Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተባብሶ መቀጠሉ ተገለጸ

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተባብሶ መቀጠሉ ተገለጸ

ቀን:

  • በወር 15,000 ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ይሄዳሉ ተብሏል

መንግሥት ከፍተኛ የገንዘብና የእስራት ቅጣት የሚጥል ሕግ ያወጣ ቢሆንም፣ በተደራጀና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ሕጉን ተግባራዊ ሊያደርግ ባለመቻሉ በሕገወጥ ደላሎች የሰዎች ዝውውር ተባብሶ መቀጠሉ ተገለጸ፡፡

ከአራት ዓመታት በፊት በተለይ በሳዑዲ ዓረቢያ በቤት ሠራተኝነትና በሌሎች ሥራዎች ተሠማርተው በነበሩ ኢትጵያውያን ላይ በደረሰው ግድያ፣ አካል ማጉደልና ከፍተኛ እንግልት ምክንያት መንግሥት ዜጎች ወደ መካከለኛው ምሥራቃዊ አገሮች እንዳይጓዙ ዕግድ ጥሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላ ቀድሞ የነበረውን የውጭ አገሮች ሥራ ሥምሪትን የሚመለከተውን አዋጅ፣ በሌላ አዋጅ በመቀየርና ግዴታዎችንም ከፍ በማድረግ ሕግ ያወጣ ቢሆንም፣ አፈጻጸሙን ተግባራዊ ሳያደርግ የጉዞውን ዕግድ አንስቷል፡፡

ዕግዱን ሲያነሳም ሳዑዲ ዓረቢያን ጨምሮ ከሌሎች አገሮች ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ላይ ሳይደረስ፣ ለ73 የውጭ አገር ሥራና አሠሪ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሥራ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ ፈቃድ የተሰጣቸው ኤጀንሲዎች ለቤት ሠራተኝነት የሚሄዱ ዜጎችን የሚልኩት፣ ስምንተኛ ክፍል የደረሱና በተመረጡ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ስለሚሄዱበት አገር በቂ ትምህርት ተምረውና የብቃት መመዘኛ ፈተና ወስደው ሲያልፉ መሆኑን፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር፡፡

መሥፈርቱን ያሟሉ ኤጀንሲዎች ዜጎቹን መላክ የሚችሉት ወደ ኳታርና ዮርዳኖስ ብቻ መሆኑን ሚኒስቴሩ ያሳወቀ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ ፈቃድ የወሰዱት ኤጀንሲዎች ግን የሚልኩት ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኩዌትና ዱባይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ የተፈቀደላቸው አገሮች ለመላክ ገና መሥፈርቶችን ለማሟላት ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ፣ ኤጀንሲዎቹና ሕገወጥ ደላሎች በመመሳጠር ተጓዦቹ የቱሪስት ቪዛ እንዲያወጡ ያደርጋሉ፡፡ በየቀኑ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድና ሌሎች አየር መንገዶች ከ1,000 በላይ ታዳጊ ሴቶች (ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ)  እንደሚጓዙ ሚኒስቴሩ ማረጋገጡን እየገለጸ ነው፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ተወካይ ቆንስላና ሌሎች እማኞችም እንዳረጋገጡት፣ በወር በሕገወጥ መንገድ ከ15,000 በላይ ዜጎች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እየገቡ ነው፡፡ ይኼም በመሆኑ በሕገወጥ መንገድ የሚጓዙት ዜጎች ለርካሽ የቅጥር ክፍያና ለተለያዩ ጉዳቶች እየተዳረጉ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ሕጋዊ ጉዞውን በማዘግየቱ የመዘዋወር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀም ከየኤምባሲዎቹ ቪዛ በመጠየቅ በሕጋዊ መንገድ የሚጓዙ ቢሆንም፣ ጉዟቸው ሕጋዊ እንዳልሆነ በሠራተኛና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አበራ አስረድተዋል፡፡ ጉዞው ሕገወጥ መሆኑ በተደረገው ክትትል በመታወቁ ‹ፈርስት ቱር ኤንድ ትራቭል› ከሚባል የጉዞ ወኪል ጋር በመመሳጠር ሲሠራ የተደረሰበት፣ ‹አልጣኺር› የውጭ ሥራና አሠሪ አገናኝ ኤጀንሲን ፈቃድ መሰረዙን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ኤጀንሲው የየመን ዝርያ ያለውና ትውልደ ኢትዮጵያዊ አስመስሎ ፈቃድ ወስዶ በመገኘቱ ፈቃዱ መሰረዙን አክለዋል፡፡ በሠራው ሕገወጥ ድርጊትም በሚመለከተው አካል በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆንም አስታውቀዋል፡፡  

ፖሊስ ባደረገው ክትትል በሕገወጥ መንገድ ለመጓዝ ቪዛና ፓስፖርት የተዘጋጀላቸው 458 ዜጎችም ‹‹ፈቃድ ተሰጥቶናል›› በሚሉ የጤና ተቋማት ምርመራ ወስደው መገኘታቸውም ተገልጿል፡፡ በፌዴራል ፖሊስ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር ከተማ ደባልቄ እንደገለጹት፣ በተለይ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚሄዱ ዜጎች ቁጥር እጅግ ብዙ ነው፡፡ በቱሪስት ቪዛ አማካይነት ሙሉ ምርመራ በማድረግ ተዘጋጅተው ሊጓዙ ሲሉ የ458 ዜጎች የጉዞ ሰነድ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስረድተዋል፡፡ ሕጉን በመጣስና ከጉዞ ወኪሎች ጋር በመመሳጠር ሕገወጥ ዝውውር የፈጸሙ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ባልፈጸሙ አገሮች ካሉ ደላሎች ጋር በመመሳጠር፣ በየቀኑ ከ1,000 በላይ የቤት ሠራተኞች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያና ሌሎች አገሮችም እየተላኩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ችግሩ የሠራተኛና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን፣ ከ60 በላይ ለሚሆኑ የጤና ተቋማት ፈቃድ የሰጠው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጭምር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ምክንያቱም በተለይ ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ ያሉ ከሦስትና ከአራት በላይ የሚሆኑ ከፍተኛ ክሊኒኮች በሕገወጥ መንገድ ለመጓዝ የጤና ምርመራ የሚያደርጉ ዜጎችን አሠልፈው ሲሠሩ እየተመለከተ ዝም ማለቱ፣ ከተጠያቂነት እንደማያድነው አስተያየት ሰጪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በሕጋዊ መንገድ ቢሠራ በቀላሉና በሕጋዊ ሰነድ መጓዝ የሚችሉትን መንግሥት ወይም የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ማስፈጸም ባለመቻላቸው፣ ለደላላ ከ25,000 ብር እስከ 30,000 ብር እየከፈሉ እንደሚጓዙም ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተጓዦች ነኢማ ሡልጣንና ፈርዶሳ ካሊድ ገልጸዋል፡፡ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዋናነት ተጠያቂ መሆን አለበት የሚሉ ተጓዞቹ፣ የሌለ መሥፈርት በማስቀመጡ ሕገወጥ ጉዞው እንዲባባስ ማድረጉን ይናገራሉ፡፡ የቀለም ትምህርት የሌላቸው፣ ነገር ግን በዓረብ አገሮች ለበርካታ ዓመታት ቆይተው የተመለሱና የአገሩን ቋንቋና ባህል የለመዱትም መሥፈርት አሟሉ ሲባሉ፣ ምርጫቸው ሕገወጥ መንገድ ቢሆን እንደማይደንቅ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ሕጉን ማስፈጸም የሚጠበቅባቸው ተቋማት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ሠራተኛና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎችም ተባብረው ሕጉን ተግባራዊ ማድረግ እንዲኖርባቸውም ተናግረዋል፡፡

ዓረብ አገሮች ካሉ ኤጀንሲዎችና ሀብታሞች ጋር የሃይማኖት፣ የቋንቋና የጥቅም ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በርካታ ኤጀንሲዎችን በመክፈት ሥራውን በሞኖፖል ለመያዝ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ በመሆኑ፣ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠውና ሊከታተላቸው እንደሚገባም ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊ ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡ የመንግሥትን ኃላፊዎች በጥቅም ለመያዝና ሁሉንም የጉዞ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በመመሳጠር፣ በመደራጀትና ለአገር አሳቢ በመምሰል የፊታውራሪነት ቦታ ለማግኘት የሚሯሯጡትንም ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም አኳያ ትኩረት ሊደረግባቸው እንደሚገባ ኃላፊው አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...