Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትኮንትሮባንዲስቶቹ ይራገፉ!

ኮንትሮባንዲስቶቹ ይራገፉ!

ቀን:

በአሳምነው ጎርፉ

ሰሞኑን በተደራጀ መንገድ ኮንትሮባንድ ሲያጧጡፉ የነበሩ 13 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መንግሥት ነግሮናል፡፡ የሰዎቹ ማንነት በቀረበው ዜና ላይ ባይገለጽም፣ ተደራጅተው ኮንትሮባንድ የሚያካሂዱ አደገኛ ሰዎች መኖራቸው በራሱ ብዙ ይናገራል፡፡ ሰፊ ሥፍራዎችን በሚሸፍነው በዚህ አደገኛ ድርጊት ውስጥ እየተሳተፉ የነበሩ ግለሰቦች የተጠናከረ ኔትወርክ እንደነበራቸው ነው፡፡ የግለሰቦቹ ማንነት እስኪነገረን ድረስ የችግሩን ጥልቀትና ውስብስብነት አንስተን መነጋገር አለብን፡፡

ሌብነት የልማትና ዕድገት እንቅፋት መሆኑ ብቻ ሳይሆን በአገር ላይም ኢፍትሐዊነትን በማንገሥ፣ ሕዝብና መንግሥትን የሚያራርቅ ብሎም ግጭትና ትርምስን የሚጋብዝ እኩይ ድርጊት ነው፡፡ ይህን እውነት በእኛም አገር ባለፉት ሦስት ዓመታት በተጨባጭ ዓይተነዋል፡፡ በዚሁ መዘዝ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮችም እንኳን ዴሞክራሲ ለማፋጠን ይቅርና ከትርምስና ከእርስ በርስ መበላላት መውጣት እየተሳናቸው፣ ተፈጥሮ ያደለቻቸውን ዕምቅ ሀብት የበይ ተመልካች ሆነዋል፡፡ በዚህ ረገድ የአገራችን መንግሥትም አደጋውን ተገንዝቦ የተለያዩ የትግል ሥልቶችን በመንደፍ ለመረባረብ እየሞከርኩ ነው ቢልም፣ በየጊዜው ብልጭ ድርግም የሚል የጥገኝነት ዝንባሌ ግን ሊወገድ አልቻለም፡፡ አሁንም ገና ሸክሙ ያልተራገፈ ዕዳ ሆኖ አለ፡፡ በተለይ መንግሥት ውስጥ የተሰገሰጉ አደገኛ ኮንትሮባንዲስቶች ጉዳይ ብዙ አሳር ያሳያል፡፡

በማንኛውም አገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ለዕድገትና ለልማት የሚበጅ አንዳችም ፋይዳ ከሌላቸው የሌብነት መገለጫዎች አንዱ ደግሞ የታክስ   ማጭበርበር በተለይም የኮንትሮባንድ ንግድ ነው፡፡ ኮንትሮባንድ የማይገባበት ቦታና  የማያጠቃልለው ዕቃ/ሸቀጥ የለም፡፡ ሕግና ሥርዓት ከተጣሰ ብሎም የመልካም አስተዳዳር ሥርዓት መዳከም ከጀመረ፣ ሁሉም ነገር ፈሩን እየለቀቀ ኮንትሮባንድ ይሆናል፡፡ ለልማት ተሠልፏል የሚባለው ባለሀብትና የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ሁሉ እየተንሸራተተና  እየተሽቀነጠረ  ኮንትሮባንዲስትና የለየለት ጥገኛ መሆንም ይጀምራል፡፡ እንዲህ ያለው ችግር እንዲስፋፋ ደግሞ መንግሥታዊ መዋቅሩ፣ ማለትም ከፀጥታ ኃይሉ እስከ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ድረስ የሚፈጠር ብልሽትና መሞዳሞድ ትልቁን ሚና መጫወቱ አይቀርም፡፡ የሕዝቡም ዓይቶ እንዳላየ መሆንም መዘዝ እያስከተለ መምጣቱ የሚታወቅ ነው፡፡

‹ኮንትሮባንድ› የሚባለው ያለሕጋዊ የመግቢያና የመውጫ ሰነድ ታክስ ሳይከፈልበት ድንበር ጥሶ፣ ኬላ በጥሶ ከአገር አገር የሚዘዋወር፣ የሚገባና የሚወጣ ሕገወጥ ሸቀጥ በሙሉ ነው፡፡ ‹ኮንትሮባንድ› የሚለው ቃል በእንግሊዝኛ ቋንቋ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የተከሰተው እ.ኤ.አ. በ1529 ሲሆን፣ ከመካከለኛው ዘመን ፈረንሣይኛ ‹‹ኮንትሬባንዴ›› ከሚለው ቃል መንጭቶ ነው፡፡ ከላቲን ‹‹ኮንትራ›› (ከሕግ ተቃራኒ) ከሚለውና ሕገወጥነትን ከሚያመለክተው ቃል የመጣ ነው ሲል ግርማ ለማ የተባለ ጸሐፊ፣ በዘርፉ ላይ በካሄደው ጥናት ቀመስ ጽሑፍ ላይ ዳስሶት ተመልክቻለሁ፡፡

ከየትም ይምጣ ከየት በሕገወጥነቱ ላይ ከተስማማን የምንጩ የትነት ለተነሳንበት ጉዳይ ችግር አይፈጥርብንም፡፡ ዋናው ነገር ሕገወጥ ንግድ በማንኛውም መንገድ ጎጂ መሆኑ ነው ቁም ነገሩ፡፡ የአገርን ኢኮኖሚ ያናጋል፣ ማኅበራዊ ሕይወት ያቃውሳል፣ ባህል ያፈርሳል፣ የጤና ጉዳት ያስከትላል፣ ለሱስና ለብልግና ያጋልጣል፣ . . . ስለዚህ ሁሉም አገሮች ኮትሮባንድን (ሕገወጥ ንግድን) ይቃወማሉ፡፡ ለማቆምና ለማስቆም በተናጠልና በጋራ ይሠራሉ፡፡ ሠርተው የተሳካላቸው ድህነትን ማሸነፍና አገርን ማረጋጋት ሲችሉ፣ ያልሆነላቸው ግን ተዋርደውና ሥርዓት አልበኝነት ሞልቶባቸው ወደ ውድቀት አምርተዋል፡፡ የእኛም ዕጣ ፈንታ ይኼ እንዳይሆን አደጋውን ለመመከት መራር ትግል ያስፈልገናል፡፡

በእርግጥ በሦስተኛው ዓለም በኮንትሮባንድ ስም መንግሥት ከንግድ ዝውውሮች ለአገሪቱ ማስገኘት ያለበትን ጥቅም ሳያስገኝ፣ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ ዕቃዎች በጣም እየበዙ መምጣታቸው የተረጋጋጠ እየሆነ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሕጋዊ የሚባለው ንግድና የንግዱ ማኅበረሰብ እየተቃወሰ መጥቷል፡፡ በዋነኛነት የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የሞባይል ስልኮች፣ መለዋወጫዎች፣ ማሽነሪዎችና የተሽከርካሪ ዕቃዎች፣ ልባሽና አዲስ አልባሳት፣ . . . ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕፃናት ምግብና ወተት፣ . . . ሽቶና የቅባት ዘሮች፣ . . . መድኃኒቶች (ድርብርብ ጥፋትና አውዳሚ ኪሳራ እየተፈጸመበት ያለ ጉድ)፣ ሱስ አስያዥ ዕፆች፣ ወሲብ ነክ ፊልሞችና ቁሶች፣ ቦምብን ጨምሮ ድምፅ ያላቸውና የሌላቸው የጦር መሣሪያዎች፣ ወዘተ በሕገወጥ መንገድ ይገባሉ፡፡

በአገራችን በተለይ በምሥራቅ፣ በምዕራብና በደቡብ መግቢያ ከተሞችና የጠረፍ መንደሮች በገፍ የሚገቡ ለመሆናቸው ማረጋገጫው፣ መዲናችንን ጨምሮ በብዙዎቹ የመሀል አገሮች ከተሞች ኮንትሮባንድ ገበያውን እየሞላ መሆኑ ነው፡፡ የመንግሥት መዋቅር ተጠቅመው በዚህ ወንጀል ላይ የተሠማሩ ቀላል ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ከመበልፀጋቸውም ባሻገር፣ እስካሁንም ችግሩ አለ፡፡ ሕዝብ ሳይቀር በግልጽ እየተናገረው ያለው ኮንትሮባንዲስቱ የተደራጀና አስፈሪ መገለጫ ያለው መሆኑን ነው፡፡ በእንጭጩ ካልተቀጨም ለሥርዓቱ፣ ብሎም ለአገር ጠንቅ መሆኑም በተጨባጭ ታይቷል (አንዳንዱ ተላላ ደግሞ ከጥገኝነት የሚጠቀም እየመሰለው ለለየለት ዘራፊ ጠበቃ የመሆን ዝንባሌ ማሳየቱ አስገራሚ ነው)፡፡

በኮንትሮባንድ መንገድ ከአገር የሚወጡ ምርቶችም ብዙ ናቸው፡፡ በዋነኛነት ቡና፣ የቅባት እህሎችና ጥራጥሬ፣ የቁም ከብቶች (በግ፣ ፍየል፣ በሬ፣ ግመል፣ . . .) ሌላው ቀርቶ እኛ ከውጭ የምናመጣው ነዳጅ፣ ዘይት፣ ስኳርና የግንባታ ግብዓቶች አልፎም እንደ ወርቅ የሚናፍቀንን ዶላርና ዩሮ ጭምር በሕገወጥ መንገድ ይሻገራሉ፡፡ ብዙ ምርቶችም እዚህ እጥረት እያለብን በሕገወጥ መንገድ ከአገር ይወጣሉ፡፡ ኮንትሮባንዲስት ማለት ለማንም የማያዝን፣ ለምንም የማይመለስ ነፍሰ በላ ፍጡር ነው የሚባለው በንፋስ አመጣሽ ገንዘብ እየተሽሞነሞነ፣ የትኛውንም ወንጀልና ኢፍትሐዊ ድርጊት ለመፈጸም ከመድፈሩም በላይ፣ ሥርዓትን ወደ ከፍተኛ ብልሽት በመክተት አገርን የሚንድም በመሆኑ ነው፡፡

ለምሳሌ የሕፃናት ወተትን እንውሰድ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በታወቁትና በተመሰከረላቸው መለያዎች (ብራንዶች) የሚታወቁ ወተቶችን ምልክት በመጠቀም፣ ጊዜው ያለፈባቸው ከሌሎች ካልታወቁ ነገሮች ጋር የተደባለቁ ወተቶችን የሚያስገቡት ኮንትሮባንዲስቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ወተቶች በጉምሩክ ጣቢያዎች ሳይታዩና ሳይፈተሹ ተገቢው ቀረጥ ሳይከፈልባቸው የሚገቡ በመሆናቸው፣ ሕፃናቶቻችን ለጤንነትና ለሕይወት ጉዳት ይዳረጋሉ፡፡ ልጆች ይታመማሉ፣ ወላጆች ይሰቃያሉ፡፡ ይህ ሁሉ በሕገወጦች ምክንያት የሚመጣ ነው (ይኼንን በአንድ ወቅት በጋላፊ፣ በአዳማና በአዲስ አበባ ዳርቻ ወረዳዎች በድብቅ መጋዘኖች ምን ሲሠራ እንደነበር ተመልክቻለሁ)፡፡ በዚህ የተነሳ ቤተሰብ ለሕክምና የሚያወጣውን ወጪ አስቡት፡፡ ለሌሎች ታካሚዎች ሊውሉ የሚችሉ መታከሚያዎች በሕገወጥ ምግብና ወተት ለተጐዱ ሕፃናት ሲውሉ፣ የሚያስከትለውን አገራዊ ጉዳት ማመዛዘን አያዳግትም፡፡ ይህን አደጋ በሚዲያና በተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ለማውገዝ ቢሞከርም፣ በቂ ክትትልና ቅጣት ካላጀበው ተገቢው ውጤት ላለመገኘቱ አሁንም የችግሩ ሰለባ የሆኑ ዜጎች ቁጥር ትንሽ ላለመሆኑ አመላካች ነው፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን በኮንትሮባንድ የሚገቡ መድኃኒቶች ጊዜው ያለፈባቸውና በመድኃኒት አስተዳደር ባለሙያዎች በተደነገገው መሥፈርት መሠረት ያልተመረቱ ናቸው፡፡ በቅርቡ ታዋቂ የሆኑ አርቲስቶች፣ ባለሀብቶችና አትሌቶች በመድኃኒት ችግርና በሕክምና ስህተት ሕይወታቸው ሲያልፍ ሰማን እንጂ፣ በየቤቱ በተመሳሳይ ችግር የሺዎች ሕይወት እየተቀጠፈ የሚገኝበት ዋነኛው መዘዝ ይኼው እየሆነ ነው፡፡ መርካቶን ጨምሮ በመዲናችን ዳርቻ ቀበሌዎች በድብቅ በተዘጋጁ መጋዘኖች ጊዜ ያለፈባቸውን መድኃኒቶች ስያሜና የመጠቀሚያ ጊዜ እንደ አዲስ ሕጋዊ በማስመሰል ተቀይሮ እየተለጠፈባቸው፣ ኢሞራላዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆናቸው ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ እነዚህ ሁሉ አገራዊ ጥቃቶች ከኢኮኖሚያዊ መዘዛቸው በላይ በተጠቃሚዎቹ ላይ የሚያደርሱትን የጤና ጉዳት መገመት አይከብድም፡፡ በዚህ ዓይነት ምንም በማያውቁ ጨቅላ ሕፃናትና በሕመም በሚሰቃዩ ዜጐች ላይ ሳይቀር ይህን ያህል ጭካኔ የሚፈጽም ኮንትሮባንዲስት ለማን ሊመለስ ይችላል? አስገራሚው ነገር ደግሞ ይህን ችግር መንግሥት ለምን መንጥሮ መለየት ተሳነው? የሚል የህሊና ጥያቄ ሲቀሰቀስ ነው፡፡

በእርግጥ ኮንትሮባንድ በዜጎች በተለይ በሕፃናት፣ ለጋ ወጣቶች፣ ሴቶችና በግል ባለሀብቶች ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ በአገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ከፍተኛ ተግዳሮት አለ፡፡ ለምሳሌ ሕገወጥ ነጋዴዎች ለሚያስገቡትም ሆነ ለሚያስወጡት ዕቃ ታክስ አይከፍሉም፡፡ ከታክስ የሚገኘው ገቢ ካልተከፈለ የአገሪቱ ገቢ ያሽቆለቁላል፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥት ለሕዝቡ ሊሠራቸው የያዛቸውን ፕሮጀክቶች ለማስፈጸም የገንዘብ ችግር ያጋጥመዋል፡፡ ልማቱም ሆነ ዕድገቱ በታለመለት ጊዜ አይደርስም፡፡ እነዚህን የልማት ወጪዎች ለመሸፈን መንግሥት ከውስጥና ከውጭ ለመበደር ይገደዳል፡፡ እልፍ ሲልም ሕጋዊውን ነጋዴና አነስተኛ ባለሀብት ሁሉ በሚያማርር ደረጃ ግብር እየጣለ ወደ ማስለቀስ የመግባት ዝንባሌ ይታያል፡፡ ይህ ሁሉ ሕገወጦች ታክስ ባለመክፈላቸው የመጣ ጉዳት ነው፡፡

በሕገወጥ መንገድ ከአገር የሚወጡ ምርቶችም ተመሳሳይ ወይም የባሰ ጉዳት የሚያስከትሉብን ናቸው፡፡ ቢሊዮን ዶላሮች የውጭ ምንዛሪ ልናገኝባቸው የምንችላቸው ምርቶች ለምሳሌ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ የቁም ከብቶች፣ ጥራጥሬ፣ ቆዳና ሌጦ የመሳሰሉት በኮንትሮባንድ የሚወጡ ከሆነ አገር ማግኘት ያለባትን ከፍተኛ ገቢ ታጣለች፡፡ ይህ ሥጋት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻል እያሳየ መምጣቱ እርግጥ ቢሆንም፣ ምንም ያልነበራቸው ጥቂቶች እንዴት በጥገኝነት መንገድ ሰማይ መንካት እንደቻሉ የምናውቀው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የአገር የኢኮኖሚ ዕድገት ይጎዳል፡፡ ለዜጐች ሥራ የመፍጠር ጥረት ይጓተታል፡፡ ለሰላምና ለደኅንነት ብቻ ሳይሆን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም ምቹ ያልሆነ ተግዳሮት እያቆጠቆጠም መምጣቱ አይቀርም፡፡

የኮንትሮባንድ ነጋዴ ግብ በዋነኛነት ለመንግሥት መክፈል ያለበትን ታክስ ሳይከፍል በነፃ በመጠቀም፣ የገበያ ተወዳዳሪነትን መርህና የአገሪቱን ሕግ በመጣስ ትርፍ ማጋበስ ነው፡፡ ባልተገባ መንገድም ቢሆን ብቻዬን ልጠቀም የሚል ስግብግብነትና ማን ይነካኛል የሚል መታበይ የሚወልደው የጥገኝነት ጎዳናም ነው፡፡ ይኼ ነገር ዋነኛ የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል ፀረ መሆኑን በአገራችን ቢያንስ ባለፉት አሥር ዓመታት እያቆጠቆጠ እንደመጣ በግልጽ ዓይተነዋል፡፡ ኮንትሮባንዲስቱ ዋነኛ ሥራው የፍተሻ ኬላዎችን ጥሶ በማለፍ፣ ዕቃውና ሰነዱ እንዳይመሳከር በማድረግ ከተጠያቂነት ማምለጥ ነው፡፡ የፍተሻ ኬላዎች ተግባር የሚገቡና የሚወጡ ዕቃዎች በሕጉ መሠረት የተሟላ ሰነድ ያላቸው እንደሆነ፣ የተጫኑትም በሕግ አግባብ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ ነገር ግን ኬላ ላይ ያሉት የሚያሳልፉት በጥቅም፣ በሽርክናና በአድርባይነት እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ ይኼን ክፉ ድርጊት መቀየር ወቅታዊው ወሳኝ ተግባር መሆን አለበት፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ እንደታየው በእነዚህ ኮንትሮባንዲስቶች ካባ ሥር ሆነው ሕገወጥ የጦር መሣሪያ በማስገባት ላይ የተሠማሩት ደግሞ በአገሪቱ ሰላም እንዳይኖር፣ ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲጋጭ ጦር እንዲማዘዝ ሲያደርጉ መታየታቸው አልቀረም፡፡ እዚህ ላይ መንግሥት ራሱ እንዳረጋጋጠው በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች የተፈጠረው ግጭት መዘዝ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች ጠረፋማ ዞኖች የታየው ዝንባሌም ውስጥ እነዚህ ችግሮች እንደ መንስዔ ተወስደዋል፡፡ ይህ ክስተትም የችግሩን ተደራራቢ ጉዳት አመላካች ነው፡፡

በአገራችን ለኮንትሮባንድ መስፋፋት ምክንያት የሆነው ዋናው ጉዳይ ግን፣ ሸማቹ በኮንትሮባንድ የገቡ ዕቃዎችን ለመግዛት የሚያሳየው ፍላጐትም እንደሆነ መታየት አለበት፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በሕገወጥ መንገድ ታክስ ሳይከፈልባቸው የገቡ በመሆናቸው ዋጋቸው ዝቅተኛ በመሆኑ፣ እንዲሁም የሕዝቡም የመግዛት አቅም መዳከም የሚያግዝ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ሕጋዊ ነጋዴውን አያበረታታም፡፡ ታክስ ከፋዩ ነጋዴ በሕገወጥ ነጋዴዎች የሚበለጥበት ሁኔታ ስለመኖሩም መርካቶ ብቻ አመላካች ነው፡፡ መንግሥትና ሕዝብ መራር ትግል ማድረግ ያለባቸው ግን፣ መንግሥታዊ መዋቅሩን መንጠላጠያ አድርጎ እየበዘበዘ ያለውን ከየትኛውም ብሔር፣ ፆታና መደብ ኃይል ጋር ሊሆን ይገባል፡፡  

ከእነዚህ እውነታዎች አንፃር የታክስ ከፋዩን አምራችና ነጋዴ መብት ለማስከበር መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡና አደረጃጃቶች የኮንትሮባንድን እንቅስቃሴ ለመግታት መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡ በእርግጥ ሥራው የመንግሥት ተቋማት የተቀናጀ ጥረትና ኃላፊነትን በጉልህ ይጠይቃል፡፡ ተግባሩ በዋናነት በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በኩል እየተከናወነ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች የሚገቡትም ሆነ የሚወጡት በበርካታ የአገሪቱ የድንበር አካባቢዎች እንደ መሆኑ የፖሊስና የመከላከያ ኃይሉ፣ በየአካባቢው ያሉ የአስተዳዳር አካላት፣ እንዲሁም የፍትሕ አካላት የተቀናጀ ጠንካራ ሥራ ማከናወን አለባቸው፡፡ ለዚህ ግን አፍ ከልብ የሆነ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊኖር ይገባል፡፡ ስለሆነም ከተሃድሶው አመራርና ከጠቅላይ ሚኒስትር ከዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ካቢኔ የሚጠበቅ ቀዳሚ ሥራም መሆን አለበት፡፡

ኮንትሮባንዲስቶች ድንበር የሚያሻግርላቸውና በፍተሻ ወቅት የሚተባበራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ያመጡትን ሕገወጥ ዕቃ የሚረከቡና በመጋዘን የሚያኖሩላቸው፣ የሚያከፋፍሉላቸውና የሚሸጡላቸው ደንበኞችም አሉዋቸው፡፡ የሚያጓጉዙላቸው ፈጣን መኪኖችና ደፋር አሽከርካሪዎችም አይታጡም፡፡ ይኼንን ሰንሰለት መበጣጣስ ነው አሁን የሚያስፈልገው፡፡ በእርግጥ ሕገወጦቹ የሚንቀሳቀሱት በሕዝቡ ውስጥ ተሸሽገው ስለሆነ፣ መንግሥትም በሕዝቡ በኩል ክትትሉን ማድረጉ እንደተጠበቀ፣ ሆኖ እኛም እንደ ዜጋ በርትተን መታገል አለብን፡፡ ሕዝቡ ስለሕገወጥ ነጋዴዎች ጥቆማ እንዲያደርግ የማበረታቻ ሥልቶችን ማጠናከርም ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሚጠበቅ ቀዳሚ ሥራ መሆን አለበት፡፡ በተለይ ተቋማዊ በሽታን ፈትሾ በማጥራት፡፡

እስካሁን በአገራችን ፈጣን ዕድገት ውስጥ ኮንትሮባንድ ይኼን ያህል ጉልበት ሲያወጣ ‹‹ሃይ›› የሚባልበት ሕግ የለም ወይ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ግልጽ ሆኖ የተቀመጠ ሕግ አለ፡፡ አዋጅ አለ፡፡ የበፊቱ አዋጅ ቁጥር 622/2001 ይባላል፡፡ ከባድ አንቀጾችን የያዘ ሕግ ነበር፡፡ በኋላም እጅግ በጣም ግልጽ የሆነውና በመመርያ ብዛት ለአፈጻጸም ችግር የነበረበትን አዋጅ ያሻሻለ ሌላ አዋጅ ወጣ፡፡ ከዓመታት በፊት በቅርቡ (ኅዳር 30 ቀን 2007 ዓ.ም.) የወጣው የጉምሩክ አዋጅም ቁጥር 859/2007 ይባላል፡፡ በዚህ አዋጅ መምጣት የበፊቱ አዋጅ 622/2007 የተሻረ ቢሆንም፣ ባለፉት ዓመታት ሲሠራበት የቆየ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ አዋጆቹን መሠረት አድርገን ስናየው ኮንትሮባንድ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡ ያለጥርጥር ድርጊቱን ያባባሰው ግን በሥልጣን መባለግ ምክንያት እንደ ሰደድ እሳት የተስፋፋው ሌብነት፣ የመልካም አስተዳዳር መዳከምና የሕግ የበላይነት በወሬ የመቅረት ችግር መሆኑን ተገዝቦ መቅረፍ አለመቻሉ ነው፡፡ የመንግሥትና የሥርዓቱ ሁነኛ መዳከም ምልክት እንደነበር ተገንዝቦ ሥር ነቀል ለውጥ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡

በኮንትሮባንድ የተገኘ ዕቃ (ንብረት) ይወረሳል፡፡ መንግሥት ሊያገኝ ሲገባው ያጣውን ታክስና ቀረጥ መጠን ይከፈላል፡፡ የረዥም ዓመታት እስራትም አለበት፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ሕጐችን ተላልፎ ሕገወጥ መሆኑን እያወቀ ወይም ሊያውቅ ሲገባው ቀረጥና ታክስ ሳይከፍል ያስገባ፣ ያስወጣ፣ የተቀበለ፣ ያጓጓዘ፣ በድብቅ ያከማቸ፣ ያስተላለፈ፣ የሸጠ፣ የገዛ ከባድ ቅጣት ያገኘዋል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ወንጀሉ የተሠራው በተደራጁ ቡድኖችና በኃይል ከሆነ ደግሞ የእስራቱ መጠን በጣም የከበደ ይሆናል፡፡ ይህ ቢሆንም ግን ከወንጀሉ አንፃር የሚቀጡት እጅግ ጥቂት ለምን ሆኑ የሚለው ጥያቄ ሊፈተሽ ይገባዋል፡፡ አብዛኛው በተደራጀ መንገድ አገር የሚቦጠቡጥ ሆኖ  መቆየቱስ ለምን ይሆን ማለትም ተገቢ ነው፡፡ ይህን እንዴት እንሻገር ነው ወቅታዊ ጥያቄ መሆን ያለበት፡፡

በአጠቃላይ ኮንትሮባንድ ከፍተኛ አገራዊ ጉዳት የሚያስከትል፣ አገሪቱ የምታደርገውን ፀረ ድህነት ትግል የሚያደናቅፍ፣ የኢኮኖሚ ዕድገቷን የሚገዳዳር፣ ፍትሐዊ የሀብት ከፍፍልን የሚጎዳና ዜጎችንም የሚያስቆጣ (በተለይ ባለፉት ዓመታት እንደታየው)፣ በሕፃናትና በታማሚዎች ላይ የጤና ጠንቅ የሚፈጥር፣ ባህልን የሚያበላሽ፣ በሱስ አስያዥ ዕፆች የወጣቱን ራዕይና ተስፋ የሚያመክን . . . ወዘተ መሆኑ እየታወቀ፣ ፀረ ኮንትሮባንድ ትግሉን አጠናክሮ ከማስቀጠል ውጪ አማራጭ የለንም፡፡ ሕዝብና መንግሥት ተቀናጅተው ይህን አደጋ የመፋለም ጉዳይም ለነገ መባል ያለበት ተግባር መሆን የለበትም፡፡ ስለሆነም ትግሉ መጠናከርና ኮንትሮባንዲስቱን ማሳፈር ያስፈልጋል፣ ይገባልም፡፡ ሰሞኑን በቁጥጥር ሥር ዋሉ የተባሉት ኮንትሮባንዲስቶችም ሆኑ ኔትወርካቸው በግልጽ ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለበት፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ተግባራዊ እየሆነ መሆኑ በይፋ ይረጋገጥ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...