ፈረንሣዊው የፊፋ ዋና ጸሐፊ ተባረሩ
ከታላላቅ መንግሥታት ተፅዕኖ ሳይቀር ገለልተኛ ሆኖ በአይነኬነቱ ለዓመታት የዘለቀው የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በተቋሙ ውስጥ የተንሰራፋውን የሙስና ቅሌት እየመረመረ የሚገኘው የፊፋ ሥነ ምግባር ኮሚቴ ምርመራውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ፈረንሣዊው የፊፋ ዋና ጸሐፊ ዠሮም ቫልክን አሰናብቷል፡፡
ከሁለት አሠርታት በላይ የፊፋን የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ያለተቀናቃኝ ጨብጠው እስከ 2015 መጨረሻ ድረስ የቆዩት ሲዊዘርላንዳዊው የዕድሜ ባለፀጋው ሴፕ ብላተርና የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር (ዩኢኤፍኤ) ፕሬዚዳንት ሚሸል ፕላቲኒ በዚሁ ከፊፋ ጋር ተያይዞ ሲነገር በቆየው የሙስና ቅሌት ተዘፍቀው ስለተገኙ የስምንት ዓመት ዕገዳ ተላልፎባቸው መሰናበታቸው ይታወሳል፡፡
አሁን ደግሞ የፊፋ ዋና ጸሐፊ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩትና የ55 ዓመቱ ፈረንሣዊው ዠሮም ቫልክ የሥነ ምግባር ኮሚቴው እ.ኤ.አ. ጥር 13 በዙሪክ ባደረገው ስብሰባ እንዲታገዱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ መክንያት ያለው ደግሞ በ2010 እና በ2014 የዓለም ዋንጫ ዝግጅት ወቅትና በተለይ ደግሞ ኮንፌዴሬሽን ኦፍ ኖርዝ ሴንትራል አሜሪካ ኤንድ ካሪቢያን አሶሴሽን ፉትቦል (ሲኦኤሲኤሲኤኤ) አዘጋጅ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ለነበሩት ጃክ ዋርነር ተሰጥቷል ተብሎ በሥነ ምግባር ኮሚቴው ይፋ የተደረገው የአሥር ሚሊዮን ዶላር ጉዳይ ስለመሆኑ ተዘግቧል፡፡ ቀጣዩ የፊፋ ምርጫ በሚቀጥለው ወር እንደሚከናወንም ተነግሯል፡፡