Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ታጥረው በተቀመጡ የሚድሮክ ቦታዎች ላይ የመጨረሻ የተባለ መመርያ ተላለፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ሚድሮክ ግንባታ ለመጀመር ተዘጋጅቻለሁ ብሏል

በአዲስ አበባ ከተማ ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ የሚድሮክ 13 ቦታዎች ጉዳይ በበላይነት እየተከታተለ የሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ከሚድሮክ ባለሥልጣናት ጋር ሐሙስ ጥር 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ከመከረ በኋላ የመጨረሻ ያለውን መመርያ አስተላለፈ፡፡

የመጨረሻ በተባለው መመርያ በመንግሥት ወገን አሉ የተባሉ ችግሮች በመፈታታቸው ሚድሮክ በአስቸኳይ ወደ ግንባታ እንዲገባ፣ ይህ ካልሆነ ግን መንግሥት ሁሉንም ቦታዎች ወደ መሬት ባንክ እንደሚያስገባና ከዚህ በኋላም ምንም ዓይነት ምክንያት እንደማይቀበል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡

ሚድሮክ በበኩሉ በቦታዎቹ ላይ ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችል የዲዛይን ክለሳ ከማከናወኑ በላይ፣ የሚድሮክ ባለቤት ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲ ከፍተኛ ገንዘብ መመደባቸውን በመግለጽ መመርያውን እንደሚቀበል በወቅቱ ማረጋገጡን ምንጮች አመልክተዋል፡፡

ጥር 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተካሄደው ውይይት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የመሬትና ማኔጅመንት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አባተ ስጦታውና ሚድሮክ በቅርቡ ያቋቋመው ሲቲ ዴቨሎፕመንት ፕሮጀክት ኦፊስ ኃላፊ አቶ አብነት ገብረ መስቀል ተገኝተዋል፡፡

የውይይቱ ማጠንጠኛ ሚድሮክ በተለያዩ ጊዜያት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተረከባቸውን ቦታዎች ለዓመታት አጥሮ መቀመጡ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሌሎች አልሚዎች ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጸም ዕርምጃ ቢወስድም፣ በሚድሮክ ላይ ግን ዕርምጃ አለመውሰዱ በመንግሥት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑ ተወስቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሥሩ በሚገኘው የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ አማካይነት ባስጠናው ጥናት 109 ቦታዎች ለዓመታት ታጥረው ተቀምጠዋል፡፡ ከእነዚህ ቦታዎች መካከል 13 የሚሆኑት የሚድሮክ ናቸው፡፡ ኤጀንሲው የአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ዕርምጃ እንዲወስድ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡

ካቢኔው 56 ቦታዎች እንዲነጠቁ ውሳኔ ሲያሳልፍ፣ በሚድሮክ ይዞታዎች ላይ ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቁ አይዘነጋም፡፡ አስተዳደሩ ከዚህ በፊት በልደታና በየካ ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ የሚድሮክ ቦታዎችን ካርታ ቢያመክንም፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውሳኔ ሚድሮክ በድጋሚ ቦታዎቹን ማግኘቱ ይታወሳል፡፡

ሚድሮክ ግንባታ ማካሄድ ያልቻለበትን ምክንያት በመጥቀስ ቅሬታ ያቀረቡት ሼክ አል አሙዲ እንደተናገሩት፣ ሚድሮክ ግንባታዎቹን ማካሄድ ያልቻለው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ችግር ነው፡፡

ሼክ አል አሙዲ ፒያሳ ባለው ቦታ ግዙፍ ግንባታ ማካሄድ አይፈቀድም በመባሉ፣ በሸራተን ማስፋፊያ ቦታ ላይ ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ ጋራዥ መነሳት ባለመቻሉ ግንባታ ማካሄድ እንዳልቻሉ ለአብነት ገልጸው ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በ13ቱም ቦታዎች ግንባታ ለማስጀመር እንዲቻል የማስተባበር ኃላፊነቱን መውሰዱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረት ሚድሮክ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት ሲከናወኑ የቆዩት ሥራዎች በመጠናቀቃቸው፣ ባለፈው ሐሙስ የመጨረሻ ውይይት ሊካሄድ መቻሉን ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የመንግሥት ተወካዮች እንደገለጹት፣ እነዚህ ቦታዎች ላይ በወቅቱ ግንባታ ባለመካሄዱ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የውል ማሻሻያ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህ አሠራር መንግሥትን ለከፍተኛ ትችት የዳረገው በመሆኑ፣ የመጨረሻ እልባት እንደሚያስፈልገው ተገልጿል፡፡

በዚህ መሠረት ሚድሮክ በአስቸኳይ ወደ ሥራ ካልገባ መንግሥት በሚወስደው ዕርምጃ ሚድሮክ ቅር ሊሰኝ እንደማይገባ መግባባት ላይ መደረሱን ምንጮች አስረድተዋል፡፡

አቶ አብነት በበኩላቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወጪ ተደርጎ (ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ) ከዚህ ቀደም የተሠሩት ዲዛይኖች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸው፣ ሼክ አል አሙዲ ግንባታውን የሚያካሂድ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት መቋቋማቸውን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ለፕሮጀክቶቹ በመመደቡ ወደ ግንባታ ለመግባት የሚያስችለው ዝግጅት መጠናቀቁን ማስረዳታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ዓለማየሁና አቶ አብነት አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች