲሠሩ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ሥራ ማከናወን አልተቻለም፡፡ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ጥናቱ ካስቀመጣቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች መካከል የሰው ኃይሉን በሚገባ ማደራጀትና መጠናከር ይገኝበታል፡፡ ባለሙያውንም ለማቆየት የተሻለ የደመወዝ ክፍያና ጥቅማ ጥቅም የሚገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት የመፍትሔ አቅጣጫዎች አካል ናቸው፡፡

በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚገነቡ 11 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ 44 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችንና 100 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከአገሪቱ የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ብዛት አንፃር፣ ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዕድገት ጋር ሲታይ በሰው ኃይልና በመዋቅር ውስንነት ምክንያት ኤጀንሲው ያልደረሰባቸው በርካታ ተግባራት መኖራቸውን የጥናቱ ግኝት ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከህወሓት የሰላም ስምምነት ኮሚቴ አባላት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኙ

የፌዴራል መንግሥትና የህወሓት የሰላም ስምምነት ኮሚቴ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር...

ማስተካከያ

በሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ዕትም...

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...