Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየዳንጎቴ ሲሚንቶ ሥራ አስኪያጅና ሠራተኞች ገዳዮችን ለመያዝ ከፍተኛ አሰሳ እየተካሄደ ነው

  የዳንጎቴ ሲሚንቶ ሥራ አስኪያጅና ሠራተኞች ገዳዮችን ለመያዝ ከፍተኛ አሰሳ እየተካሄደ ነው

  ቀን:

  ሥራ አስኪያጁ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ደርሷቸው ነበር

  ረቡዕ ግንቦት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀኑ አሥር ሰዓት ላይ በጥይት ተደብድበው የተገደሉት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ጸሐፊና ሾፌር ገዳዮችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ከፍተኛ አሰሳ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

  በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን አዳበርጋ ወረዳ ሙገር ከተማ አቅራቢያ ከሚገኘው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስብሰባ ውለው በመመለስ ላይ የነበሩት ህንዳዊው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዲፕ ካማራ፣ ጸሐፊያቸው ወ/ሮ በአካል አለልኝና ሾፌራቸው አቶ ፀጋዬ ግደይ ባልታወቁ ታጣቂዎች በተከፈተባቸው የተኩስ ዕሩምታ ሕይወታቸው ወዲያውኑ አልፏል፡፡

  ከድርጅቱ ከባድ ተሽከርካሪዎች ሾፌሮች ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ ስለነበረ፣ ሚስተር ካማራ ቀኑን ሙሉ ከአሽከርካሪዎች ጋር ሲወያዩ እንደዋሉ ታውቋል፡፡ ከቀትር በኋላ ለአሥር ሰዓት አሥር ጉዳይ ሲል ሚስተር ካማራ ከጸሐፊያቸውና ከሾፌራቸው ጋር በኪራይ በሚጠቀሙበት ቶዮታ ላንድክሩዘር 105 መኪና ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀምረዋል፡፡ የዳንጎቴ ኢትዮጵያ የፀጥታ ጉዳይ ኃላፊ ንጉሤ ለማ (ጄኔራል) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሚስተር ካማራ ከግቢ ከመውጣታቸው በፊት አነጋግረዋቸው ነበር፡፡ ‹‹ከግቢ ከወጡ ከአሥር ደቂቃ በኋላ በስልክ ተደውሎ አሰቃቂ ዜና ተነገረኝ፤›› ብለዋል፡፡

  እንደ እሳቸው ገለጻ ወንጀሉ የተፈጸመው ከዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ጋትራነቤ በተባለ አነስተኛ መንደር ነው፡፡ ቤድሮክ የተሰኘ የሲሚንቶ ፋብሪካ በቅርቡ የሚገኝ ሲሆን፣ ጋትራነቤ የተባለው መንደር አቀበትና የግራና በቀኝ የባህር ዛፍ ጫካ የተሸፈነ በመሆኑ ጥቃቱን ለመፈጸም ሳይመረጥ እንዳልቀረ አስረድተዋል፡፡

  ሚስተር ካማራን ለሁለት ዓመት ያህል በሾፌርነት ያገለገለው አቶ ፀጋዬ ላንድክሩዘር መኪናውን እያሽከረከረ አቀበቱ ላይ ሲደርስ ሁለት ፊታቸውን የሸፈኑ ታጣቂዎች ከግራና ቀኝ ተኩስ እንደከፈቱበት የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ ሾፌሩ በጥይት ሲመታ መኪናው አቅጣጫ ስቶ ከመንገድ ዳር ምልክት (ማገጃ) ጋር ተላትሞ ቆሟል፡፡ በዚህም ጊዜ ታጣቂዎቹ ወደ ቆመው መኪና ተጠግተው በርካታ ጥይቶችን እንደተኮሱ እማኞች ተናግረዋል፡፡

  ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ፈጽመው ከአካባቢው በፍጥነት እንደተሰወሩና በሥፍራው የደረሱት የዳንጎቴ ሠራተኞችና የኦሮሚያ ፖሊስ ባልደረቦች የጥቃቱን ሰለባዎች ወደ ኢንጭኒ ከተማ ወስደዋቸዋል፡፡ የዚያኑ ዕለት ማምሻውን የሟቾች አስክሬን አዲስ አበባ ወደሚገኘው አቤት ሆስፒታል ተጓጉዟል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ በአካባቢው ሰፊ አሰሳ እያደረጉ እንደሆነ ጄኔራል ንጉሤ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  የተፈጸመው ግድያ የዘረፋ ወንጀል እንዳልሆነ የድርጅቱ ሠራተኞች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ድርጊቱ ከተፈጸመ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በሥፍራው የተገኙት የድርጅቱ ሠራተኞች በሚስተር ካማራ መኪና ውስጥ ላፕቶፕ፣ የሞባይል ስልኮች፣ ወርቆች፣ 8,000 ብርና መጠኑ ያልታወቀ የህንድ ገንዘብ (ሩፒ) መገኘቱ ድርጊቱ ከዘረፋ ጋር ግንኙነት እንደሌለው ያሳያል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

  በ2008 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሚስተር ዲፕ ካማራ የሠራተኛና አሠሪ ውዝግብ ተለይቷቸው እንደማያውቅ የድርጅቱ ሠራተኞች ይናገራሉ፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከድርጅቱ ሾፌሮች ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት በየዕለቱ ከጸሐፊያቸው ጋር ወደ ሲሚንቶ ፋብሪካው ይጓዙ ነበር፡፡ በየስድስት ወራት ወደ አገራቸው ለዕረፍት የሚሄዱት ሚስተር ካማራ በሚያዝያ ወር ዕረፍት መውጣት የነበረባቸው ቢሆንም፣ ከከባድ መኪና ሾፌሮች ጋር የተፈጠውን ችግር ሳልፈታ አልሄድም በማለት ማራዘማቸውን ባልደረባቸው ገልጸዋል፡፡

  ከሾፌሮቹ ጋር ከሞላ ጎደል ከስምምነት ላይ በመድረሳቸው ዓርብ ግንቦት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመጓዝ የአውሮፕላን ቲኬት ቆርጠው እንደነበር፣ የሥራ ባልደረባቸው እንባ እየተናነቃቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ግድያው የተፈጸመ ዕለት በጊዜ ከፋብሪካ የተነሱት አንዳንድ ስጦታዎች ለቤተሰቦቻቸው ለመግዛት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

  ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የነበሩት ሚስተር ዲፕ ካማራ አስከሬን ሐሙስ ግንቦት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ህንድ ተሸኝቷል፡፡ የዳንጎቴ ኢትዮጵያ የማኔጂመንት አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ዓሊ አብዶ፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሃላላና በርካታ የዳንጎቴ ኩባንያ ሠራተኞች አስከሬኑን ከአቤት ሆስፒታል እስከ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሸኝተዋል፡፡ የጸሐፊያቸው የወ/ሮ በአካል አለልኝ ሥርዓተ ቀብር ሐሙስ ግንቦት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በፈረንሳይ አቦ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ ወ/ሮ በአካል ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናት ነበሩ፡፡ በዩኒቲና በአድማስ ዩኒቨርሲቲዎች የአካውንቲንግ ትምህርት ያጠኑት ወ/ሮ በአካል በፀጉ ብርሃንና በሳሊኒ ኩባንያዎች ማገልገላቸውን፣ በሰኔ 2007 ዓ.ም. በዳንጎቴ ኢትዮጵያ በጸሐፊነት እንደተቀጠሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

  የሚስተር ዲፕ ካማራ ሾፌር አቶ ፀጋዬ ግደይ አስከሬን ቤተሰቦቹ ወደሚኖሩበት አዲግራት ከተማ ሐሙስ ግንቦት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ተሸኝቷል፡፡ አቶ ፀጋዬ ባለትዳር የነበረ ሲሆን፣ ለሁለት ዓመት ያህል ሚስተር ካማራን በቅንነት እንዳገለገለ የሥራ ጓደኞቹ በቁጭት ይናገራሉ፡፡

  ዳንጎቴ ሲሚንቶ አብዛኛውን ሥራ በኮንትራት ለኤጀንሲዎች የሚሰጥ በመሆኑ፣ በሠራተኞቹና በኤጀንሲዎች መካከል በየጊዜው ግጭት እንደሚፈጠር የድርጅቱ ሠራተኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  በጥሬ ዕቃነት የሚያገለግሉ ማዕድናት ምርት፣ የሲሚንቶ ማሸግና መጫን፣ እንዲሁም የትራንስፖርት ሥራዎች ኩባንያው በኮንትራት ለኤጀንሲዎች ይሰጣል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሾፌሮችና በኤጀንሲው መካከል የከረረ ውዝግብ ተፈጥሯል፡፡ ዳንጎቴ ሲሚንቶ 500 ያህል የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ሲኖሩት፣ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑት በአደጋ፣ በብልሽትና በሕዝባዊ አመፅ በደረሰባቸው ቃጠሎ ከሥራ ውጪ ሆነው ቆይተዋል፡፡

  በሾፌሮችና በኤጀንሲው መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ከሁለት ወራት በላይ የትራንስፖርት ክፍሉ ሥራ አቁሟል፡፡ ሲሚንቶና የከሰል ድንጋይ የሚመላለሰው በግል ትራንስፖርት ኩባንያዎች እንደሆነ ታውቋል፡፡ ቀደም ሲል የነበረው ኤጀንሲ የሥራ ውሉ ተቋርጦ አዲስ ኤጀንሲ መቀጠሩን የሚናገሩት የኩባንያው ሠራተኞች፣ አዲሱ ኤጀንሲ ለሾፌሮቹ የሚከፈለው ደመወዝ ከ5,500 ብር ወደ 2,500 መቀነሱን በመግለጹ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደቀሰቀሰ ገልጸዋል፡፡

  ‹‹ከቀድሞ ኤጀንሲ ወደ አዲስ ኤጀንሲ የሚደረገው ርክክብ ሒደት ሁለት ወራት ፈጅቷል፡፡ በዚህ ጊዜ አሽከርካሪዎቹ ደመወዝ የሚከፈላቸው ቢሆንም፣ አበል የማይከፈላቸው በመሆኑ ሆድ ብሷቸዋል፤›› ያሉት የድርጅቱ ሠራተኞች፣ 134 ሾፌሮች የሚያሽከረክሩት መኪና እንደሌላቸው በመግለጽ ከማኔጅመንቱ ጋር ከፍተኛ ተቃርኖ ውስጥ ገብተው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

  በኅዳር ወር 2010 ዓ.ም. የዳንጎቴ ሲሚንቶ የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ ህንዳዊው ሚስተር ዲሊፕ ሻክዋት በተበሳጩ ሾፌሮች በገዛ ቢሮዋቸው ውስጥ ተደብድበዋል፡፡ ድብደባ ከተፈጸመባቸው በኋላ ሚስተር ዲፕ ካማራ ሚስተር ዲሊፕ ሻክዋትን ወደ አዲስ አበባ በማምጣት፣ አዝማን ሆቴል ተቀምጠው ሥራቸውን በኢሜይልና በስልክ እንዲያከናውኑ አድርገዋል፡፡

  ሚስተር ዲፕ ካማራ በኤጀንሲውና በአሽከርካሪዎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለማብረድ ጣልቃ በመግባት ብዙ ጥረት እንዳደረጉ የሚናገሩት ባልደረቦቻቸው፣ በመጨረሻም ተሳክቶላቸው ከስምምነት ላይ እንደደረሱ አስረድተዋል፡፡

  ‹‹ሚስተር ዲፕ 2,500 ብር የተባለው ቀርቶ ቀድሞ ሲከፈላቸው እንደነበረው 5,500 ብር ደመወዝ እንደሚቀጥል ገልጸውላቸው ሾፌሮቹም ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሚስተር ዲፕ ካማራ የቅርብ የሥራ ባልደረባ ሚስተር ዲፕ ከመሞታቸው አንድ ሳምንት በፊት፣ የማስጠንቀቂያ መልዕክት በሞባይል ስልካቸው እንደደረሳቸው ገልጸዋል፡፡

  በግንቦት 2008 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሚስተር ዲፕ ካማራ ወደ ኢትዮጵያ የመጡበትን ሁለተኛ ዓመት በቅርቡ ከሥራ ባልደረባቻቸው ጋር እንዳከበሩ ተገልጿል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ሞዛምቢክ ውስጥ በማዕድን ኩባንያ ውስጥ በኃላፊነት ያገለግሉ እንደነበር ታውቋል፡፡

  በየጊዜው የሚፈጠሩ የሠራተኛና የአሠሪ ግጭቶችን ለመፍታት በማሰብ በ2010 ዓ.ም. የአዲስ ዓመት በዓል ዋዜማ ዳንጎቴ ኢትዮጵያ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ትልቅ ድግስ ደግሶ፣ የዕርቅ ፕሮግራም ማካሄዱን በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ከ2,000 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የድርጅቱ ሠራተኞች፣ የወረዳ አስተዳዳሪዎችና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ተወካዮች ታድመዋል፡፡

  በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ሚስተር ዲፕ ካማራ ማኔጅመንታቸው በሥራ ሒደት ላይ ለፈጸመው ስህተት ይቅርታ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀው ነበር፡፡ ‹‹በኦሮሞ ባህል መሠረት እንደ ጉዲፈቻ ልጃችሁ ተቀበሉኝ፤›› ሲሉ በጠየቁት መሠረት፣ የአገር ሽማግሌዎች ጥያቄያቸውን ተቀብለው መርቀው ‹‹ኦቦ ገለታ›› በማለት የኦሮሚኛ ስም አውጥተውላቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የትርፍ መጠኑን በ127 በመቶ ያሳደገው አቢሲኒያ ባንክ ካፒታሉን በ2.5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወሰነ

  የአቢሲኒያ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩ  ካፒታል በ2.5 ቢሊዮን ብር...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ያገኘው ፔይሊንክ አክሲዮን ማህበር ምሥረታውን አካሄደ

  ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው...