Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአገልጋይነት ያለተጠያቂነት

አገልጋይነት ያለተጠያቂነት

ቀን:

ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ቦሌ ድልድይ አካባብ ከሚገኝ የተፈጥሮ አበባ መሸጫ መደብር ጎራ ብሎ የታዘበውን ያካፈለን አቶ መላኩ ብርሃኑ በአንድ የግል ኩባንያ ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ነው፡፡ አጋጣሚውን እንዲህ ያስታውሳል፡፡ ከቢሯቸው ለሚካሄድ ዝግጅት አበባ ለመግዛት በማሰብ ለመጠየቅ ከመደብሩ ጎራ አለ፡፡ ሁለት ሰዎች ከመደብሩ ደጃፍ ቆመዋል፡፡ እንደ እሱ ገዢዎች እንደሆኑ ይገምታል፡፡ አንደኛው የመደብሩ አስተናጋጅ ደግሞ አጎንብሶ በስልኩ ተጠምዷል፡፡ ‹‹ነገ በጠዋት ትከፍታላችሁ ወይ?›› የሚለውን የአቶ መላኩን ጥያቄ ከቀልቡ ሆኖ ስላልሰማው ጥያቄውን ለመድገም ተገደደ፡፡ ለጥያቄው፣ የእሱን አገልግሎት ፈልጎ ለሄደው ሰውም ትኩረት ሳይሰጥ ዘግየት ብሎ በጠዋት እንደማይከፍቱ መልስ ሰጠ፡፡ ይህ የቅርብ አጋጣሚው በመሆኑ እንጂ ከታች ጀምሮ በተለያዩ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት አገልግሎት ሽተው ሲሄዱ ዘወትር የሚስተዋል የአገልጋዮች አቀራረብ እንደሆነ አቶ መላኩ ይናገራል፡፡

‹‹ሠራተኞች ቦታ የያዙት ለምን እንደሆነ የሚረዱት አይመስለኝም፡፡ የትም ይኬድ የት የሚታየው ነገር አገልግሎት መስጠት የሚባለው አልገባንም ያሰኛል›› ይላል በሥራም በግል ጉዳይም በመንግሥት በግልም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከታዘበው በመነሳት አገልጋዩ ሥራው የሚጥልበትን ግዴታ የዘነጋ፣ በሚሰጠው አገልግሎት ማለትም ሥራውን በማከናወኑ መመስገን የሚሻ እንዲሁም የተቀመጠበትና የያዘውን ቦታ እንደ ሥልጣን የሚመለከት ነው ሲል ይደመድማል፡፡

አቶ መላኩ ብቻም ሳይሆን አስተያየት የጠየቅናቸው ሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ ነገር ያጋጠማቸው ናቸው፡፡ በተወሰነ መልኩ ከአገልጋይ አቀራረብና አመለካከት አንፃር በግሉ ዘርፍ የተሻለ ነገር ቢኖርም በጥቅሉ ግን ሆስፒታል (የግልም የመንግሥት)፣ ፖሊስ ጣቢያ፣ እንደ አሌክትሪክ ኃይልና ገቢዎች ካሉ ቢሮዎች ሲኬድ የሚስተዋለው ተስተናጋጁ (አገልግሎት ፈላጊው) ላይ አዛዥ አለቃ የመሆን አመለካከት እንደሆነ ብዙዎች ገልጸውልናል፡፡

በሌላ በኩል የአገልጋዮች አቀራረብ እንደየ ስብዕናቸው እንደሚለያይ አንዳንዶቹ ሥራቸው የጣለባቸውን ኃላፊነት ጠንቅቀው የሚያውቁና በተገቢው መንገድ የሚያስተናግዱ ሲሆኑ፣ ለማመን በሚከብድ መልኩ ቅንጣት ታህል እንኳ የአገልጋይነት መንፈስ የሌላቸውና ግዴታቸውን መወጣት የማይፈልጉ እንዳሉ የምትናገረው ወይዘሪት ፀጋ አሰፋ በአንድ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ነች፡፡ ‹‹ሰው ቆሞ እየጠበቃቸው እነሱ የግል ጉዳያቸውን ይዘው ይቅርታ ጠብቁኝ እንኳ የማይሉ ብዙዎች ናቸው›› ትላለች፡፡

