Sunday, May 26, 2024

የግብፅ የፍርኃት ፖለቲካና ታላቁ የህዳሴ ግድብ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ስቶኮልም ዓለም አቀፍ የውኃ ኢንስቲትዩት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ፣ ለምሥራቅ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አገሮች ያዘጋጀውን ዓውደ ጥናት እንዲካፈሉ ከተጋበዙ የኢትዮጵያ የሚዲያ ተቋማት መካከል ሪፖርተር አንዱ ነበር፡፡

ለዚህ ዓውደ ጥናት ሰኞ ሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ማለዳ በካይሮ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሰው ስድስት አባላት ያሉት የኢትዮጵያ የጋዜጠኞች ቡድን፣ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ከአውሮፕላን ማረፊያው መውጣት አልቻለም ነበር፡፡

ጋዜጠኞቹ ከአውሮፕላን ማረፊያ ለመውጣት የተቸገሩበት ምክንያት በአንድ ጉዞ ወደ ግብፅ ለመግባት የሞከሩ ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው እንጂ፣ ወደ ካይሮ ከተማ ለመግባት ያላሟሉት ነገር ኖሮ አይደለም፡፡

የአውሮፕላን ማረፊያው የኤሚግሬሽን ሠራተኞች ለተወሰኑ ደቂቃዎች ጋዜጠኞቹን በአውሮፕላን ማረፊያው ያቆዩበት ምክንያት፣ ለኃላፊዎቻቸው እስኪያሳውቁ ነበር፡፡ ፈቃድ ከተገኘ በኋላ የጋዜጠኞቹ ቡድን ከካይሮ ወደ ሜድትራኒያን ከተማ አሌክሳንዶርያ ተጉዟል፡፡

በአሌክሳንዶርያ ከተማ በነበረው የአምስት ቀናት ቆይታ፣ ከተለያዩ የከተማዋ ነዋሪዎች ለመረዳት የተቻለው ተመሳሳይ በፍርኃት የተቃኘ አቀባበል ነበር፡፡

ጋዜጠኞች በተዘዋወሩባቸው የተለያዩ መደብሮች ከየት እንደመጡ የተረዱ ግብፃውያን በተሰባበረ እንግሊዝኛ “You Problem” ይላሉ፡፡ በምላሹ ምክንያቱን ሲጠየቁ “Big Dam” በማለት ይመልሳሉ፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ያላቸውን ሥጋት ሲናገሩ ነው፡፡

የግብፅ የፍርኃት ፖለቲካና ታላቁ የህዳሴ ግድብ

 

ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳንና ከደቡብ ሱዳን እንዲሁም ከግብፅ በህዳሴ ግድቡና በናይል ወንዝ ላይ ዓውደ ጥናት በማዘጋጀት ጋዜጠኞችን የጋበዘው ስቶኮልም ዓለም አቀፍ የውኃ ኢንስቲትዩት፣ የጋዜጠኞች ቡድኑ የአስዋን ግድብን ለማስጎብኘት ፕሮግራም ይዞ የነበረ ቢሆንም የግብፅ መንግሥት አለመፍቀዱን ከኢንስቲትዩቱ የሥራ ኃላፊዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች ከግብፅ ጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ውይይት ከተረዷቸው ጉዳዮች መካከል፣ እያንዳንዱ ግብፃዊ ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ስለዓባይ በመደበኛ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ይማራል፡፡ ነገር ግን አመዛኙ ግብፃዊ ወደ አገሩ የሚገባው የዓባይ ውኃ የሚነሳው ወይም የሚመነጨው ከኢትዮጵያ እንደሆነ መረጃ የለውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በግብፃውያን ዘንድ የዓባይ ውኃ ከማኅበራዊ ሕይወት ጋር በእጅጉ እንዲቆራኝ ተደርጓል፡፡ በየዓመቱ ነሐሴ ወር ላይ የናይል (ዓባይ) ቀን ይከበራል፡፡

ፋዩብ በተባለው የግብፅ ገጠራማ አካባቢ ጋዜጠኞች ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ በአካባቢው በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ገበሬዎች የዓባይ ውኃ መጠን ከ15 ዓመታት ወዲህ የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱን ይናገራሉ፡፡ የአካባቢው ባለሥልጣናት በበኩላቸው የውኃ መጠን ቅናሹ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተከሰተ መሆኑን ቢረዱም፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት ይህንን ሁኔታ እንደሚያባብሰው ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ማብራሪያ ሳይሰጡ ያስረዳሉ፡፡

በዓውደ ጥናቱ “Impacts of water Security and Livelihoods Including forced migration” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት ግብፃዊ ተመራማሪ፣ ለግብፅ የሚደርሳት የውኃ መጠን መቀነስ ግብፃውያንን ለስደት እንደሚዳርግ ተናግረዋል፡፡

በከባቢው የአየር ለውጥና የአካባቢ መጎሳቆል የተነሳ ወደ ግብፅ የሚደርሰው የውኃ መጠን በአሁኑ ወቅት መጠነኛ ቅናሽ ማሳየቱን የተናገሩት ተመራማሪው ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ሁለት ሚሊዮን ግብፃውያን ወደ አውሮፓ አገሮች እንደሚሰደዱ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በህዳሴው ግድብ ፖለቲካ የዶክትሬት መመረቂያ ጥናታቸውን በማገባደድ ላይ የሚገኙ አንድ ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ፣ የስደት ጉዳይ አዲስ የግብፅ የፍርኃት ፖለቲካ ትርዒት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ አገሮች ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ የሚገቡ ስደተኞች ጉዳይ ራስ ምታታቸው እንደሆነ የሚረዱት የግብፅ ፖለቲከኞች፣ ወደ አውሮፓ ለመግባት የድንበራቸው አካል የሆነውን ሜዲትራኒያን ባህር ማቋረጡ ብቻ ለግብፃውያን በቂ እንደሆነ በመተረክ፣ የአውሮፓ ኃያላን በፍርኃት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጥሩ የተጠነሰሰ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በዚህ ዓውደ ጥናት ላይ ጥናታቸውን ያቀረቡት ደግሞ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ኬቨን ዊለር (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ኬቨን ዊለር “Cooperative filling approaches for the Grand Ethiopian Renaissance Dam” በሚል ርዕስ ባቀረቡት የምርምር ሥራቸው ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በተባበረ ስምምነት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በውኃ የሚሞሉ ከሆነ፣ ግድቡ በግብፅ ላይም ሆነ በሱዳን ላይ ጉልህ ጉዳት እንደማያደርስ አስረድተዋል፡፡

‹‹በቴክኒክ ረገድ ካየነው ኢትዮጵያ ግድቡን በሦስት ዓመት ውስጥ መሙላት ትችላለች፤›› የሚሉት ዊለር፣ ‹‹ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ግድቡን በፍጥነት በመሙላት በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉዳት ማድረስ እንደማይፈልግ በተደጋጋሚ ይፋ ማድረጉ መልካም ነገር ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሱዳን የሚገኙ ግድቦችና የመስኖ መስመሮች ከፍተኛ ደለል የሚሞላቸው በመሆኑ፣ ሱዳን ደለሉን ለመጥረግ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን እንደምታወጣ ይናገራሉ፡፡ ለአብነትም ከጋዛር የመስኖ ቦይ ደለል ለማስወገድ ሱዳን በየዓመቱ አሥር ሚሊዮን ዶላር እንደምታወጣ ጠቁመዋል፡፡

የሱዳን ሮዛሬስ ግድብ ውኃ ማጠራቀሚያ ግድብ (Reservoir) በደለል ምክንያት ውኃ የማጠራቀም አቅሙ 34 በመቶ መቀነሱን ተመራማሪው ያስረዳሉ፡፡

የህዳሴው ግድብ መገንባት ግን ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳንና ወደ ግብፅ ተጠርጎ የሚሄደው ደለል 86 በመቶ በማስቀረት፣ የሁለቱም አገሮች ግድቦች በሙሉ አቅማቸው እንዲሠሩ ዕድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል፡፡

ዓመቱን ሙሉ ማለትም ዝናባማ ያልሆኑ ወቅቶችን ጨምሮ ከፍተኛ የውኃ መጠን ወደ ታችኛው የተፋሰሱ አገሮች አመጣጥኖ በመላክ ረገድ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡

ዋናው ነገር ሦስቱ አገሮች በፍጥነት ወደ ትብብር መምጣታቸው እንደሆነ፣ ትብብርና መተማመንን ለመፍጠር ደግሞ ተዓማኒነት ያለው መረጃ ሦስቱም አገሮች እርስ በርስ መጋራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

የህዳሴውን ግድብ አሞላል በተመለከተ ሦስቱ አገሮች በጋራ የቀጠሩት የፈረንሣይ ኩባንያ ቢአርኤል የጥናት ሥራውን እስካሁን ለመጀመር አልቻለም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አማካሪ ድርጅቱ ጥናቱን ለመጀመር ባቀረበው የሥራ መፈጸሚያ መመርያ ላይ ኢትዮጵያና ሱዳን ያቀረቡት ቅሬታ አንዱ ነው፡፡

በዚህ የጥናት መፈጸሚያ መመርያ ላይ ለጥናት ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎች መነሻ ዓመት፣ እ.ኤ.አ. በ1959 በግብፅና ሱዳን የዓባይ ውኃን ለመከፋፈል የተፈራረሙት ውል እንዲሆን ቀርቧል፡፡

ኢትዮጵያ የዚህ ውል አካል ባለመሆኗ እንደማትቀበል በመግለጿ ለመረጃ ግብዓት መነሻ የሚሆነው ዓመት ላይ መግባባት አልቻሉም፡፡

ኬቨን ዊለር እንደሚሉት የህዳሴው ግድብ ከፍተኛ የውኃ መጠን ለሱዳን ያስገኛል፡፡ ነገር ግን ይህንን የውኃ መጠንን በመጠቀም የግብርና ተግባሯን ለማስፋፋት እ.ኤ.አ. የ1959 ስምምነት ሊገድባት እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴ ላለፉት ሁለት ዓመታት የህዳሴው ግድብ አሞላልን በተመለከተ የሚጠናውን ጥናት ለማስጀመር ሲያደርጉት የነበረው ድርድር ሲቋረጥና እንደገና ሲቀጥል ቆይቶ፣ ባለፈው ሳምንት እልባት እንደተገኘለት ይፋ ተደርጓል፡፡

ማክሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በተደረገ ድርድር የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የደኅንነት ኃላፊዎች ከስምምነት መድረሳቸው ተገልጿል፡፡

‹‹በውይይቱ ሁሉም አገሮች የተግባቡበትና የራሳቸውን ጥቅም ያስከበሩበት ነው፤›› ሲሉ የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ስምምነት ተደረሰባቸው ከተባሉት ጉዳዮች መካከል አንዱ በግድቡ ውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ላይ ጥናት የሚያከናውኑ የተመራማሪዎች ቡድን ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስረድተዋል፡፡

እነዚህ አጥኚ ቡድኖች በሦስት ወራት ውስጥ ሥራቸውን እንደሚያጠናቅቁና የደረሱበትን ውጤትም ለውኃ ሀብት ሚኒስትሮቹ እንደሚያቀርቡ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ውይይቱ ከዚህ ቀደም ከተደረጉት መሰል ስብሰባዎች የተሻለ ውጤት የተገኘበት ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ሦስቱ አገሮች የጋራ መሠረተ ልማት ፈንድ ለማቋቋም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያ በበኩላቸው፣ በሚኒስትሩና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በኩል ስምምነት ተደረሰ ተባለ እንጂ መሠረታዊው የውዝግብ ጉዳይ አሁንም አልተፈታም ይላሉ፡፡

ለጥናቱ ግብዓት የሚሆነው መረጃ መነሻ ዓመት ጉዳይ፣ እንዲሁም ሦስቱ አገሮች ለጥናቱ የሚያቀርቡት መረጃ ተዓማኒነትን የማረጋገጥ፣ ወይም መቅረቡ የሚረጋገጥበት ሁኔታ ላይ ስምምነት እስካልደረሱ ድረስ ሌላ ዙር ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው እንደማይቀር ተናግረዋል፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ረቡዕ ግንቦት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በተደረሰው ስምምነት መደሰታቸውን ገልጸው፣ ‹‹የግብፅ የውኃ ድርሻ እንደማይቀንስ ማረጋገጫ አግኝቻለሁ፤›› ማለታቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡ የሚቀጥለው ዙር የሦስቱ አገሮች ስብሰባ በካይሮ በሰኔ ወር የመጨረሻ ሳምንት እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -