Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነትና ቅድመ ታሪክ ከቋንቋ አንፃር እንዴት ይታያል?

የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነትና ቅድመ ታሪክ ከቋንቋ አንፃር እንዴት ይታያል?

ቀን:

መጋቢት ወር በሀገረ አሜሪካ ለንባብ ካበቁት አካዴሚያዊ መጻሕፍት ተጠቃሹ ‹‹ቋንቋና ነገድ በኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነትና ቅድመ ታሪክ›› የሚል ርዕስ ያለው የዶ/ር ግርማ አውግቸው ደመቀ መጽሐፍ ነው፡፡ ዶ/ር ግርማ የሥነ ልሳንና የኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች ባለሙያ ሲሆኑ፣ የምርምር ትኩረታቸው በአብዛኛው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ታሪክና ሥነ መዋቅር ላይ ነው፡፡ በቅርቡ በእንግሊዝኛ ካሳተሟቸው መጽሐፎች መካከል የአማርኛ ጥንተ አመጣጥ፣ ሰዋስዋዊ ለውጥ በሴሜቲክ የአማርኛ ሰዋሰው በዘመን፣ ሒደትና የአርጎባ ንግግር ዓይነቶች/ቋንቋዎች ይገኙባቸዋል፡፡

ስለአዲሱ መጽሐፋቸው በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን እንደተገለጸው፣ መጽሐፉ ስለኢትዮጵያ ቋንቃዋችና ቤተሰቦቻቸው የታሪካዊ ሥነ ልሳን ጥናት መውሰድ እስከሚችለው ጊዜ ገደብ ድረስ በመጓዝ መሠረታዊ መረጃ ያቀርባል፡፡ ቋንቋና ተናጋሪው የሚለያይ አይደለምና፣ ከቋንቋዎቹ አንፃር በመነሳት የኢትዮጵያን ሕዝብ ማንነትና ቅድመ ታሪክ ይዳስሳል፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ከተወሰኑ ብቸኛ ቋንቋዎች በስተቀር አፍሮ ኤሽያቲክና ናይሎሰሀራን ከሚባሉ ታላቅ ቤተሰቦች ይመደባሉ፡፡ ከጥቂት የናይሎሰሃራን ቋንቋዎች በስተቀር ሌሎቹ ለረዥም ጊዜ በኢትዮጵያ የነበሩ ናቸው፡፡ መጽሐፉ የአፍሮኤሽያቲክ ቋንቋዎች ከኤሽያ በተለያየ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ገቡ የሚለውን መላምት በስፋት መርምሮ ይህ ስለመሆኑ አሁን ያለው መረጃ ማረጋገጫ  እንደሌለው ያሳያል፡፡ ከዚህም በላይ በኅብረተሰብ መካከል ስላለው ውህደትና ልዩነት በስፋት ይረዝራል፡፡

የመጽሐፉ አዘጋጅ ዶ/ር ግርማ ‹‹መሠረታዊ መነሻ የቅጾች ማስታወቂያ›› በሚለው ምዕራፋቸው እንደገለጹት መጽሐፉ አራት ቅጾች ይኖሩታል፡፡ ለኅትመት የበቃው ቅጽ አንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነትና ቅድመ ታሪክ፤ ቅጽ ሁለት ኦሞቲክ፣ ናይሎሰሀራንና ምድባቸው ያልለየላቸው ቋንቋዎች፤ ቅጽ ሦስት ኩሽና ኩሽቲክ፤ ቅጽ አራት ሴማዊ ቋንቋና ሕዝብ ናቸው፡፡

ቀዳሚው ቅጽ በስድስት ምዕራፎች በ248 ገጾች የተደራጀ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ማንነትና ታሪካዊ አመጣጥ ከቋንቋ አንፃር ተተንትኖ መረጃዎቹም በታሪካዊና ንፅፅራዊ ሥነ ልሳን ዘዴ መቅረቡ ተወስቷል፡፡  

ዶ/ር ግርማ በመቅድማቸው ያነሷቸው ዐበይት ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዱ ‹‹የሴሜቲክ ሕዝብ ከዓረብ ወደኢትዮጵያ ገባ›› የሚለው መላምት፣ ሌላው ስለ ኩሽቲክ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚቀርበው ሐሳብና የኩሽ ምንነትን ፈትሸዋል፡፡ እንዲሁም የሀበሻን ምንነትንም መርምረውታል፡፡ በቅጽ አንድ መጽሐፋቸው ላይ ያነሷቸውን ነጥቦች እዚህ ላይ እንደወረደ ማቅረብ ወደድን፡፡  

መቅድማዊው ሐሳብ  

‹‹በትምህርት ዓለም መፍትሔና ማብራሪያ ያገኙ ጉዳዮች ወደ ኅብረተሰቡ ሳይወርዱ ይቀሩና መረጃ የሌለው ‹‹አፈ ታሪክ›› ነግሦ የሚታይበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የሴሜቲክ ሕዝብ ከዓረብ ወደ ኢትዮጵያ የገባ ነው የሚለው መላምት አንዱ ነው፡፡ ሌላኛው በሥነ ልሳን ጥናት ኩሽቲክ ቋንቋዎች የሚባሉትንና የእነዚህ ተናጋሪዎችን የሚመለከት ነው፡፡ የኩሽቲክ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ የሚቀርበው ታሪካዊ ትንታኔ በአንዳንድ ሥራዎች ከጥንታዊ ኩሽ መንግሥት ሕዝብና ከመጽሐፍ ቅዱስ ኩሽ አጠቃቀም ጋር እየተምታታ ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡ በተለይ ትንሽ በተማረው ዘንድ አንዱ የወሬ መክፈቻ የሴሜቲክ – ኩሽቲክ ጉዳይ እስከመሆን ደርሷል፡፡

‹‹ኩሽቲክና ሴሜቲክ ከቋንቋ ዘር ግንድ አንፃር ምንጫቸው አንድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙትን ኦሞቲክ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉትን እነ ጥንታዊ ግብፅን፣ በርበርን፣ ቻዲክ ቋንቋዎችን ጨምሮ የእነዚህ ወላጅ/ልዕለ ቋንቋ በአሁኑ ጊዜ አፍሮኤስያዊ/አፍሮኤሽያቲክ በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ከአፍሮኤሽያቲክ ቋንቋዎች በተጨማሪ በኢትዮጵያ የናይሎሰሃራን ቋንቋዎችና የተወሰኑ በቋንቋ ዘር ዝምድና ምደባቸው ያልየላቸው ቋንቋዎች አሉ፡፡

‹‹ኩሽ የሚለው ቃል (ወይም የዚህ ዝርያ ቃል) በጥንታዊ ሥራዎች ነገድን፣ ሕዝብንና አገርን ሲያመለክት፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሕዝብንና የቋንቋ ቤተሰብን ያመለክታል፡፡ በዘመናችን በትምህርታዊ ዐውድ አሁን በዚህ ቃል የሚገለጹትን የቋንቋ ቤተሰቦችም ሆኑ እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገሩ ሕዝቦች ጥንት በቅድመ – ክርስቶስ ከሁለት ሺሕ ዓመት በፊት ጀምሮ በነበረው ኩሽ በሚባለው አገር ከሚኖሩ ነገዶችም ሆነ በሌላ ከተጠቀሱት ሕዝቦች በቀጥታ የወረዱ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኩሽም አሁን በሥነ ልሳን ጥናት ካለው አጠቃቀም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የለውም፡፡ የምርምር ዕውቀት ሁልጊዜ ወደ ሕዝብ አይወርድምና በኅብረተሰባችን በተለይም በፖለቲከኞና ትንሽ ፊደል በቆጠሩት ዘንድ የጥንቱ አጠቃቀምን አሁን ካለው ጋር እያገናኙ ለሙገሳም፣ ለወቀሳም ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡

‹‹ቀደምት በአገራችን ሊቃውንት በቀረቡ ሥራዎች፣ ለምሳሌ በእነ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያና ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የጥንቱ አጠቃቀም ከአሁኑ ጋር እየተጋጨ ብዙም ግልጽ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ በአብዛኛዎቹ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለይ በስልሳዎቹና በሰባዎቹ ዘመናዊ የታሪክ ጸሐፊዎች ሥራዎችም ቢሆን ያለው የሕዝብ ታሪክ/ቅድመ ታሪክ ትንታኔ ቀደምት የሥነ ልሳን ሥራዎች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ አሁን ስለቋንቋዎቹና ስለሕዝቡ ያለን ዕውቀት የሚያንፀባርቅ አይደለም፡፡

‹‹በውጭ ጸሐፊዎችም ሆነ በአገራችን በተለይ ቀደምት ጸሐፊዎች፣ በኩሽ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ስለኢትዮጵያ ሕዝብ ማንሳት፣ ባህና ታሪክ/ቅድመ ታሪክ በስፋት የተሠራጨው ትረካ የተስተካከለ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይልቁንም በኢትዮጵያዊያን ጸሐፍት በተደረጉ ሥራዎች በከፊል የሚታየው የእርስ በርስ የመጣረስ ችግር ነገሩን በውል ሳያጤኑ ከተዛባና አንዳንዴም በዘረኝነት መርዝ ከተቀባ የውጭ ሥራዎች ከመገልበጥ የመጣ ነው፡፡

‹‹ከላይ የጠቀስናቸው ሥራዎች ከወጡ በኋላ፣ በሥነ ልሳን ዘርፍ በርካታ እመርታዎች ተካሂደዋል፡፡ በሥነ ሰብ፣ ሥነ ማኅበረሰብና በታሪክ ዘርፎችም እንዲሁ፡፡ በእነዚህ ዘርፎች የተደረጉ ምርምሮች አመርቂ ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው ባይባልም፣ ከበፊቱ በተሻለ ስለቋንቋዎቹና ስለሕዝቡ ግንዛቤ አሁን አለን፡፡ ይሁን እንጂ፣ በአገራችን ከዘመናችን ባሉት አዳዲስ ጥናቶች የታዩ ግኝቶች ጋር እኩል በመሄድ የማስተማሪያ መጻሕፍቶቻችን ሲታደሱ ብዙም አይስተዋልም፡፡ ይህ የሚከተለውን የኪዳነ ወልድ ክፍሌን ቃል ያስታውሰናል፤

‹‹ሀገራችንና ቋንቋችን ያረገዙትን ለመውለድ፣ ወልዶም ለማሳደግ፣ ሐኪምና ጊዜ አላገኙም፤ የተወለደውም ትምርታችን ወላጆቹና ሞግዚቶቹ ታርደው፣ ተሰደው ስላለቁ እንደ ሙት ልጅ ሆኖ ከመጫጨትና ከመመሥጨት በቀር እያደገና እየሰፋ፣ እየፋፋ መሄድ አልቻለም፡፡

‹‹አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ከዛሬ ምዕት ዓመት በፊት አካባቢ ያሉት አሁንም የተለወጠ አይመስልም፡፡ በየሙያው በአገራችን ያለን የሰው ኃይል ከቁጥር የማይገባ ብቻም ሳይሆን፣ ያለው የኢኮኖሚክ ሁኔታና የምሁሮቻችን ዝግጅት በሰል ያለ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል ደረጃ ላይ አይደለም፣ ያሉት ከኢኮኖሚክ ችግሩ በላይ በፖለቲካው እየተገፉ በየሰው አገር ተበትነው ለመኖር የተገደዱበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይህን ሥራ ያዘጋጀነው ከላይ ያሉትን ችግሮች በማሰብ ነው፡፡ የታሪካዊ ሥነ ልሳንና የዓይነታዊ ሥነ ልሳን ሥራዎችን፣ እንዲሁም ወቅታዊ የታሪክና የሥነ ሰብ ግንዛቤዎችን ከሥር ከሥሩ እየተከታተሉ የማስተማሪያ መጽሐፎቻችን መታደስ እስከሚችሉ ለመነሻ ግንዛቤ እንዲሆን በማሰብ ነው፡፡

ሀበሻ

‹‹ሀበሻ ኢትዮጵያዊ ከሚለው ቃል ይልቅ በአጠቃቀም በኅብረተሰቡ ዘንድ ሥር የሰደደ ነው፡፡ በርካታ አገራዊ (ቁሳዊና ሐሳባዊ) ባህሎች በዚህ ቃል ቅፅልነት ሲገልጹ ይስተዋላል፡፡ ለዚህ አስረጅ፣ የሀበሻ ዶሮ፣ የሀበሻ ጎመን፣ የሀበሻ መድኃኒት፣ የሀበሻ ኩራት፣ የሀበሻ ተንኮል፣ የሀበሻ ምቀኝነት፣ ወዘተ የሚሉትን አጠቃቀሞች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሀበሻ የሚለው ቃል ከህንድ እስከ አውሮፓ መላው ዓለም ኢትዮጵያን ለመግለጽ ሲጠቀሙበትም ቆይቷል፡፡ በህንድ፣ በፓኪስታንና በአጎራባች አገሮች ሀበሽ የሚባሉ በጀግንነታቸው የተመሰገኑ ከአካባቢያችን የሄዱ ሕዝቦችም አሉ፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት በውጭው አገር ኢትዮጵያዊውና ኤርትራዊው መሰሉን ሲያይ ‹‹ሀበሻ ነህ?›› የሚል ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ይህን ቃል ኢትዮጵያዊ የመሰለውን ሰው ለመተዋወቅ ከአጎራባች አገሮች በተለይ ከሶማሊያ የመጡም ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡ ይሁን እንጂ ሀበሻ የሚለው ቃል የተለየ ፖለቲካዊ ትርጉም ሰጥቶትም ይገኛል፡፡  

ሀበሻና ሴም

‹‹ሀበሻ የሚለውን ቃል ከሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪዎች ጋር የማገናኘት ሁኔታ ታሪካዊ መረጃ እንደሌለው ቢገለጽም፣ በአሁኑ ጊዜ በተለይ በአገራችን ተደጋግሞ ሲሰማ ይስተዋላል፡፡ በእግረ መንገድ ይህን ቃል የሚያነሱ ሥራዎችም ይህንኑ ሲደግሙት ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ ሚረን የቀይ ባህር ዜጎች በሚለው መጽሐፉ ሀበሻ የሚለውን ቃል በሙዳየ ቃላት የበየነው በኢትዮጵያና በኤርትራ ደጋማ ቦታዎች የሠፈሩ ሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦችን የሚመለከት እንደሆነ ነው፡፡

‹‹ሀበሻና ሴምን የማገናኘት ጉዳይ በኅብረተሰቡ ዘንድ በስፋት እንዲሠራጭ ያስቻለው በየትምህርቱ ቤቱ ሲሰጥ የነበረ ታሪክ ይመስላል፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሲሰጥ የነበረው በጣም የተለመደው መላምት ሴማዊ ሕዝቦች ከደቡብ ዓረቢያ ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረው መጡ የሚል ነው፡፡

‹‹በዚህ ጉዳይ ቀደምት ሥራዎች ውስጥ ኢዮብ ሉዶልፍ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የመጡበትም ጊዜ በአብዛኛው ከ1,000 እስከ 500 ቅጋአ (ቅድመ የጋራ አቆጣጠር) ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ለዚህ መላምት ሥር መስደድ በግንባር ቀደምትነት ከሉዶልፍ በማስከተል ከሚጠቀሱት ውስጥ አንደኛው ኮንቲ ሮሲኒ ናቸው፡፡ እነ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ በዚሁ በወቅቱ አሳማኝ መስሎ በታየው መላምት ላይ ተመርኩዘው የማስተማሪያ መጻሕፍት በማዘጋጀት፣ ሐሳቡን ወደ ትምህርት ቤት አወረዱት፡፡ ታደሰ ታምራትም ታላቅ ናቸው ብሎ ያሰባቸውን እነ ኮንቲ ሮሲኒን ሐሳብ እንዳለ ተቀብሎ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ታሪክ የሴማዊ ሕዝቦች መስፋፋት አድርጎ ማቅረቡ ለአመለካከቱ ሥር መስደድ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡ በቀዳሚዎቹ ምዕራፎች እንደገለጽነው፣ እንደእነዚህ ጸሐፊዎች እምነት ወደ ኢትዮጵያ መጡ ከሚባሉት የሴም ነገዶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ነገደ ሐበሽትና ነገደ አግዓዚ የተሰኙ ናቸው፡፡ ነገደ ሐበሸት ስሙን ለሕዝቡ መጠሪያ ሲያሳልፍ ነገደ አግዓዚ ደግሞ ቋንቋውን ተወልን፡፡

  ‹‹በዚህ ሥር በሰደደ መላምት ሀበሻ ከሀበሸት፣ ግዕዝ ደግሞ ከአግዓዚ ከሚሉት ቃላት የመጡ ናቸው፡፡ ግዕዝም ከሳባ በቀጥታ የመጣ ነው የሚለውን የግምት አነጋገር የእኛዎቹ እንዳለ ተቀብለውት በትምህርት ቤት ማስተማሪያዎች ውስጥ ይሰጥ ነበር፤ ‹‹ይህ ግዕዝኛ አነጋገር የመጣ ከክርስትና በኋላ ነው እንጂ የፊተኛው አነጋገርና ጽሑፍ ቀድሞ በደቡብ ዓረብ ሳሉ የሚጽፉበትና የሚነጋገሩበት የሳባ ቋንቋ ነው፡፡ ይኼም የሳባ ፊደልና ቋንቋ ለግዕዝ እንደ አባት የሚቆጠር ነው፡፡ የዚህ መላምት ቅርሻ እስካሁን ላለው በኅብረተሰቡ ዘንድ ለተስፋፋው የተሳሳተ አስተያየት መሠረት የሆነ ይመስላል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነልሳን ፕሮፌሰር ዘለዓለም ልየው ስለ መጽሐፉ በሰጡት አስተያየት፣ ዶ/ር ግርማ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ማንነትና ታሪካዊ አመጣጥ ከቋንቋ አንፃር ተንትኖ ያቀረቡባቸው መረጃዎች በታሪካዊና ንጽጽራዊ ሥነልሳን ዘዴዎች ተቀነባብረው በመቅረባቸው ስለ ኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ተናጋሪዎቻቸው ያለንን ዕውቀት ለማሳደግ በእጅጉ ይረዳል ብለዋል።

‹‹ከበቂ መረጃ ጋር አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ቋንቋዎች ምንጫቸው አንድ መሆኑን እንረዳለን። የተናጋሪዎች ለብዙ ዘመናት ተራርቆ መኖር ከአንድ ቤተሰብ የተገኙ ቋንቋዎችን ሊያለያይ እንደሚችል ሁሉ፣ ለብዙ ዘመናት አብሮ በመኖር የተነሳ ከተለያዩ የቋንቋ ቤተሰቦች የተገኙ ቋንቋዎች ደግሞ በቋንቋ ባህርያትና በሌሎችም እሴቶች እየተመሳሰሉ ሊሄዱ እንደሚችሉ በውል ያስገነዝባል፤›› በማለትም በመጽሐፉ ላይ አስፍረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...