Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የራሱን ማስተር ፕላን ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የራሱን ማስተር ፕላን ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

ቀን:

– የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የጋራ ማስተር ፕላኑን ውድቅ አደረገው

የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ዝግጅት እንዲቆም ከወሰነ በኋላ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በራሱ ክልል ውስጥ የሚገኘውን የማስተር ፕላኑን ክፍል ብቻ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ጀመረ፡፡

የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ ከኦሮሚያና ከአዲስ አበባ የተወጣጡ ከፍተኛ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚመራ ሥራ አመራር ቦርድ ነበረው፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ከሕዝብ በደረሰበት ጫና የልዩ ዞኑ ማስተር ፕላን እንዲቆም በመወሰኑ ከሥራ አመራር ቦርዱ ራሱን አግልሏል፡፡ በዚህ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ሥራ አመራር ቦርድ ለማቋቋም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አመልክተዋል፡፡

አዲስ የሚቋቋመው ሥራ አመራር ቦርድ ቀደም ሲል ከተዘጋጀው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ውስጥ ለልዩ ዞኑ የተሠራውን ክፍል በመተው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ክልል ላይ ብቻ በሚያርፈውና ተግባራዊ በሚደረገው ማስተር ፕላን ላይ ይነጋገራል ተብሏል፡፡

ማስተር ፕላኑ የቦርዱንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔን ይሁንታ አግኝቶ፣ 138 መቀመጫ ባሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የአዲስ አበባ ከተማ ባለሥልጣናት በዚህ ጉዳይ ላይ በቅርቡ ይፋዊ መግለጫ ስለሚሰጥ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ይዞታ በሆነው 54 ሺሕ ሔክታርና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ይዞታ በሆነው 1.04 ሚሊዮን ሔክታር፣ አንድ ላይ ከ1.1 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ማስተር ፕላን በማዘጋጀት፣ ከሞላ ጎደልም ዝግጅቱን ማገባደዱ ይታወቃል፡፡

በማስተር ፕላኑ ሁለቱ የአስተዳደር አካላት በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ተሰባጥረው የሚያድጉበት ዕቅድ ተነድፎ ነበር፡፡

ነገር ግን ይህ ግዙፍ ማስተር ፕላን በመዘጋጀት ላይ እንዳለ የተለያዩ ጥያቄዎች በመነሳታቸው በተለይ በኦሮሚያ ክልል ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ በዚህ ምክንያትም በኦሮሚያ ክልል በተነሳው ሁከት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ሕልፈት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ከማስከተሉም በላይ፣ በመማር ማስተማር ሒደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ተፈጥሯል፡፡

ከዚህ ማስተር ፕላን በተጨማሪ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49(5) ላይ፣ ኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ የሚያገኘው ልዩ ጥቅም ቢደነገግም፣ ድንጋጌው ወደ ተግባር አለመሸጋገሩ ጥያቄ አስነስቷል፡፡

ከጥር 2008 ዓ.ም. መጀመርያ አንስቶ ለሦስት ቀናት አስቸኳይ ስብሰባ የተቀመጠው የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ የውዝግብ መንስዔ ሆኖ የቆየው የአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ወስኗል፡፡ ቀደም ሲልም የክልሉ መንግሥት ሕዝብ ካላመነበት ተግባራዊ አይደረግም ማለቱ ይታወሳል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሐዘኑን ከመግለጽ ባሻገር፣ የተጎዱትንም ከሕዝብ ጋር ሆኖ ለማቋቋም እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ አስተዳደር ማግኘት ያለበትን የልዩ ጥቅም ጥያቄን በመተለከተ ሕገ መንግሥቱ ላይ በተቀመጠው መሠረት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለተነሳው የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ከከፍተኛ ባለሥልጣናት የተወጣጣ ግብረ ኃይል መቋቋሙን በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ ለአሥር ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው ማስተር ፕላን በ2005 ዓ.ም. መጠቀሚያ ጊዜው አብቅቷል፡፡ አዲሱ ማስተር ፕላን ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ መተግበር ቢኖርበትም፣ በዙሪያው ካሉ አካባቢዎች ጋር ተጣጥሞ እንዲሠራ በመወሰኑ ለ25 ዓመታት ተግባራዊ እንዲሆን እንዲዘጋጅ ታስቦ ነበር፡፡

ነገር ግን የኦሮሚያ ክልል ከዕቅዱ ራሱን በማግለሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለብቻው ተግባራዊ የሚያደርገው ዕቅድ ላይ አተኩሯል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በሳምንታዊው የአቋም መግለጫ፣ በኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተደረሰበትን የማስተር ፕላን ዝግጅት የማቆም ውሳኔ ደግፏል፡፡ ይህም እየተገነባ ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሕዝብ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ብሏል፡፡ በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና መሪ ድርጅቱ ኦሕዴድ ከሕዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት የተነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት መንቀሳቀስ መጀመራቸውን፣ በክልሉ የልማት ጉዳይም ሆነ መልካም አስተዳደርን በማስፈን ዘመቻ ላይ ከሕዝቡ ጋር እየተወያዩና እየወሰኑ መሥራታቸውን ይቀጥላሉ ሲል ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...