ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሥልጣን ጊዜያቸውን ጨርሰውም ሆነ ሳይጨርሱ ከኃላፊነት የሚነሱ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአምባሳደርነት የሚሾሙበትን አሠራርና የፍትሐዊነት ችግር በተመለከተ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ተነሳ፡፡
ጥያቄው የተነሳው ሐሙስ ግንቦት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የመሥሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ሲያቀርቡ ነው፡፡ ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላ በፓርላማው የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበርካታ ጉዳዮች ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ በውጭ አገሮች በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች የሚመደቡ ዲፕሎማቶች ያላቸው ክህሎት፣ ዕውቀት፣ አሿሿምና ተሿሚ ዲፕሎማቶች የሚመደቡባቸውን አገሮች የጥቅም ግጭትና ፍትሐዊነትን በተመለከተ፣ የቋሚ ኮሚቴው አባል በሆኑት በአቶ ዘለቀ መሐሪ የቀረቡት ይገኙበታል፡፡
‹‹የአገራችን የዲፕሎማሲ ሥራዎች ከሚከናወኑባቸው መንገዶች አንዱ፣ ከአገር ጥቅም አኳያና ከስትራቴጂካዊ ወዳጅነት አንፃር በየአገሮች ሚሲዮኖች መክፈት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ለኤምባሲዎች የሚመደቡ አምባሳደሮች ወቅቱ ከሚጠይቀው የዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ አኳያ፣ የቢዝነስ ዲፕሎማሲውን ለማሳለጥና የአገሪቱን ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር፣ ባላቸው ብቃትና ክህሎት መሠረት አድርጎ መሾም ሲገባ፣ አንዳንዶቹ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶችን ሲመሩ ውጤታማነታቸው ጥያቄ ውስጥ የገባ ነበሩ፡፡ እነዚህን ተሿሚዎች ወይ በጡረታ መሸኘት፣ ወይም ሌላ ቦታ መመደብ ሲገባቸው በአምባሳርነት መመደቡ፣ በዲፕሎማሲ ሥራ የአገርን ጥቅምና ገጽታ ከማስቀደም አኳያ በብቃትና በልምድ ላይ ያልተመሠረተ ሹመት ለምን ያስፈልጋል?›› የሚሉ ጥያቄዎች ለሚኒስትሩ ቀርቦላቸዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባል የተሿሚ ዲፕሎማቶችን (አምባሳደሮችን) በስም ባይጠቅሱም፣ ባልና ሚስት በአንድ ሚሲዮን ስለመመደባቸውም ተጨማሪ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ለአብነትም በካናዳና በብራሰልስ (ቤልጂየም) የተመደቡ ዲፕሎማቶችን ማየት እንደሚቻል ጥያቄውን ያቀረቡት አቶ ዘለቀ፣ ወቅቱ ከሚጠይቀውና ከዲፕሎማሲ ውጤትና ከአዋጁ አንፃር እንዴት እንደሚታይ የሚኒስትሩን ማብራሪያ ጠይቀው ነበር፡፡
ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ ወርቅነህ (ዶ/ር)፣ የአምባሳደሮቹ ምድባ በትምህርትና በብቃት ላይ ተመሥርቶ ብቻ መሆን አለበት የሚለውን እንደሚቀበሉት ገልጸዋል፡፡ የአምባሳደርነት አመዳደቡ በሁለት ዓይነት መንገድ እንደሚከናወን ያስረዱት ሚኒስትሩ፣ አንደኛው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከታች እርከን ጀምሮ የሚያበቃቸውን ሠራተኞች በመምረጥ ሲሆን፣ ሌላው በመንግሥት ከተለያዩ ተቋማት ለሚመጡ ምደባ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን በነበረው አሠራርም ቢሆን በተመደቡ አምባሳደሮች የአገሪቱን ፍላጎት በማሳካት ረገድ የታየ ችግር አልነበረም ብለዋል፡፡
‹‹በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ተመድበው በአመራር ላይ የነበሩት ሚኒስትሮች ሆኑ ሌሎች ኃላፊዎች ለአምባሳደርነት ሲታጩ፣ በፊት የነበራቸውን ልምድና የአመራር ዕውቀት ይዘው ነው የሚመጡት፡፡ የአገሪቱን ፍላጎትና ጥቅም፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚያውቁ በመሆናቸው መጠነኛ ሥልጠና በመስጠት የሚመደቡበት አሠራር ያለ ሲሆን፣ የአገሪቱን ጥቅምና ፍላጎት በዲፕሎማሲው መስክ ሊያሳኩ እንደሚችሉ ስለሚታመንባቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡
ነገር ግን ይኼ አሠራር በምክር ቤቱ አባላት ብቻ ሳይሆን በሕዝቡም ውስጥ እየተነሳ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ወደፊት ግን በብቃትና በክህሎት ላይ ተመሥርቶ ግልጽ የሆነ የአሠራር መመርያ እንደሚያስፈልግና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሠራሩን ለማስፈጸም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በተሿሚ ዲፕሎማቶች ባልና ሚስት አመዳደብ ላይ የአድሎዓዊነት ጥያቄ ስለመኖሩና ሁለት ዲፕሎማቶች አንድ ቦታ ስለመመደባቸው በተመለከተ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ እንዳስረዱት፣ ሁለት ግለሰቦች በተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ሲያገለግሉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ምክር ቤቱ ይኼንን ጉዳይ በተመለከተ የሚነሱ ነገሮችን በግልጽ የማወቅ መብት ስላለው የሁለቱ ባልና ሚስት ማንነት እንዲገለጽ ሲጠይቁ፣ ወ/ሮ አስቴር ማሞ ከእነ ባለቤታቸው፣ እንዲሁም አቶ እውነቱ ብላታ ከእነ ባለቤታቸው መሆናቸውን በግልጽ አስረድተዋል፡፡ ወ/ሮ አስቴር በካናዳ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሲሆኑ፣ ባለቤታቸው እዚያው በዲፕሎማትነት ይሠራሉ፡፡ አቶ እውነቱ እንዲሁ በብራሰልስ በአምባሳደርነት ሲሾሙ፣ ባለቤታቸው እዚያ አብረዋቸው በዲፕሎማትነት እንደሚመሩ ተገልጿል፡፡
‹‹ወ/ሮ አስቴርም ሆኑ ባለቤታቸው በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልል ደረጃ (ኦሮሚያ) በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩ ናቸው፡፡ የካበተ ልምድ የነበራቸው መሆኑ በአምሳደርነት ከመመደባቸው በፊት የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱም አምባሳደሮች ከእነ ባለቤቶቻቸው አንድ ቦታ መመደባቸውን በተመለከተ ሲነሳ ለነበረው ጥያቄ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜም ጭምር ውሳኔ የተሰጠበት ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን አንድ ቦታ መሥራት አለባቸው ብለን አናምንም፡፡ ተገቢም አይደለም፡፡ አሁንም ቢሆን ማስተካከል አለብን፤›› ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ የሁለቱን ሰዎች ጉዳይ በተመለከተ ጥያቄው በሕዝቡም ውስጥ ያለ በመሆኑ ለወደፊቱ ተመሳሳይ ችግሮች ቢኖሩ እንኳ መፍትሔ መኖር ስላለበት፣ በቅርቡ ዕርምጃ በመውሰድ ይስተካከላል በማለት ለምክር ቤቱ ቃል ገብተዋል፡፡
ነገር ግን የሁለቱ ግለሰቦች ምደባ ሲካሄድ የተወሰነው በዝምድና እነሱን ለመጥቀም ታስቦ እንዳልነበር ገልጸው፣ ለወደፊቱ ማንኛውም ሚኒስትር የነበረ ሰው አምባሳደር ሆኖ የሚሾምበት አካሄድ ግልጽ በሆነ አሠራር ቀድሞ በነበረበት ኃላፊነት ያስመዘገበው ልምድና ችሎታ ተገምግሞ እንደሚሆን ጨምረው ገልጸዋል፡፡