Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየምሁራን አሥራፂነት የሚሻው ቴክኒክና ሙያ

የምሁራን አሥራፂነት የሚሻው ቴክኒክና ሙያ

ቀን:

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና (ቲቪኢቲ) በሠለጠኑ አገሮች የስማቸው መጠሪያ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የተናቀ ሙያ ተደርጎ ሲወሰድ ኖሯል፡፡ ከዚህ አኳያ ሙያው ተወዶና ተከብሮ እንዴት ነው መሥራት የሚቻለው በሚለው ዙሪያ ከኅብረተሰቡ ጋር ለመወያየት የሚያስችል ብዙ የንቅናቄ ሥራዎች ወደፊት እንደሚኖር የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

በቅርቡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ጥራት ችግር እና የሥራ አጥነት ትስስር ላይ ባዘጋጀው መድረክ ላይ በኢንስቲትዩት የሙያ ደረጃ ምደባና ብቃት ምዘና ዳይሬክተር ወ/ሮ ንግሥት መላኩ እንደገለጹት፣ ከንቅናቄው ባሻገር ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በጥናትና ምርምር ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ለቲቪኢቲ ተቀባይነትና ተፈላጊነት በእጅጉ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ለዚህም የእንቦጭ አረምን አስመልክቶ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ያለው ሥራ የቲቪኢቲና የዩኒቨርሲቲ ቅንጅታዊ ሥራ ጅማሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የሙያ ደረጃውንም ይሁን ምዘናውን የሚመራው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ስለሆነ ዘርፉን ከሚመሩ ሰዎች ጋር በጋራ ለመሥራት መታቀዱን፣ ለዚህም ዕውን መሆን የኢንስቲትዩቱ ምክር ቤት ሰብሳቢ የንግድ ሚኒስትሩ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበርም ከኢንስቲትዩት ጋር አብሮ እየሠራ እንደሚገኝና ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቴክኒክና ሙያ ቋሚ ኮሚቴ አንድ ሰው እንደተመደበ፣ የዚህ ዓይነቱ መቀናጀት ለሥልጠና ውጤትና ለጥራቱ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው  ከሁሉም በላይ ግን የአመለካከት ቀረፃ ላይ ከተሠራ ብዙ ለውጦች ይኖራሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

አቶ ተሻለ በሬቻ በፌዴራል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ የትምህርት ጥራት ጉዳይ በአገር ደረጃ አጀንዳ ከሆነ ቆይቷል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ግን ከአጠቃላይ ትምህርትና ከከፍተኛ ትምህርት ዘርፎች አንፃር ሲታይ የተናቀ ዘርፍ (ማርጂናላይዝድ) መስሎ ይታያል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ለዘርፉ ምሁራን ውጤታማነት የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው ለማለት ይቻላል፡፡

ከዚህ አኳያ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና የሕዝብ አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ለተግባራዊነቱም ከመምህራንና በአጠቃላይ ከዩኒቨርሲቲዎች ብዙ እንደሚጠበቅ መታወቅ እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የሰው ኃይል እያለፈ ያለው በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ሥርዓት ውስጥ ነው፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ውስጥ የሚያልፈው በጣም ትንሽ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ጠቃሚነትና ተቀባይነት ላይ ምሁራን ካልተረባረቡበት በስተቀር በአገር ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል እንደማይሆን አቶ ተሻለ ተናግረዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ባለሙያዎች የሠሩትን የሙያ ውጤቶች በቤቱ አስውቦ ይጠቀምባቸዋል፡፡ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች የሠሩትንም ልብስ ይለብሳል፡፡ ለልብስ ሠሪዎቹ ገን የሚሰጠው ግምት ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ እያደገ፣ እያደገ መጥቶ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና የሚገቡ ሠልጣኞችም ከኅብረተሰቡ የወጡ እንደመሆናቸው መጠን ከፍተኛ የሆነ የአመለካከት ችግር እንዳለባቸው ነው ያመለከቱት፡፡

በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ላይ ምርምር የሚሠሩ ምሁራን ሕዝቡን የማነቃነቅ ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ዕድል ሊሰጣቸው እንደሚገባ፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚና ሌሎችም መሰል ተቋማት የግንዛቤ ማስበጫ መድረኮችን እያዘጋጁ በንቅናቄው ሥራ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳስበዋል፡፡

መንግሥትም በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች መካከል አንዱና ዋነኛው የትምህርት ፍኖተ ካርታ የማዘጋጀቱ ተግባር ይገኝበታል፡፡ ዝግጅቱም በሚቀጥለው ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ላይ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ ነጥቦች እንዳስፈላጊነታቸው በፍኖተ ካርታው ውስጥ ይካተታሉ፡፡

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በተቋሙ ውስጥ በሚሰጠው ሥልጠና ብቻ የሚፈለገው ጥራት ሊመጣ አይችልም፡፡ ጥራት ሊመጣ ከተፈለገ በዋናነት ኢንዱስትሪው መሳተፍ አለበት፡፡ ተሳትፎውም ከሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ጀምሮ በምዘናውና በሁሉም ሊሆን ይገባል፡፡ እንዲያው በአጠቃላይ የኢንዱስትሪው የተደራጀ ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

በሠለጠኑት አገሮች ኢንዱስትሪዎች፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ላይ የሚሳተፉት ወይም ተፅዕኖ የሚያደርጉት በቻምበር፣ በአሶሼሽን፣ ወዘተ ተደራጅተው ነው፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ግን እያንዳንዱ ኢንስቲትዩት ከኢንዱስትሪ ጋር ያለው ግንኙነት በልምምጥ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ኢንዱስትሪው ከኢንስቲትዩቱ ለአፕሬንቲሽን የሚቀርቡለትን ሠልጣኞች ተቀብሎ የተግባር ሥልጠና ሊሰጣቸው ግድ ይላል፡፡ ለዚህም ትብብሩ ማበረታቻ ሊቸረው ይገባል፡፡ በምን መልኩ ነው መሰጠት የሚቻለው ለሚለው ጥያቄ ደግሞ ታክስ በመቀነስ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህም የተሻለ ሌላ አማራጭ ካለ ደግሞ ለማወቅ የሚስችል ጥናት እየተሠራ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ የኢንዱስትሪው የተደረጀ ተሳትፎ በመጣ ቁጥር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ጥራቱ እየተሻሻለ ይመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው፣ በሙያውም ውስጥ አመራር ላይ የሚቀመጠው ሰው በሥርዓቱ ወይም በዘርፉ ውስጥ ያደገ ያለፈ ብቻ መሆን እንዳለበት ከምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናትና ምርምር ተቋም መምህርና ተመራማሪ ዋና ለቃ (ዶ/ር) ‹‹ኢትዮጵያን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት ሁለት ተቋማት በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው ከፍተኛ ትምህርት ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ነው፡፡ ስለሆነም ተቋማቱ ኃላፊነታቸውን ተገንዝበው ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ 

የትምህርት ፖሊሲው ከወጣ ወይም ሥራ ላይ ከዋለ ቢያንስ 27 ዓመታት እንደሆነው፣ ካለው የትምህርት ጥራት ችግር አኳያ ሲታይ ግን ፖሊሲው እንደገና ሊከለስ እንደሚገባ ከዶ/ር ዋና ለቃ ማብራርያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...