‹‹ቢሆንም ግን ባንክም ይኬድ ሆስፒታል አቀራረቡን ማሳመር ቀድሞ ሰላምታ መስጠት የሚጠበቅበት አገልግሎት ፈላጊው ነው፤›› ትላለች፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ የተለያዩ ችግሮች ተነቅሰው እየወጡ የአገልጋዮች አቀራረብና አመለካከት ላይ ሁልጊዜም የሚታየው ይህ ትልቅ ጉድለት ለምን ትኩረት እንደማይሰጠው ጥያቄ ታነሳለች፡፡

አገልግሎት ፈልገው ወደ ተቋሞቻቸው የሚሄዱን ተገልጋይ ወይም ደንበኛም ብለው ይጥሯቸው ለእነዚህ ሰዎች ጥሩ አቀራረብ ማድረግ ትርፍ ዋነኛ ትኩረታቸው ለሆነ የግል ኩባንያዎች፤ ከሕዝብ የሚሰበሰብ ግብር የጀርባ አጥንታቸው ለሆነ የመንግሥት ተቋማት ወሳኝ መሆኑ አከራካሪ አይሆንም፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተሠሩ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም የአገልጋይ አቀራረብና አመለካከት ከምንም በላይ ዋጋ ሊኖረው ሁሉ ይችላል፡፡

ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደገለጹት ግን መሬት ላይ ያለው ነገር ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ ዜጎችን መጠበቅ ከችግር መከላከል የሚጠበቅበት ፖሊስ በዜጎች ላይ ራሱን የሾመ አለቃ፣ የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ የቆመው ትራፊክም እንዲሁ ራሱን በአሽከርካሪዎች ላይ የሾመ አዛዥ ነው፡፡ እንደ ሆስፒታል ባሉ ሌሎች የሕዝብ አገልግሎቶች በሚሰጡባቸው ተቋማት ያሉ አገልጋዮችም አገልግሎት የሚሰጡት በመልካም ፍቃዳቸው እንጂ የያዙት ቦታ ኃላፊነት ስለሚጥልባቸው መሆኑን የዘነጉ የረሱም ጭምር መሆናቸው ላይ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

ይህ ችግር ዕለት በዕለት ብዙዎች የሚያልፉበት በመሆኑ ነገሩን ተላምደውት ቅሬታ ከማቅረብና እንደ ችግር መፍትሔ ያሻዋል ብሎ ከማመን ይልቅ ለራሳቸው የሚሆንና የራሳቸውን ጉዳይ ለማስፈጸም የሚረዳ አካሄድ መዘየድን እንደመረጡ የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም፡፡ ይህም በጥቅሉ አቀራረብን ማሳመር ሲሆን በፈገግታ ጥሩ ሰላምታ መስጠት የኔ ጌታ የእኔ እመቤት ማለትን ይጨምራል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶሲዮሎጂ ዲፓርትመንት መምህር የሆኑት ዶ/ር የራስ ወርቅ አድማሴ እንደሚሉት አገልጋይ አዛዥ፤ ተገልጋይን ማጉላላት ልማድ በሆነበት የተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት አሳስቆና አጎብድዶ ጉዳይን መጨረስ የተለመደ ሆኗል፡፡ ‹‹በተገቢው መንገድ አገልግሎት ማግኘት መብቴ ነው የሚለው ሳይሆን ፈገግታና አክብሮት አሳይተን ጉዳያችንን ቶሎ ማስፈጸምን ነው የምንመርጠው›› የሚሉት ዶ/ር የራስ ወርቅ አገልግሎት ሰጪውም ሌላ ቦታ እንዲሁ የሚያደርግ እሳቸው እንደሚሉት (የሚሽመደመድ) እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል መብታቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁና በአገልጋዮች ችግር እንደሚገባን አልተስተናገድንም ጉዳያችን አልተፈጸመም ሲሉ መሄድ የሚገባቸው ድረስ ሄደው አቤቱታቸውን የሚያቀርቡም አጋጥመውናል፡፡

መካኒሳ አካባቢ በሚገኝ ኮንዶሚኒየም ሳይት ተከራይቶ የሚኖር ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነው፡፡ በአንድ ወቅት የመቶ ብር የመብራት ካርድ ቢሞላም በቆጣሪ ችግር ለቀናት ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል መቆየታቸውን ያስታውሳል፡፡ ጉዳዩ ወደሚመለከተው ጣቢያ በመሄድ ችግሩን ለማመልከት ከቢሮ ወደ ቢሮ እያለ የተለያዩ ባለሙያዎችን ቢያናግርም ችግሩን በቅጡ የሚሰማው ሊያገኝ አልቻለም፡፡ አንዳንዶች ጉዳዩን ለመስማት ጊዜ ወይም ፍላጎት አልነበራቸውም፣ ሌሎች ደግሞ የእነሱ ኃላፊነት አለመሆኑን ገልጸው ወደ ሌላ መርተውታል (በቂ መረጃ ሳይሰጡ)፡፡

ሰባት ቀናት በዚህ ሁኔታ አለፉ፡፡ በዚህ ወቅት ገንዘብ ከፍሎ አገልግሎት ማግኘት አለመቻሉ የእሱ ሳይሆን አገልግሎቱን የመስጠት ኃላፊነት ያለበት አካል ችግር መሆኑን ገልጾ በዚህ ደግሞ የሚመለከተው የበላይ አካል ድረስ እንደሚሄድ ደጅ ይጠናቸው ለነበሩት የጣቢያው ባለሙያዎች አስታወቀ፡፡ ይህ የሆነው ጠዋት ላይ ሲሆን አቤቱታ ሲያስመዘግብ በተወው አድራሻ መሠረት የጣቢያው ባለሙያዎች በዚያው ዕለት ከሰዓት በኋላ ከቤቱ በመሄድ የቆጣሪውን ችግር ሊፈቱለት ችለዋል፡፡ ከቤት የነበረችው ባለቤቱ ስትሆን ከባለሙያዎቹ አንዱ ባለቤቷ ባለሥልጣን መሆኑን መጠየቁን ያስታውሳል፡፡ ይህ የሚያሳየው ከብዙ ውትወታ በኋላ እንኳ አገልጋዮች ተገልጋዩን ለማስተናገድ ሲወስኑ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሳይሆን የራሳቸውን ሌላ ስሌት ሠርተው ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡

እሱም ከዚህ አጋጣሚው በመነሳት የአገልጋዮች በአግባቡ ሰውን አለማስተናገድ ኃላፊነታቸውን ያለመወጣት ነገር እንዳለ ሆኖ የተገልጋዮችን አለባበስ፣ ጾታ፣ ዜግነት ወይም ሌሎች ግምቶችን በመውሰድ አንዱን የመስማትና ቅድሚያ የመስጠት ሌላውን የማጉላላት ነገር መኖሩን እንዳስተዋለ ይናገራል፡፡ ያነጋገርናቸው ሌሎችም የእሱን ሐሳብ የሚጋሩ ሲሆን በአገልግሎት አሰጣጥ የአገልጋዮች የበላይ መሆን ለመድሎ፣ ለሙስናም ጭምር መደላድል የፈጠረ መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡

በተገልጋዩ ኅብረተሰብ በኩል የሚታየው መብቱን ያለማወቅ ይልቁንም የጉዳዩ በፍጥነት ማለቅን እንደ ልዩ ነገርና በአገልጋዩ ቅንነት የሆነ አድርጎ መመልከት እንደሆነ፤ ይህም ለችግሩ ስር መስደድ አንደኛው ምክንያት መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይስማማሉ፡፡ አቶ መላኩ ደግሞ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአሠራር ሥርዓት ክፍተትን በቀዳሚ ምክንያትነት ያስቀምጣል፡፡ ዶ/ር የራስ ወርቅም የአቶ መላኩን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ተጠያቂነትን ማስፈን ያልቻለ የተቋማት አሠራር ለሥራዎች አለመከወን፣ ለተገልጋዮች መጉላላት ለአድልዎና ለሙስና በር ከፍቷል ይላሉ፡፡ ‹‹ብዙ ሰው ይቀጠራል ሥራ ግን አይሠራም ተጠያቂነትም የለም›› የሚሉት ዶ/ር የራስ ወርቅ ቀደም ባሉት ዓመታት በግሉ የአገልግሎት ዘርፍ ጥሩ ነገር የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ነገሮች ተወራርሰው የከተማ የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ አገልጋዮች የበላይና አዛዥ የሆኑበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህ ከታች እስከ ላይ የሚስተዋል እንደሆነም ያስረግጣሉ፡፡ እዚህ ድምዳሜ ላይ ካደረሷቸው በልብስ መደብር፣ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ በሚመለከተው ተቋም፣ ባንክና ሌሎችም ተቋማት በተለያየ ጊዜ ያስተዋሏቸው ነገሮች ናቸው፡፡

ቀደም ሲል በመንግሥት ተቋማት መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ መደረግን ተከትሎ ሠራተኞች ከደረታቸው ላይ ስማቸው እንዲኖር መደረጉን ያስታወሱት ዶ/ር የራስ ወርቅ ዛሬ ከዚህ ጀምሮ ብዙ ነገሮች ችላ እየተባሉ እየተተው መሆኑ ነገሮችን ይበልጥ ወደ ኋላ መመለሱን ያስረዳሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የሥራ ሒደት ለውጡ ፈጥሮት የነበው የተወሰነ መነሳሳት ዛሬ ጠፍቷል፡፡ ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት፣ ሥነ ሥርዓት አለማክበርም በሠራተኞች እንደ ችግር የማይታይበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል፡፡

በሌላ በኩል የመንግሥት ተቋማት የሥራ አፈጻጸም ዕቅድ ራሱ ለአገልግሎት ጥራት ትኩረት የሚሰጥ አለመሆኑን አቶ መላኩ ይገልጻል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል ገንዘብ እንሰበስባለን ወይም ይህን ያህል ሰው እናስተናግዳለን የሚለውን የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዕቅድ ተገልጋዩ በሚከፍለው ዋጋ የሚፈጸም እንደሆነ አድርጎ ነው የሚመለከተው፡፡ ሰዎች መብታቸውን ለማስከበር መሄድ የሚገባቸው ድረስ ይሂዱ እንዳይባል የተቋማቱ አሠራር ይህንንም የሚያበረታታ አይደለም ብሎ ያምናል፡፡ ‹‹የተጣለብኝ ግብር መጠን አግባብ አይደለም ብዬ ብል አቤት ለማለት መጀመሪያ አንድ አራተኛውን መክፈል ያስፈልጋል፡፡ ወደ ፍርድ ቤት ልሂድ ቢባል ደግሞ ግማሹን መክፈል ያስፈልጋል›› የሚለው አቶ መላኩ ይህ መብቱን የሚያውቀውም መብቱን ለማስከበር እንዳይበረታታ እንደሚያደርግ ይገልጻል፡፡

የሥነ ምግባር ደንቦችን ከመለጠፍና ዋጋ የማይሰጣቸውን ሐሳብ መስጫ ሳጥኖች ከማኖር ይልቅ በትክክል ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችሉ አሠራሮችን በአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ውስጥ መገንባት አቶ መላኩና ዶ/ር የራስ ወርቅ እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጡት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወይዘሪት ፀጋ ለአገልጋዮች ተገልጋይን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል ትላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...