Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የብር ምንዛሪ ለውጥ የወጪ ንግዱን አሻሽሎታል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዓመት ዓመት አልሳካ ያለውን የወጪ ንግድ ለማሳደግ በማሰብ በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም. የተደረገው የብር የምንዛሪ ለውጥ፣ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ገቢ እንዳሻሻለው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

መንግሥት የብርን የመግዛት አቅም በ15 በመቶ መቀነሱ የሚታወስ ነው፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ የወጪ ንግድ ግኝት ከዕቅዱ አኳያ እምብዛም የተሳካ ባይሆንም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር መሻሻል እንዳሳየ ተናግረዋል፡፡

‹‹የብር ምንዛሪ ማሻሻያው የወጪ ንግድ ግኝት አምስት በመቶ የሚጠጋ መሻሻል እንዲያሳይ አድርጎታል፡፡ ይሁን እንጂ ከዕቅዱ አኳያ የጠበቅነውን ያህል ማሳካት አልቻልንም፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

በ2010 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም አገሪቱ ከወጪ ንግድ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን፣ ይህ አፈጻጸም ከዕቅዱ አንፃር በ1.5 ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ነው፡፡ ይሁንና ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ4.3 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

የዓለም ባንክ ረቡዕ ግንቦት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ሪፖርት፣ በምንዛሪ ለውጡ ምክንያት የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ግኝት እንዳደገ፣ ነገር ግን ይህ ጥቅም በዋጋ ግሽበት ምክንያት ወደታች መውረድ እንዳልቻለ አመልክቷል፡፡

ነገር ግን ሚኒስትሩ የዋጋ ግሽበት ከምንዛሪ ለውጡ ጋር አይገናኝም ይላሉ፡፡ ‹‹የዋጋ ግሽበት በዋናነት በአገሪቱ ተቀስቅሶ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እንጂ፣ ከውጭ ምንዛሪ ለውጡ ጋር የሚያያዝ ነገር የለውም፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ሚኒስትሩ እንደሚሉት የወርቅና የጫት ገቢ ባይቀንስ ኖሮ፣ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ በዘጠኝ በመቶ ሊያድግ ይችላል፡፡

በተደጋጋሚ መሳካት ባልቻለው የወጪ ንግድ ገቢ ግኝት ምክንያትም የአገሪቱ የመበደር አቅም እየተዳከመ ስለመጣ፣ የአጭር ጊዜ የክፍያ ጊዜና ከፍተኛ የወለድ ምጣኔ ያላቸውን ብድሮች ትታለች፡፡ በዚህ ምክንያት ገንዘብ ሊያጥራቸው የሚችሉ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ እንዲያስችል፣ መንግሥት ከግል ዘርፉ ባለሀብቶች ጋር በጥምረት ለመሥራት ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውስጥ ማቋቋሙን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ከፀደቀ አንድ ዓመት የሞላውን የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት የሚያትት ሕግ ለመተግበር የሚስችለው ይህ ዳይሬክቶሬት፣ ከግል ባለሀብቶች ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ለይቶ በቦርድ በማፀደቅ ለጨረታ አቅርቦ፣ ከአሸናፊዎች ጋር ፕሮጀክቶችን የማቀላጠፉን ሥራ ያከናውናል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች የመንገድ፣ የባቡርና የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች