Tuesday, February 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለሕዝብ ፍላጎት ተገዢ መሆን ይለመድ!

ለአዲስ አበባና ለኦሮሚያ ልዩ ዞን ተዘጋጅቶ የነበረው የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሙሉ በሙሉ እንዲቆም፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰሞኑን መወሰኑ ታውቋል፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰውም ከሕዝብ ጋር በተደረገ ውይይት ተቀባይነት እንደሌለው በመረጋገጡ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በኦሮሚያ ምክር ቤት (ጨፌ) ጉባዔ ፀድቆ የነበረው የከተሞች አዋጅም በተወሰኑ አንቀጾች ላይ በሕዝብ የተነሱ ጥያቄዎች በመኖራቸው፣ ጨፌው እንደገና እንዲያየው ውሳኔ ላይ መደረሱ ተገልጿል፡፡ በክልሉ በሚከናወኑ ማናቸውም ጉዳዮች ላይ የሕዝብ አመኔታ ካልኖረ በስተቀር ተፈጻሚነት እንደማይኖር ተወስቷል፡፡ ይህ ዓይነት ዕርምጃ የሚደገፍ ከመሆኑም በላይ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን ለመፍጠር ጠቃሚ ነው፡፡ ጎን ለጎን ደግሞ የልማት አጀንዳው ሲታጠፍ በእርግጥም የሕዝብ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑ ግልጽ መሆን አለበት፡፡

ምንም እንኳ ዕርምጃው የሚደገፍና ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም፣ የሰው ሕይወት ከመጥፋቱና የአካል ጉዳት ከመድረሱ፣ እንዲሁም የንብረት ውድመት ከመከሰቱ በፊት ከሕዝብ ጋር መምከር አለመቻሉ ያስቆጫል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የጋራ ማስተር ፕላኑን መነሻ በማድግ በተለያዩ ሥፍራዎች በተቀሰቀሱ ሁከቶች የታየው፣ የክልሉ መንግሥት ከሕዝብ ጋር የነበረው መስተጋብር የላላ እንደነበር ነው፡፡ በክልሉ ከነውጡ በኋላ ከአርሶ አደሮች፣ ከከተማ ነዋሪዎች፣ ከወጣቶችና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች የተንፀባረቁት የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የፍትሕ መጓደልና የሙስና መንሰራፋት ናቸው፡፡ በተደረጉት ውይይቶች የመንግሥት ተወካዮች እነዚህን ችግሮች ለማስወገድና የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ለመሥራት ቃል መግባታቸው ተሰምቷል፡፡ ይህም ጥሩ ነው፡፡ የሕዝብ ይሁንታም ያሻዋል፡፡

ለበርካታ ጊዜያት የውዝግብ መንስዔ የሆነው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ የተቀናጀ ማስተር ፕላን፣ በኦሮሚያ ክልል በኩል ሙሉ በሙሉ እንዲቆም የተወሰነው ሕዝቡ በጥልቀት ተወያይቶበት በተገኘው ግብረ መልስ መሠረት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በየትኛውም የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ሕዝብ የግልጽነት ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ ጥያቄውን ተቀብሎ ተገቢውን ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ መንግሥት የሚደመጠው ሕዝብን ሲያዳምጥ ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ በመልካም አስተዳደር ዕጦት ሲሰቃይ፣ ፍትሕ አጥቶ ሲንገላታ፣ በኔትወርክ በተሳሰሩ ኃይሎች በሙስና ሲታመስና ግራ ሲጋባ አመፅ ይቀሰቀሳል፡፡ ሰብዓዊ ክብሩና መብቱ ተጥሶ አቤቱታውን የሚሰማ ሲጠፋ ያለው አማራጭ ነውጥ ማስነሳት ነው፡፡ የታየውም ይኸው ነው፡፡ በአሁኑ ውሳኔም የሕዝቡ ድምፅ በትክክል መገኘቱም ሊረጋገጥ ይገባል፡፡

ምንም እንኳን የጋራ ማስተር ፕላኑ የታሰበው ለጋራ ልማት ነው ቢባልም፣ ከሕዝቡ ጋር ውይይት ያልተደረገበትና ግንዛቤ የተያዘበት ስላልነበር የዛሬ ዓመት አካባቢም በተለያዩ አካባቢዎች ሁከት ተነስቶ ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ሕዝቡ በጋራ ማስተር ፕላኑ ላይ ጥርጣሬ ሲኖረውና ጥያቄ ሲያነሳ ችላ መባል አልነበረበትም፡፡ በክልሉ ውስጥ በስፋት በሚታዩት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት የሕዝብን ጥያቄዎች ማዳፈን የተለመደ በመሆኑ ችግሩ ተንከባሎ መጥቶ ለብዙ ዜጎች ሞት፣ አካል መጉደል፣ የሥነ ልቦና ጉዳትና ለንብረት ውድመት ዳርጓል፡፡ የዘገየው ዕርምጃ የማስተር ፕላኑን ተግባራዊ መሆን ሙሉ በሙሉ ቢያስቆምም፣ አሁንም በተለያዩ ጉዳዮች የሚታዩ ችግሮችን ሥር ነቀል በሆነ መንገድ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተግባር ማሳየት የግድ ይላል፡፡ የሕዝብ አመኔታም በግልጽ መንፀባረቅ አለበት፡፡ በሕዝብ ስም ተገቢ ያልሆኑ ተግባራት እንዳይፈጸሙ መንጠቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ከኦሮሚያ ጉዳይ ወጥተን የመላ አገሪቱን ዙሪያ ገብ ችግሮች ስንቃኝ፣ ከዲስኩር አልዘል ያሉ ፉከራዎች ብቻ ናቸው የሚሰሙት፡፡ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ ተሠርቶ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የመከሩበት ጥናት የአገሪቱን ወቅታዊ ገመና ፍንትው አድርጎ አሳይቷል፡፡ ሕዝቡ በመልካም አስተዳር ዕጦት በመሰቃየቱ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ መሸርሸሩን፣ ፍትሕ በገንዘብ እየተሸጠ ሕዝብ መድረሻ ማጣቱን፣ ሙስና እንደ ሰደድ እሳት መዛመቱን፣ በሕገ መንግሥቱ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው ቢባልም የደላላ መጫወቻ መሆኑን፣ ወዘተ ብዙ ችግሮች ተወስተዋል፡፡ በየተገኘው መድረክም ዕርምጃ ይወሰዳል እየተባለ ይነገራል፡፡ አሁን ግራ የሚያጋባው መንግሥት ከንግግር የዘለለ ተግባራዊ ለመሆን ለምን አቃተው የሚለው ነው፡፡ ቁርጠኝነት የጠፋው ለምንድነው? ሥርዓቱ ችግሮች ናቸው ብሎ ነቅሶ ባወጣቸው ጉዳዮች ላይ ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ችላ ያለው ለምንድነው? ሕዝብ መልስ ይፈልጋል፡፡ ተጨባጭ መልስ፡፡

ድንገት በየሚዲያው ብቅ እያሉ ተግባራዊ ዕርምጃ መውሰድ እንጀምራለን የሚሉ ባለሥልጣናት ሕዝቡ እየጠበቃቸው መሆኑን ይዘነጋሉ? ወይስ ሕዝቡ እነ እከሌ ይጠየቁ ብሎ ሰላማዊ ሠልፍ እስኪወጣ ነው የሚጠብቁት? ሕዝብ እነ ማን በላዩ ላይ እንደሚቀልዱበት፣ እነ ማን ፍትሕ እንደሚያዛቡበት፣ እነ ማን ደግሞ እየዘረፉ እየከበሩ እንዳሉ ያውቃል፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥት ዲስኩር እንዲያሰማ ሳይሆን ቁርጠኛ ዕርምጃ እንዲወስድ ነው የሚፈለገው፡፡ መንግሥት የማይቻለው ከሆነም ቁርጡን ተናግሮ የመሸበት ይደር፡፡ የአገር ችግር ናቸው የተባሉ ጉዳዮችን እያወሱ ተጠያቂነትን ወደ ጎን መግፋት ወይም ማድበስበስ የትም አያደርስም፡፡ በሕዝብ ላይ መቀለድና ያላግባብ መበልፀግ የሚያመጡት ምሬት የሚፈጥረው አመፅ ማንም አያስቆመውም፡፡ ለሕዝብ ችግሩን ከመናገር በላይ ተግባራዊ ዕርምጃ ወስዶ ማሳየት የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡

የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 12 የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነትን በማያወላዳ መንገድ ገልጾታል፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት፣ ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ ዕምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ማንሳት እንደሚችልና ዝርዝሩ በሕግ እንደሚወሰን ተደንግጓል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች መሠረታዊ መብቶችንና ነፃነቶችን አካቷል፡፡ እነዚህ በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩ መብቶችና ነፃነቶች ሲከበሩ ሕዝብ ይደመጣል፡፡ ሕዝብን የሚያንገላቱና የሚዘርፉ ደግሞ በሕግ ይጠየቃሉ፡፡

የሕገ መንግሥቱን ተፈጻሚነትና አተረጓጎም በተመለከተ አንቀጽ 13፣ በማንኛውም ደረጃ የሚገኝ የፌዴራል መንግሥትና የክልል ሕግ አውጪዎች፣ ሕግ አስፈጻሚዎችና የዳኝነት አካላት በመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ምዕራፍ ውስጥ የተካተቱትን ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡ ሕገ መንግሥት ይከበር ማለት የሕግ የበላይነት ይኑር ማለት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይከበር ማለት ሕዝብ ይደመጥ ማለት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይከበር ማለት ሕገወጥነት ይወገድ ማለት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይከበር ማለት ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት ይግለጹ ማለት ነው፡፡ አፈና ይቁም ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ዜጎች በመንግሥት አሠራሮች ላይ ጥያቄ ኖሯቸው፣ ምቾት ሳይሰማቸው፣ እንዲሁም ከፍላጎታቸው ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ጥያቄ የማቅረብ መብታቸው ይከበር፡፡ የዜጎችን መብት በማፈን አገር ማስተዳደር አይቻልም፡፡ በሕዝብ ስም በመነገድ ውዥንብር የሚፈጥሩ ካሉም በቃችሁ መባል አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲ የሚገነባው ኃላፊነት የሚሰማው ነፃ ኅብረተሰብ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ይህ ነፃ ኅብረተሰብ ለሕግ የበላይነት ጠበቃ ሲሆን፣ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት መከበር ምሰሶ ይሆናል፡፡ ለሰላምና ለመረጋጋት ደግሞ ዘብ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ለሕዝብ ፍላጎት ተገዥ መሆን ይለመድ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አፍሪካውያን እንዳይታዘቡን ጥንቃቄ ይደረግ!

የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው የመሪዎች ጉባዔ በኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሄደ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ ከዛሬ 61 ዓመት በፊት ከጥንስሱ እስከ ምሥረታው ወሳኝ ሚና የነበራት ኢትዮጵያ...

ታሪክን ከመዘከር ባሻገር የመግባቢያ መንገዱም ይፈለግ!

እሑድ የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ የተመረቀው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከታላላቅ አገራዊ ክንውኖች ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ ይህንን መሰል የታሪክ ማስታወሻ በታላቅ ክብር...

ባንኮቻችን ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ያስፈልጋቸዋል!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሚመሰገንባቸው ተግባራት መካከል አንደኛው፣ በውስጣዊ ትርምስ ለመፍረስ ይንገዳገዱ የነበሩ ባንኮችን በጠንካራ ቁጥጥር መታደግ መቻሉ ነው:: ከዚህ ቀደም በተለያዩ ነባር የግል ባንኮች...