Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቄራዎች ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተርን ጨምሮ ስድስት ዳይሬክተሮች ክስ ተመሠረተባቸው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመንግሥት ሥራን በማያመች አኳኋን በመምራትና በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው የታሰሩትን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጨምሮ፣ ስድስት ዳይሬክተሮችና ሁለት ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሠረተ፡፡

ተከሳሾቹ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አቶ ኤፍሬም ደሳለኝ፣ የእርድ አገልግሎትና የሥጋ ሽያጭ የሥራ ሒደት ዳይሬክተር አቶ ተኮላ ኃይሉ፣ የፕላን በጀትና ፋይናንስ የሥራ ሒደተ ዳይሬክተር አቶ ሙንተሃ ዓሊ፣ የፕላን በጀትና ፋይናንስ የሥራ ሒደት ረዳት ዳይሬክተር ወ/ሮ ፀሐይ ደበሌ፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ውብሸት አሰፋና የገንዘብና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ንጉሤ ታደሰ ሲሆኑ፣ ክሱን የመሠረተባቸው የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡

ከድርጅቱ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው ከዳይሬክተሮቹ ጋር ክስ የተመሠረተባቸው፣ በጡረታ ይተዳደራሉ የተባሉት አቶ ገብረ አምላክ በርሄና የአዲቤክ ኤክስፖርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ በረከት አድማሱ (በሌሉበት) መሆናቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

የድርጅቱ ኃላፊዎች የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት በማሰብ ከአዲቤክ ሥራ አስኪያጅ ጋር በመመሳጠር ድርጅቱ የከብት እርድ ሲፈጽም፣ የእርድ ተጠቃሚ ደንበኞች የማይወስዷቸውን ተረፈ ምርቶች አወዳድሮ ለመሸጥ ያወጣውን ጨረታ በሕገወጥ መንገድ እንዲያሸንፉ ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

ድርጅቱ ተረፈ ምርቶቹን ለመሸጥ ያወጣውን ጨረታ የሚያሸንፍ ተጫራች ተረፈ ምርቱን የሚያዘጋጅበት ቦታ ከሌለው እንደማይሰጠው የታወቀ ቢሆንም፣ አዲቤክ ማሸነፍ እንደሌለበት እያወቁ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ እንዲያሸንፍ ማድረጋቸውን ክሱ አክሏል፡፡ አሸናፊው ለሚወስደው ተረፈ ምርትም በቅድሚያ 500,000 ብር ማስያዝ የነበረበት ቢሆንም፣ 260 ሺሕ ብር እንዲያሲዝ በማድረግ ድርጅቱን ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸው ተገልጿል፡፡ አሸናፊው ድርጅት ቀደም ብሎ ለወሰደው ተረፈ ምርት ያልከፈለው ገንዘብ ስለነበረበት የፍትሐ ብሔር ክስ የተመሠረተበት ቢሆንም፣ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ክሱ እንዲቋረጥ በማድረግ ስህተት መፈጸማቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ ድርጅቱ ከእርድና ከሥጋ ሥርጭት ጋር በተያያዘ ከአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ጋር ውል የገባ ቢሆንም፣ በኃላፊዎቹ የተፈጸመው ድርጊት ከማኅበሩ ጋር ከገባው ውል ፍፁም ተቃራኒ በሆነ መንገድ መሆኑን ክሱ ያብራራል፡፡

ሽያጩ የተፈጸመው የልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ወይም እያንዳንዱ ነጋዴ ውክልና ሳያገኝና የተሸጠው ተረፈ ምርት ክፍያ ለልኳንዳ ነጋዴዎች በትክክል ስለመድረሱ ሳይረጋገጥ፣ ለልኳንዳ ነጋዴዎች ክፍያ እንዲፈጸም የክፍያ መጠየቂያ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ የሥራ ሒደት በማቅረብ እንዲፈጸም መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡ ኃላፊዎቹ ከአዲቤክ ኤክስፖርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ጋር በመመሳጠር የክፍያ መጠየቂያ በማቅረብ በተለያዩ ቼኮች በድምሩ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፈል በማድረግ ባደረሱት ጉዳት፣ በፈጸሙት የመንግሥት ሥራን በማያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል ክስ እንደ መሠረተባቸው የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

በሌላ በኩል ተከሳሾቹ የድርጅቱን ንብረት አወጋገድ ሥርዓት አግባብ ባለው መንገድ ማስፈጸም ሲገባቸው የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ያወጣው መመርያ ለድርጅቱ ሳይደርስ የደረሰ በማስመሰል፣ አቶ ገብረ አምላክ በርሄ የተባሉትን ተከሳሽ ለመጥቀም ሕገወጥ ተግባር መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡

መመርያው ለድርጅቱ የደረሰ በማስመሰል፣ የሥራ አመራር ቦርድ እንዲወገዱ የተጠየቁትን የኮላ መቀቀያ ኩከሮችን በሚመለከት ‹‹በቅድሚያ በቴክኒክ ኮሚቴ መወገድ ያለበት ስለመሆኑ ማረጋገጫ ይቅረብ›› የተባለውን፣ ‹‹የሥራ አመራር ቦርዱ ንብረቶቹ እንዲወገዱ ውሳኔ ሰጥቷል›› በማለት የሐሰት ውሳኔ በማስተላለፍ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠራቸውን ያብራራል፡፡

አቶ ገብረ አምላክ የተባሉት ተከሳሽ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ‹‹ለሚመለከተው ሁሉ›› የሚል ሐሰተኛ ደብዳቤ ይዘው በመቅረብ የመኪና ጐማ፣ ባትሪና ቁርጥራጭ ብረቶች ያለምንም ደረሰኝ እንዲወስዱ መደረጉንም ክሱ ይገልጻል፡፡ ግለሰቡ ሌላ የሐሰት ደብዳቤ በማቅረብ ከኃላፊዎቹ ጋር በመመሳጠር የተጠቀሱትን የድርጅቱን ንብረቶች ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡ ኃላፊዎቹ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራትና በወንጀል ድርጊት ተካፋይ በመሆን ሙስና ፈጽመዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡ ክሱን የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ለተከሳሾቹ ክሱን አንብቦ በክሱ ላይ ተቃውሞ ካላቸው ለመጠባበቅ ለጥር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች