Tuesday, January 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ባንክ የአገልግሎት ዘርፉ ትኩረት እንዲሰጠው አሳሰበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአገልግሎት ዘርፉ በተለይም ለንግድ ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት፣ በስድስተኛው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የዓለም ባንክ ሪፖርት አሳሰበ፡፡ ባንኩ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው ረቡዕ ግንቦት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ነበር፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉንና የአገልግሎት ዘርፉን ግንኙነት ያጠናውን ሪፖርት ይፋ ያደረገው የዓለም ባንክ፣ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ቢሆንም፣ የአገልግሎት ዘርፉ ግን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ለኢኮኖሚውና ለአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ከፍተኛውን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡ ሪፖርቱ አክሎም፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ. ከ2016 እስከ 2017 በጀት ዓመት በ10.9 በመቶ ማደጉን አስታውቋል፡፡

ይሁንና ይህ ዕድገት ባለበት አገር ውስጥ እየታየ ያለው ዝቅተኛ የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) ዕድገት ተቀባይነት እንደሌለው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

‹‹የአገልግሎት ዘርፉ አፈጻጸም በአጠቃላይ የኢኮኖሚውን በተለይም የወጪ ንግድ ዘርፉን አፈጻጸም የሚያመላክት ነው፡፡ ይሁንና ዘመናዊ የአገልግሎት ዘርፎች እጅግ አነስተኛ በሚባል የዕድገት ደረጃ ላይ ይገኛሉ፤›› ሲል ሪፖርቱ አትቷል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አፈጻጸም እጅግ አነስተኛ እንደሆነ፣ በዓመት ከአሥር በመቶ በላይ በሆነ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት እያስመዘገበች ለምትገኝ አገር ሦስት ቢሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ በምንም ሁኔታ ተቀባይነት እንደሌለው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህ የኤክስፖርት ዘርፍ አፈጻጸም እጅግ አናሳ በመሆኑ የመበደር አቅማችንን እየጎዳው ስለመጣ፣ አሁን የግል ዘርፉን ይበልጥ ለማሳተፍ እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሆኖም የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግሥት ኢኮኖሚውን ይበልጥ እየደገፈ ላለው የአገልግሎት ዘርፍ፣ የበለጠ ድጋፍ እንዲያገኝ የሰጠውን አስተያየት ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበሉት ተናግረዋል፡፡

‹‹አሁን ዘለን ወደ አገልግሎት ዘርፉ አንገባም፡፡ ለዚህ ጊዜው ገና ነው፡፡ ኢንዱስትሪው ከሚሰጠን ምርታማነትን የማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ ክምችትና ቀጣይነት ያለው የወጪ ንግድ ዕድገት አኳያ ለኢትዮጵያ የማያወላዳ አቅጣጫ ሆኖ ይቀጥላል፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ሆኖም የኢንዱስትሪውን ዘርፍ እስከደገፈ ድረስ የአገልግሎት ዘርፉ ዕድገት የሚያስፈልግና ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላ በነበረው ውይይት ላይ የተሳተፉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር)፣ ‹‹አገልግሎት ዘርፉ ዕድገት እምብዛም ልንኮራበት የሚገባን አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሌላውን ዘርፍ ሀብት እየወሰደ ነውና ትርፍ የሚያገኘው፡፡ ዕድገቱም በፖሊሲ የተደገፈ እስካልሆነ ድረስ ጤናማ ነው ለማለትም አያስችልም፤›› ብለዋል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ግን የአገልግሎት ዘርፉ ማደጉ ሳይሆን የሚያሳስበው፣ ይህ ዕድገት ትኩረት እየተሰጠው ላለው አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዴት ድጋፍ ይስጥ የሚለው ነው ብለዋል፡፡

‹‹አሁን መሥራት ያለብን ይህ ዘርፍ እንዴት የአምራች ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ተወዳዳሪና ምርታማ ለማድረግ ይደግፈው የሚለው ላይ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ምንም እንኳን ዘርፉ በመንግሥት ድጋፍ ያልተደረገለት ቢሆንም፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አፈጻጸም የራሱን አስተዋጽኦ እንዳያበረክት ብዙ ተፅዕኖዎች ቢኖሩበትም፣ ባለፉት አሠርት ዓመታት የአገልግሎት ዘርፉ በተለይም የንግድ ዘርፉ በእጅጉ ማደጉን የዓለም ባንክ ሪፖርት አመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች