Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሁለት ሳምንት ከግል ባንኮች 4.5 ቢሊዮን ብር ወደ ንግድ ባንክ ገባ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ድርጊቱ የግል ባንኮችን ሥጋት ላይ ጥሏል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ የሚያቀርብ መሆኑ ከታወቀ በኋላ፣ በርካታ የግል ባንኮች ደንበኞች 4.5 ቢሊዮን ብር ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስገቡ፡፡ ይኼ ድንገተኛ ክስተት የግል ባንኮችን ሥጋት ፈጥሮባቸዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ዕርምጃ ለመውሰድ ቃል መግባቱም ተሰምቷል፡፡

ከወቅታዊው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ ንግድ ባንክ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መድቤያለሁ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት፣ የውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎች ሌተር ኦፍ ክሬዲት ለመክፈት የተጠየቁት 100 በመቶ ክፍያ በመሆኑ፣ በሌሎች የግል ባንኮች ያላቸውን ገንዘብ አውጥተው ወደ ንግድ ባንክ እንዲሄዱ አስገድዷቸዋል፡፡

ያልተጠበቀ ነው የተባለው የገንዘብ እንቅስቃሴ አብዛኛዎቹን የግል ባንኮች በሁለት ሳምንት ውስጥ ከፍተኛ ወጪ እንዲያወጡና በእንቅስቃሴያቸው ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተጠቁሟል፡፡ የብድር ጥያቄዎችን መልሰው እንዲመረምሩና ወጪያቸውን እንዲቀነሱም ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንዳንድ አምራቾች ሥራ ወደማቆም የደረሱ በመሆናቸው፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰደው ዕርምጃ በግል ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳደሩም በላይ፣ ደንበኞች ሳይፈልጉ ወደ ንግድ ባንክ እንዲሄዱ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡

ሁኔታው ያልተለመደ በመሆኑም ከግል ባንኮች የደረሰውን መረጃ መሠረት በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ችግሩን ለብሔራዊ ባንክ በማሳወቅ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ አድርጓል፡፡ በዚሁ ስብሰባ ላይ ንግድ ባንክ እሰጠዋለሁ ባለው የውጭ ምንዛሪ ምክንያት በሁለት ሳምንታት ውስጥ ከግል ባንኮች ወደ ንግድ ባንክ የሄደባቸውን ገንዘብ በአስረጅነት በማቅረብ፣ በዚህ ምክንያት ለሚፈጠር የገንዘብ እጥረት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክም ችግሩን በመረዳት ሰሞኑን በተፈጠረው ችግር ምክንያት ሊገጥም የሚችል እክል ካለ ለማቃለል፣ መፍትሔ ይሆናሉ ያላቸውን ዕርምጃዎች ለመውሰድ ቃል ገብቷል ተብሏል፡፡

ውይይቱ ባለፈው ሐሙስ ጥር 5 ቀን 2008 ዓ.ም. የተካሄደ ሲሆን፣ የግል ባንኮች ሊገጥማቸው ይችላል የተባለውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ ብሔራዊ ባንክ እንደ መፍትሔ ይወስዳል ተብሎ የሚጠበቀውና በምክክሩ ወቅትም ቃል የገባው፣ ባንኮች ከእያንዳንዱ ብድር ለቦንድ ግዢ የሚያውሉትን 27 በመቶ ክፍያ እንዲያዘገዩ ይደረጋል የሚለው አንዱ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ባንኮች የገንዘብ እጥረት በሚያጋጥማቸው ጊዜ ለቦንድ ግዢ ያዋሉትን ገንዘብ በማስያዝ፣ ከብሔራዊ ባንክ በሦስት ወራት ክፍያ የሚበደሩትን ብድር አቆይተው እንዲከፍሉ ማድረግ ነው፡፡

ይህ የተገባ ቃል ቢሆንም አፈጻጸሙ እንዴት ይሆናል የሚለው ጉዳይ ግን ወደፊት የሚታይ ይሆናል ተብሏል፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተፈጠረውን ችግር የበለጠ ያባባሰው ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሌተር ኦፍ ክሬዲት ለመክፈት የጠየቀው የመቶ በመቶ ክፍያ ነው፡፡ የተፈቀደላቸውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት መቶ በመቶ ክፍያ ለመፈጸም ያልቻሉ ደንበኞች መኖራቸውም ታውቋል፡፡

ከዚህ ቀደም አንድ ዕቃ ለማስመጣት የሚፈልግ ኩባንያ ወይም ግለሰብ የ100 ብር ዕቃ ለማስመጣት ቢፈልግ 20 ወይም 30 በመቶውን በቅድሚያ ከፍሎ ሌተር ኦፍ ክሬዲት ይከፍት እንደነበር የሚገልጹት የባንክ ኃላፊዎች፣ ዕቃው ሲታዘዝ ብድሩ እንደሚፈቀድና የዕቃው ዶክመንት ሲመጣ ቀሪው ክፍያ እንደሚፈጸም ይናገራሉ፡፡ አሁን ግን ንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ከፈለጋችሁ በምትፈልጉት የውጭ ምንዛሪ ልክ ገንዘብ ካስገባችሁ ሌተር ኦፍ ክሬዲቱን እከፍትላችኋለሁ በማለቱ፣ በተለያዩ የግል ባንኮች ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ይጠብቁ የነበሩ ደንበኞች ጭምር ገንዘባቸውን ከባንኮቹ አውጥተው ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሊወስዱ ችለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለመደው የሌተር ኦፍ ክሬዲት አሠራር ቢሠራ ይህ ሁሉ ችግር ላይፈጠር ይችል ነበር ተብሏል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ ከግል ባንኮች በሁለት ሳምንት ወደ ንግድ ባንክ አካውንት እንዲዛወር ከተደረገው 4.5 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከአንድ የግል ባንክ ብቻ ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡ 700 ሚሊዮን ብርም ወጥቶብኛል ያለ ባንክ አለ፡፡ 400 ሚሊዮን ብር በአንድ ሳምንት የወጣበት ባንክ መኖሩን የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

በአንድ ጊዜ ባንኮች ሳይታሰብ ይህንን ያህል ገንዘብ ማውጣታቸው ደግሞ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ውጥረት የሚፈጥር እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ እንደታወቀ ብሔራዊ ባንክ የባንኮችን የሥራ ኃላፊዎች በመጥራት በጉዳዩ ላይ ውይይት መደረጉ ግን በተወሰነ ደረጃ እፎይታ ሰጥቷቸዋል፡፡ ቢሆንም ክስተቱ ለባንክ ኢንዱስትሪው በተለይ ለግል ባንኮች ትልቅ ሥጋት ሆኗል፡፡ አንዳንድ ባንኮችም ይህ የገንዘብ ፍልሰት እንዳይቀጥልና ባንኮቻቸው ላይ አደጋ እንዳይፈጠር የውጭ ምንዛሪ ለማቅረብ እየሞከሩ ነው፡፡

ሰሞኑን ውጥረት የፈጠረው የፋይናንስ እንቅስቃሴ ግን በተለያዩ ወገኖች የተለየ አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡ ድርጊቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የበላይነት ያሳየ ነው የሚሉ ወገኖች፣ የኢንዱስትሪው የውድድር ሜዳ የተስተካከለ አለመሆኑ በግልጽ የታየበት ነው ብለውታል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁንም ጡንቻው ፈርጥሞ እንዲታይ፣ እንዲሁም በሌሎች ባንኮች ላይ እያሳረፈ ያለው ተፅዕኖ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጎልቶ የታየበትም ነው ተብሏል፡፡

አንዳንድ ወገኖች ደግሞ ባንኮች በተወሰኑ የቀናት ልዩነት ይህንን ያህል ገንዘብ እንዲያጡ መደረጉ አስገራሚ ቢሆንም፣ አሁን ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንፃር መንግሥት መፍትሔ ለመስጠት የሄደበት አካሄድ ግን ትክክል እንዳልሆነ የገለጹም አሉ፡፡

ሆኖም አሁንም ጎልቶ እየወጣ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሌሎች የግል ባንኮች የሚታዩት እንደተወዳዳሪ ሳይሆን፣ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን የመጉዳት ዓይነት ነገር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

መንግሥት ወይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይህንን ያህል የውጭ ምንዛሪ ሊያዘጋጅ መሆኑ ከታወቀ፣ ብሔራዊ ባንክ መረጃውን ለሌሎች ባንኮችም ማሳወቅና ዝግጅት እንዲኖር ማድረግ ይገባው ነበር ሲሉም ያክላሉ፡፡

የውጭ ምንዛሪውም ሁሉንም ባንኮች ባማከለ መንገድ መሠራጨት እንደነበረበት በመጥቀስ፣ ድርጊቱ የባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ጤናማ ውድድር እንዳይፈጠር ያደረገ፣ ለወደፊትም ሥጋት የሚፈጥር ድርጊት መሆኑን በመጥቀስ ድርጊቱን ኮንነውታል፡፡ ትክክለኛ የሚባለውን አሠራር ከማስፈንና ከግልጽነት አንፃር ሲታይም በጣም አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡

የግል ባንኮች ባልተጠበቀ ሁኔታ የሄደባቸውን ገንዘብ መልሶ ለማምጣት ብዙ ሥራ ይጠይቃቸዋል እየተባለ ነው፡፡ በተለይ ባንኮች የ2007 በጀት ዓመት የትርፍ ክፍፍል ያልሰጡ በመሆናቸው ይህንንም ለመክፈል ሊቸገሩ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

ችግሩ የአንድ ሰሞን መሆኑና በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚስተካከል እንደሆነ የተናገሩም አሉ፡፡ በአንድ ወቅትም ቢሆን ችግር መፈጠሩ ግን አይቀርም፣ ቢሆንም እንዲህ ዓይነት ያልታሰበ የገንዘብ ዝውውር ሲደረግ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ በሰሞኑ ችግር ግን የግል ባንኮች የተወሰነ መንገጫገጭ የሚገጥማቸው መሆኑ ግን ብዙዎች ተስማምተውበታል፡፡ በሌላ በኩል ክስተቱ በአገሪቷ ውስጥ ያለውን የገንዘብና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያመላከተ ነው ተብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት 16 የግል ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ እንደደረሰ ይታወቃል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች