Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሶማሌላንድ በበርበራ ወደብ የምታካሂደውን የማስፋፊያ ግንባታ በመስከረም ወር እንደምትጀምር ታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ኢትዮጵያ 30 በመቶ የወጪና የገቢ ንግዷን በበርበራ በኩል እንደምታስተናግድ ይጠበቃል

ራሷን እንደቻለች ሉዓላዊት አገር ዕውቅና ለማግኘት በመጣጣር ላይ የምትገኘው ሶማሌላንድ፣ ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስን በባለድርሻነት ያካተተውን የበርበራ ወደብ የማስፋፊያ ግንባታ በመጪው መስከረም ወር እንደምትጀምር አስታወቀች፡፡

የበርበራ ወደብ የኦፕሬሽን ሥራዎችን የሚመሩ ኃላፊዎች ሰሞኑን በወደቡ ጉብኝት ላደረጉ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ወቅት እንደታስወቁት፣ በሰኔ ወር የወደብ ግንባታውን ለሚያካሂዱ ኩባንያዎች ሥራው እንደሚሰጣቸውና በመስከረም ወርም  ግንባታ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡

የበርበራ ወደብ የኦፕሬሽን ሥራዎች ኃላፊ ሚስተር ዓሊ ኢስማኢል መሐመድ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ስለፕሮጀክቱ በሰጡት ማብራሪያ መሠረት፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ የወደቡ የማስፋፊያ ግንባታ እ.ኤ.አ. በ2020 ይጠናቀቃል፡፡ 430 ሜትር ርዝመት ያለው አዲስ ወደብ ሲገነባ በአንድ ጊዜ ሦስት ትልልቅ መርከቦችን ያለ ችግር ማስተናገድ እንደሚችል ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ሁለተኛውን ምዕራፍ ጨምሮ በጠቅላላው 800 ሜትር ርዝመት የሚኖረው የአዲስ ወደብ ግንባታ ሥራው በጠቅላላው ከስድስት ያላነሱ መርከቦችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል፡፡ ነባሩ የበርበራ ወደብ በ650 ሜትር ዝርመት የተገነባ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ እስከ አምስት መርከቦችን እያስተናገደ እንደሚገኝ ተብራርቷል፡፡

የሚገነባው አዲስ ወደብ አሁን ያለውን 150 ሺሕ ባለ 20 እና ባለ 40 ጫማ ኮንቴይነሮችን የማስተናገድ አቅም ወደ አንድ ሚሊዮን የሚያሳድገው ሲሆን፣ ከብትን ጭነት በተጨማሪ የቀንድ ከብትና የተሽከርካሪ ጭነቶችንም በሰፊው የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል ተብሏል፡፡

በሶማሌላንድ የሳሂል ግዛት ዋና መዲና በሆነችውና ከዋና ከተማዋ ሐርጌሳ በ154 ኪሎ ሜትር ርቀር ላይ በምትገኘው በርበራ ከተማ ዳርቻ የሚገነባው ወደብ በሚጠናቀቅበት ወቅት፣ የኢትዮጵያን 30 በመቶ የገቢና የወጪ ዕቃዎች እንደሚያስተናግድ ከኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አሥር በመቶው ዕቃ በፖርት ሱዳን በኩል፣ ቀሪው 60 በመቶ በጂቡቲ በኩል እንዲስተናገድ ታቅዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ95 በመቶ ያላነሰው የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ዕቃ በጂቡቲ ወደብ በኩል እየተስተናገደ ይገኛል፡፡

የበርበራ ወደብ ማስፋፊያ በ442 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደሚገነባ ይፋ የተደረገው ከሁለት ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ. በ2016 እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የሶማሌላንድ መንግሥት ከዱባዩ ዲፒ ወርልድ ኩባንያ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት የሚደረግ ግንባታ ቢሆንም፣ በመሀሉ ኢትዮጵያ የወደቡን የ19 በመቶ ድርሻ በመያዝ በቅርቡ በተደረገ ስምምነት የወደቡ ባለድርሻ መሆኗ ይታወሳል፡፡

ይሁንና የኢትዮጵያ ድርሻ 19 በመቶ ነው ይባል እንጂ በገንዘብ ምን ያህል ኢንቨስት እንደምታደርግ ሲገለጽ አይደመጥም፡፡ ለዚህ ጉዳይ ማብራሪያ የተጠየቁት የማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ፣ ‹‹እንዲህ ያሉ ዝርዝር የስምምነቱ ጉዳዮችና የገንዘብ ድርሻ በመንግሥታቱ ደረጃ  የሚገለጹ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ የሚያገናኛትን የመንገድ ግንባታ ምንም እንኳ ከወደብ አገልግሎት አኳያ ዋና ጠቀሜታ ቢኖረውም፣ ከወደብ ልማት ሥራው ጋር እንደማይገናኝ፣ ይልቁንም መንግሥት ከያዘው የገቢና የወጪ ንግድ ኮሪደሮች ልማት ጋር እንደሚያያዝ ጠቅሰዋል፡፡ ሪፖርተር በስልክም በአጭር መልዕክትም ስለጉዳዩ ለማነጋገር የሞከራቸው ኃላፊዎች ምላሽ አልሰጡም፡፡

ሚስተር መሐመድ፣ አላን ሳንቼዝ ከተባሉት የፕሮጀክት ኦፕሬሽን ሥራዎች ኃላፊና ከምክትላቸው ሚስተር አብዲ አብዱላሂ ሐሰን ጋር በመሆን የበርበራ ወደብን ባስጎበኙበት ወቅት እንዳብራሩት፣ በሁለት ምዕራፎች ተከፋፍሎ ግንባታው የሚካሄደው የበርበራ ወደብ ከአጎራባች አገሮች ጋር ተፎካካሪ በመሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአካባቢው ተጠቃሚዎች አማራጭ ወደብ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በብዛት የኢትዮጵያ ዕቃዎች የሚስተናገዱበት የኮንቴይነር ማሳረፊያ ቦታ ውጫሌ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ በመጪው ነሐሴ ወር ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ሥርዓት የሚታገዝ የኮንቴይነር አገልግሎት እንደሚጀመርም አስረድተዋል፡፡

ከዱባይ፣ ከቻይና፣ ከግብፅ፣ ከህንድ፣ ከኦማንና ከሌሎችም አገሮች የሚመጡ ጭነቶችን የሚያስተናግደው የበርበራ ወደብ እ.ኤ.አ. በ2017 በተመድ የዓለም የምግብ ድርጀት በኩል ወደ ኢትዮጵያና ሌሎች አገሮች የተሠራጨውን 25 ሺሕ ቶን የዕርዳታ እህል ያስተናገደ ሲሆን፣ በዚህ ዓመትም 40 ሺሕ ቶን የዕርዳታ እህል ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ሚስተር መሐመድ ገልጸዋል፡፡

በሶማሌላንድ፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና በኢትዮጵያ የሦስትዮሽ ባለቤትነት በዲፒ ወርልድ ኩባንያ አማይነት የሚተዳደረው የበርበራ ወደብ የግንባታ ስምምነት ይፋ በተደረገበት ወቅት፣ የሶማሊያ መንግሥት ተቃውሞውን ከማሰማቱም በላይ ስምምነቱ ሉዓላዊነቴን ተጋፍቷል ሲል ውድቅ እንዳደረገው ይታወሳል፡፡ ጂቡቲም በበርበራ ወደብ ግንባታ ውስጥ ኢትዮጵያ መሳተፏ ብቻም ሳይሆን፣ 30 በመቶውን የገቢና የወጪ ጭነት ለሶማሌላንድ መስጠቷ እንዳስከፋት ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በወደብ ልማት በኩል በሶማሌላንድ ያደረገው ተሳትፎ የሞቃዲሾን ሉዓላዊነት እንደማይጋፋ በመግለጽ የሶማሊያን ክስ አስተባብሏል፡፡

በዲፒ ወርልድ ኩባንያ የ51 በመቶ ድርሻ፣ በሶማሌላንድ መንግሥት የ30 በመቶ ድርሻ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የ19 በመቶ ድርሻ የሚገነባው የበርበራ ወደብ፣ ለሶማሌላንድ የዕውቅና ይሰጠኝ ጥያቄ ተገቢነት ተጨማሪ የመከራከሪያ ነጠብ ለመሆን እንደበቃ የሚገልጹ አሉ፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት ሶማሌላንድ ራሷን የቻለች ሉዓላዊ አገር እንደሆነች በማወጅ መንግሥት ብትመሠርትም፣ በዓለም መንግሥታት ዘንድ ዕውቅና ሳይሰጣት ቆይታለች፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥቂት አገሮች የሶማሌላንድ ሚሲዮን እንዲቋቋም በማድረግ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መመሥረታቸው ይታወቃል፡፡

በየዓመቱ በምታካሂደው ብሔራዊ የነፃነት መታሰቢያ ክብረ በዓልም ይህንኑ የዕውቅና ጥያቄ በማውሳት ራሷን የቻለች አገር ተብላ ለመታወቅ የሚያበቃት ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ለማሳየት ትጥራለች፡፡ የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሰዓድ አሊ ሺሬ (ዶ/ር) ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታም ይህንኑ አንፀባርቀዋል፡፡ አገራቸው በእንግሊዝ ሞግዚትነት ሥር ከነበረችበት ጊዜ ቀደም ብሎም ቢሆን በጣሊያን ሥር ከነበረችው ሶማሊያ ጋር አንድ የሚያደርጋት ምንም ዓይነት ነገር እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡ ከምሥረታዋ ጀምሮም ሰባት ሕዝባዊ የምክክር መድረኮችን በማካሄድ ዕርቀ ሰላም እንዳወረደች፣ ሚሊሻዋን መሣሪያ እንዳስፈታችና በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምዘና ፍትሐዊና ገለልተኛ ምርጫዎችን በማካሄድ ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት ሥርዓት እንዳሰፈነች በመዘርዝር፣ ሉዓላዊ አገር ለመባል የሚያበቋትን መመዘኛዎች እንዳሟላች ሞግተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች