ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ለማመንጨት ወደሚያስችለው ደረጃ እየተቃረበ እንደሚገኝ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ገለጹ፡፡ ሚኒስትሩ ዓርብ ታኅሳስ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፣ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ50 በመቶ በላይ መሆኑን ጠቁመው የዓባይ ውኃም በግድቡ አራት የውኃ ማሳለፊያ ቀዳዳዎች (ከልቨርት) ማለፍ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ለመጀመሪያው የግንባታ ክፍል ሲባል የዓባይ ውኃ መስመር በጊዜያዊነት ተቀይሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ የግንባታ ክፍል ውኃ ለማሳለፍ ከሚችልበት ደረጃ በመድረሱ የዓባይ ውኃ ወደ ዋናው መስመሩ እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ለውኃው ጊዜያዊ ማለፊያ ሲባል ግንባታ ያልተከናወነበት ውስን ሥፍራ ላይ ግንባታ ተጀምሮ የተወሰነ ደረጃ ሲደርስ ግድቡ ውኃ መያዝ መጀመር ያስችለዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨሻ ላይ በሁለት ተርባይኖች ኃይል የማመንጨት ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡ ሚኒስትሩ ግድቡ ኃይል ለማመንጨት እየተቃረበ መሆኑን ቢገልጹም፣ ቁርጥ ያለ ቀን ግን አላስቀመጡም፡፡
አንዳንድ የግብፅ ሚዲያዎች እንደሚሉት ኢትዮጵያ በግድቡ ውኃ ላለመያዝ አልተስማማችም፣ ልትስማማም እንደማትችል አቶ ሞቱማ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ገዢ የሆነው ስምምነት መሪዎቹ የተፈራረሙት የመርህ መገለጫ ስምምነት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ስምምነት ላይ ደግሞ ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን የውኃ ሙሌቱ ይካሄዳል እንደሚል፣ የሙሌቱ ሁኔታ በሦስቱ አገሮች ስምምነት መሠረት እንዲሆን ከተፈለገ ጥናቱ ፈጥኖ እንዲካሄድ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በጥናቱ ረገድ ደግሞ ኢትዮጵያን ምንም የሚያሰጋት ነገር እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