Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አንዱ በጎረሰው ሌላው ለምን ይታነቅ?

ሰላም! ሰላም! ‹‹ትንሳዔ ባይኖር ኖሮ ገና የሚባል ቀን አይኖርም ነበር፤›› ያለው ማን ነበር? የባሻዬን ልጅ ስጠይቀው ባሻዬ ሰምተው፣ ‹‹ከነገር መጀመሪያ የነገር መጨረሻ ይበልጣል’ ብሎ ሰሎሞን ጨርሶልህ ማንስ ቢለው ምን አስጨነቀህ? ወይስ ዕውቀትም እንደ ገንዘብ በመተዋወቅ ይተላለፋል ብለህ አመንክ?›› ብለው ወሽመጤን ቆረጡት። ደመወዛችን አይቆረጥ እንጂ የወሽመጡንስ ግድ የለም ለምደነዋል። ግን አንዲያው ይኼን ይኼን የጥበብ ቃል፣ ከዕድሜ ጠገብ እየሰሙ ምነው በአጀማመራቸው የሚመፃደቁብን በዙ? ብዙ ተባዙ ይኼንንም ይጨምራል እንዴ? ደግሞ ባሻዬን እንዲህ ብላቸው ‘ጥያቄ በማብዛት መልስ አይገኝም’ ብለው ይወርዱብኛል ብዬ ዝም አልኩ።  እውነቴን ነው የምላችሁ በጥያቄ ብዛት ከባቢ አየሩን መጣስ ቢቻል ኖሮ እኮ ማንም ከእኛ ቀድሞ ህዋ ለሽርሽር አይጓዝም ነበር። ጨረቃን ለመርገጥ አሜሪካ የፈጀችውን ማገዶ እኛ በጥያቄዎቻችን ቁልል በአቋራጭ ከንቱ ባደረግነው ነበር።

ዳሩ አለ የዳር አገር ሰው። ለነገሩ አሁን አሁን የመሀል አገሩም ጥግ መጣሉን እያየ ዳሩ ባይ ሆኗል። ልማታውያን ቢሰሙ ‹‹ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ›› ብለው ስለሚያልፉት እኛም ዳራችንን ከመያዝ ሌላ ትርፍ የለንም። የባሻዬ ልጅ ሰሞኑን፣ ‹‹ትርፋችን ትርፍ አንጀት ማስወጣት ሆኗል፤›› ሲለኝ ያለነገር አልነበረም። አብሮ አደጉ ያላቅሙ የፈረንጅ ምግብ ቤት ገብቶ ጠስቆ ሲያበቃ ቢል መጣለትና የ12 ወራት ደመወዙን ከፈለ። ወዳጆቹ ሰምተው፣ ‹‹ለምን አንደኛውን ፈረንጅ አገር ሄደህ የዕድሜ ልክ ደመወዝህን አትገብርም?›› እያሉ ሲያሾፉ ማታ ‘ቆረጠኝ’ ብሎ አልጋ ያዘ። ሲብስበት አንስተው ሆስፒታል ወሰዱት። ከማደንዘዣ ሲነቃ ‹‹ትርፍ አንጀት ነው። ቆርጠን አውጥተነዋል። በሰላም ሂድ…›› ቢሉት ሐኪሞቹ ምን ቢል ጥሩ ነው? ‹‹እኔንስ ቆርጣችሁ የምትጥሉኝ መቼ ነው?›› . . . ሆሆ! መጨረሻዬን ያሳምረው ማለት ቀላል ነገር መስሏችኋል?

ስለትርፍና ኪሳራ እንጫወት እስኪ። ያው ሁሌ እንደማወጋችሁ ገቢዬንና ወጪዬን በተመለከተ ማንም አያምነኝም። እኔ በእኔ ገቢና ወጪ እመኑ ትድናላችሁ አላልኩ። እስኪ ይታያችሁ! ጥሎብን ግን አለመተማመን ይቀናናል። ባሻዬ፣ ‹‹ሰው ዝም ብሎ የአምላኩን ማዳን ቢያምን ለእርሱ መልካም ነው፤›› እያሉ ቃል የሚጠቅሱት አንድም ይኼን ይኼን ሲታዘቡ ነው። ታዲያ ሰው በሰው ጉዳይ ምን አገባው? ይኼ ነው ትርክቱ። አንድም ‘የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል’ ይሏት ብሂል፣ አንድም ቅናት በዚህች በእኛዋ ምስኪን አገር ያሉ፣ የነበሩ፣ ወደፊት ግን እንዳይኖሩ የምመኛቸው ነገሮች እንቅልፍ ስለሚነሱን ነው። ‘ደላላው አንበርብር ምንተስኖት በተለይ የአባልነት መታወቂያ ካርድ ካወጣ በኋላ ገቢው ከኢኮኖሚ ዕድገቱ በሁለት አኃዝ ጨምሮ አድጓል’ ነው  አሉ የሚሉኝ። የሚሉኝ እንኳን ራሳቸውን ስለማያውቁ የት ይሁኑ እነማን እንጃላቸው።

ታዲያ ግርም የሚለኝ የዚህ የአባልነቱ ነገር ነው። በተለይ መቼ ዕለት አንድ ስካቫተር እያያሻጥኩ ሳለሁ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ባልደረባዬ የነበረ ሰው አይቶኝ፣ ‹‹እኛማ ቸርኬ የሌለው ጎማ እናሻሽጥ እንጂ። ይኼው ባለጊዜ በላያችን ላይ ሚሊዮን ይቆጥራል፤›› ብሎኝ አለፈ። ዓይን ያወጣ ፀብ ስለተጣላን ከእርሱ የምጠብቀው ነበር። ይልቅ ያልጠበቅኩት ጊዜ በምን ተዓምር ለእኔ ወግኖ መታየቱን ነው። ሳስብ ያቺ የአባልነት ሐሜት ትዝ አለችኝ። ብግን አልኩ። ‘ለምን አባል ሆኜ አንደኛውን የአበጠው አይፈነዳም?’ ብዬ ቱግ ስል ስካቫተሩን ለመግዛት በማስፈተሽ ላይ የነበረ ደንበኛዬ አስተውሎኝ፣ ‹‹ተረጋጋ እንጂ! እርግብ የዶሮ አባል ብትሆን ጭሮ መብላት ይቀርላታል? ተቧደንክ አልተቧደንክ ሠርተህ መብላትህን አትተው። ይልቅ ለአሉባልታ ጆሮ አትስጥ፤›› አለኝ። ‘እሱስ ተሰርቆም እየተበላ ነው’ ብዬ በውስጤ ቅዝቅዝ አልኩ። ሌላው በጎረሰው እኔን ለምን ይነቀኝ? አይደል እንዴ!

በዚህ እየተገረምኩ ጧት ማታ ቤቴን ቤቴን እንዳልኩ አንገት ደፍቼ መኖሬን ያዩት ደግሞ፣ ሌላ ትርፍና ኪሳራ ሊያሰሉ በአልጠበቅኩት መንገድ መጡብኝ። የዕድራችን አባል በድንገት አረፈ ተብሎ ቀብረን መጥተናል። ንፍሮ ሊያዘግነኝ መስሎ አንድ የአሉባልታ ጋዜጣ (ቀዬው ያወጣለት ስም ስለሆነ ነው የተጠቀምኩት) መጣና አጠገቤ ተቀመጠ። ‹‹ማንጠግቦሽ እንዴት ናት ለመሆኑ? ደህና ናት?›› አለኝ በጥርጣሬ እያነሳ እየጣለኝ። ‹‹ደህና ናት›› አልኩት። ደግሞ ምን ሊወራ ነው እላለሁ። ይታወቀን የለ ነገር በሰው አንጎል ሲጋገር? ዝም ብለን ነው እንጂ በጀት የምናባክነው ‘ጆሮ ጠቢ’ አያስፈልገንም እኮ ለዚህ ለዚህ። ‹‹አንበርብር እውነቴን ነው የምልህ እንዲያው አንተ ወልደህ ቢሆን ኖሮ እኔ ሌላ ሥራ አይኖረኝም ነበር። እንዲያው ነጋ ጠባ ልጅህን ስስም ብውል ደስ እንደሚለኝ? እንዲያው ለመሆኑ ማንጠግቦሽ ዝም ትላለች?›› አይለኝ መሰላችሁ ቆይቶ።

እኔ በአገሬ የወንድ ሞግዚት አይቼ አላውቅ። ሽንት ጨርቅ መቀየር ቀርቶታል ሰውዬው። ‹‹አልገባኝም?›› ስለው ኮስተር ብዬ፣ ‹‹ይኼውልህ አንበርብር ትዳር እኮ በተለያዩ የጊዜ ክፍልፋዮች የተከፋፈለ ነው። ለአፍላ ፍቅር፣ ለጫጉላ፣ ጎጆን ለማደርጀት ጊዜ አለው። አንተ እኮ ይኼው አገሬው ሁሉ በቅርቡ በስሙ ፎቅ ሠርቶ ሳያከራይ አይቀርም የሚልልህ የሳንቲም ችግር የሌለብህ ሰው ነህ። መታደል እኮ ይኼ ነው! ኧረረረረ! አይምሰልህ! መታደል ነው። ታዲያ ዘር ከሌለበት ፍቅርም እኮ ይቀዘቅዛል። መላመድ አለ . . .›› ቅብጥርሶ እያለ ሲቀጥል ልቤ ተጎተተ። እንዲያው ግርም ብሎኝ በኋላ ለማንጠግቦሽ ስነግራት፣ ‹‹መውለድ አቅቶኝ ቢሆን እርሱም የሚያከራየው ማህፀን ኖሮት ቢሆን አንድ ነገር ነው። ያልፀነሰውን ከሚያምጥ ያረረ ድስቱን አያማስልም?›› ብላ አራስ ነበር ሆና ሰነበተች። ትዳር መኪና ቢሆን ብላችሁ አስቡ ለቅፅበት። ‘አልቻልክበትም እኔ ስነዳ እይ’ ሊባል እስኪ? በሰው መኪና? እግዚኦ!

እንግዲህ ጨዋታም አይደል የያዝነው? ከደላላ አንዱና ዋነኛ ተግባር ስለላ ነው። ዘወር ዘወር ማለት አለ። ማሰስ ደግሞ ከመሀል አይጀመርም። ለነገሩ የኮንዶሚኒየሙ ትውልድ እንጀራ መጋገር ስለተወ የምጣድ ምሳሌ ይለፈው። ስካቫተሩን አሻሽጬ ባገኘሁት ጠቀም ያለ ረብጣ ሻይ ቡና እያልኩ ደግሞ ሌላ ሥራ ልፈልግ ስወጣ ሰፈሩ በአንድ እግሩ ቆሟል። ‹‹ምንድነው?›› ስል ሳያሰልሱ ከባሻዬ ጋር በአጥር የሚጣሉ አባወራ መሀል መንገድ ላይ ቁጭ ብለው ሲፀዳዱ ደረስኩ። መንደርተኛው እግዚኦ ይላል። ‹‹በቃ ሰውዬው ለቀዋል አማኑኤል እንውሰዳቸው…›› ትላለች ከኋላዬ በመብረቅ ድምፅ። ገና ለገና ባሻዬ የዕድሩ ሰብሳቢና ገንዘብ ያዢ ናቸው በሚል አጉል ተስፋ ደግሞ ጆሮ በሚበሳ ድምፅ ‹‹እሰይ ባሻዬ ተገላገሉ። አረፉ ከእኝህ ነገረኛ ሰውዬ…›› ይባልልኛል።

ዘወር ስል የባሻዬን ልጅ አየሁት። ተጠቃቀስንና ወደ አዛውንቱ ጠጋ ብለን፣ ‹‹ምነው? ምነው? አሁን ይኼ ከእርስዎ ይጠበቃል? በተከበሩበት አገር?›› ብዬ ጀመርኩ። አገጫቸውን እንደተደገፉ ምንም የመደንገጥ ምልክት ሳያሳዩ፣ ‹‹አይ ልጄ! እኔስ ሆን ብዬ ነው ይህን የማደርገው። ይብላኝ ለአፋሹ!›› እያሉ ምሳጤያቸው በረታ። የባሻዬ ልጅ በመጓጓት፣ ‹‹እኮ ምን አስበው?›› አላቸው። ‹‹አይገርምህም? ይኼ የአካባቢያችን ሰው እኔ እዚህ የተፈጥሮ ግዳጄን ስወጣ ዓይቶ እንደደነገጠው፣ ሰሜን ኮሪያ የኃይድሮጂን ቦምብ ሙከራ አደረገች፣ አሜሪካ ሊሰነዘርባት ከሚችል ማንኛው አደጋ ራሷን ለመጠበቅ የጦር ኃይሏን በተጠንቀቅ አሰለፈች፣ ሩሲያ አዲዮስ ምዕራባውያን አለች፣ አይሲስ በየቀኑ. . .  ይታይህ፣ በየቀኑ . . . ሰው እንደ በግ አረደ፣ ከፎቅ ወረወረ… ሲባል ደንግጧል? አልደነገጠም! የፍትሕ እጦቱን፣ የእጅ አዙር ሳንሱሩን፣ የመልካም አስተዳደር ብልሽቱን፣ ሙስናውንማ ለምደነው ምን እልሃለሁ? በቃ ለምደነው ጭራሽ ስንኮተኩተው እንውላለን። አሁን እስኪ ከእኔ ድርጊትና ከነገርኩህ የቱ ጨርቅ ያስጥላል?›› ብለው ሁለታችንም ላይ ሲያፈጡ ማን የአዕምሮ ሐኪም እገዛ እንደሚያስፈልገው ገባኝ። አልገባችሁም? ልድገመው? ቂቂቂ!

በሉ እንሰነባበት። ያጫወትኳችሁ አባወራ ተግባር የአለቃ ገብረ ሃናን ሥራ አስታወሰኝ። አንዳንዶች የዚህ ታሪክ ዋና ባለመብት ሌላ ሰው ናቸው ሲሉ ብሰማም ‘ቱ ሌት’ በማለት በአለቃ ገብረሃና ስም አጫውታችኋለሁ። በነገራችን ላይ አሻሻልኩ ብሎ አንድን ጥሩ መሠረት ማናጋት በበኩሌ ማወቅ አልለውም። ከመፈላሰፌ በፊት ግን የአለቃን የምታውቋትን ጨዋታ ጫፍ ላስያዛችሁ። ግብዣ ተጠርተው ኖሮ የአዘቦት ልብሳቸውን ለብሰው ሲሄዱ አትገቡም ተባሉ አሉ። ተመልሰው የክት ልብሳቸውን ለብሰው ሲሄዱ ታሪኳ ትዝ ትላችኋለች። አስታወሳችኋት? ላለማሰልቸት አልጨርሳትም። በዚህ አጋጣሚ እንኳን ፕሮፓጋንዳ ተረትም ሲደጋገም እንደሚሰለች መልዕክት ለማስተላለፍ በማለት ያለ ስፖንሰር የሠራሁት ማስታወቂያ ነው። ምናልባት አንዳንዶቻችሁ ኢርፎን ሰክታችሁ የኢትዮጵያ ቴሌቭዢን እያያችሁ ከሆነ ምራ አልመራም ከሚባለው ጣጣ ስላመለጣችሁ ደስ ይበላችሁ። ግን ዴሞክራሲ ባይኖር አሁን ይኼን ሁሉ ብዬ የት እገባ ነበር?

ስቀጥል. . . (ከአጀማመራችሁ ይልቅ ለአጨራረሳችሁ ፀልዩ እያልኩ አጨራረሴን ላከሽፈው ነው መስል) እንኳን ከሕይወት ከሞት መማር ባንወድም ከአለቃ ‘ልብሴ እንጂ እኔ አልተጠራሁም’ ተረት የምንመዛት ነገር አለች። በያዝነውና ባፈራነው ልክ እንጂ የሰው ዘር አባል በመሆናችን ብቻ መከባበር ድሮ ቀርቷል። ለነገሩ ድሮም ባይኖር ነው አለቃ ልብሳቸውን ወጥ የለቀለቁት። ግን ወደፊት ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም? ለተሻለ ነገ፣ ለተሻለ ብሩህ ወደፊት በስሚንቶና በብሎኬት ብቻ መሠረት አይጣልም እላለለሁ እኔ አንበርብር ምንተስኖት። አዋጅ ከመሰለም ይምሰል! ማን አውጆ ማን ይቀራል? እንዴ? ሳንከባበር ፍቅር አለ ታዲያ? ፍቅር ሳይኖር እኛ የሚባል ተውላጠ ስም ባዶ ቃል አይሆንም? አገር ያለሰው ካልቆመች ሰው እንደ ሰውነቱ ሊታይ አይገባውም? እስኪ የሰው ዘር አባል እንሁን መጀመሪያ! አንዱ በጎረሰው እስከ መቼ እንታነቅ? መልካም ሰንበት!      

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት