Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የመምህርነት መነሻው ምን መሆን አለበት?

አቶ ዓምደ ሥላሴ ጀምበሬ በቀድሞው የሐረርጌ ክፍለ ሀገር ጉርሱም አውራጃ ሰቀሬ ወረዳ በ1924 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ የአንደኛና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሐረርና በአዲስ አበባ ከተማ ተከታትለዋል፡፡ በትምህርት አስተዳደር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ፣ እንዲሁም በአሜሪካ ከኦሐዮ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአገልግሎት ዘመንም በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በመምህራን ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት በመምህርነት፣ በሱፐርቫይዘርነትና በዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡ የሐረርጌ ክፍለ ሀገርና የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮዎችን በዋና ሥራ አስኪያጅነት መርተዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ፕላንና ፕሮግራም ኃላፊ፣ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅና የሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ፣ እንዲሁም የአስተዳርና ሒሳብ መምርያ ረዳት ሚኒስትር፣ ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በፕሮጀክት መሥሪያዎች ግዥ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ባለትዳር የአንድ ወንድ፣ አራት ሴት ልጆች አባትና የሰባት የልጅ ልጆች አያት የሆኑትንና በጡረታ ላይ የሚገኙትን አቶ ዓምደ ሥላሴን ጀምበሬን በትምህርት ዘርፍና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞውንና የአሁኑን የትምህርት ሥርዓት አጠር ባለ መልኩ ቢገመግሙልን?

አቶ ዓምደ ሥላሴ፡- የቀድሞው ሥርዓተ ትምህርት እንዲህ እንደዛሬው በሰፊው የተሠራጨና የተስፋፋ ሳይሆን ጠባብ ነበር፡፡ ነገር ግን ያሉት ትምህርት ቤቶች ጥራት ያለው ትምህርት ያቀርቡ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ትምህርት ቤት በጣም ተስፋፍቷል፡፡ ከብዛቱም የተነሳ የትምህርቱ ጥራት እንደተፈለገው ላይሆን ይችላል፡፡ የመምህራኑም አሠለጣጠን አጠያያቂ ይመስለኛል፡፡ በዚያን ዘመን ግን በመማር ማስተማሩ ሥራ ላይ የሚሳተፉ መምህራን ሁሉ ከመምህራን ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ሠልጥነው የተመረቁ ናቸው፡፡ በማስተማሩ ሥራ ላይ ከተሠማሩ በኋላም የማስተማር ብቃታቸው በየወቅቱ በኢንስፔክተሮችና ሱፐርቫይዘሮች ክትትልና ግምገማ ይደረግባቸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ አሁንም ቢሆን በመጠኑ ያለ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን የትምህርቱ ሥርጭት በመስፋፋቱ የተነሳ ቁጥጥርና ግምገማው በተሟላ መልኩ ይከናወናል ለማለት አያስደፍርም፡፡  

ሪፖርተር፡- እርስዎ በትምህርት ሚኒስቴር በልዩ ልዩ የኃላፊነት ቦታ ባገለገሉበት ዘመን የመምህራን አሠለጣጠን እንዴት ነው? የአሁኑን አሠለጣጠንስ እንዴት ያዩታል?

አቶ ዓምደ ሥላሴ፡- ወደ መምህራን ሥልጠና ከመግባቴ በፊት ስለ ትምህርት ሥርዓቱ በተጨማሪ ትንሽ የምለው አለ፡፡ ይኼውም በወቅቱ የነበረው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስም የተሰየመ አንድ ዩኒቨርሲቲ ነበር፡፡ ይህ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ከሚገኙና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ከተቸራቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የትምህርትን ጥራት በተመለከተ እኩል ደረጃ ላይ ነበር፡፡ በዚህ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ሁሉ አሜሪካ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለማግኘት ቅድሚያ ይሰጣቸው ነበር፡፡ የአጠቃላይ ሥርዓተ ትምህርቱ ውጤታማ ሊሆን የቻለው የመምህራን ምልመላና ሥልጠና ላይ የሚካሄደው እንቅስቃሴ ሁሉ ጥራታቸው የተጠበቀ ስለሆነ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በዚያን ዘመን በመምህርነት ለመሠልጠን የሚፈልግ ሰው በትምህርት ውጤቱ ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገበ ብቻ ነበር፡፡ ሥልጠናውም አጭር ሳይሆን የአራት ዓመት ሥልጠና ነበር፡፡ ሠልጣኞቹም ለምርቃት አንድ ዓመት ሲቀራቸው በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተዘዋወሩ ለሙከራ ያስተምሩ ነበር፡፡ አሠልጣኞቹም በየትምህርት ቤቱ እየተዘዋወሩ የማስተማር ዘዴያቸውን፣ ብቃታቸውን ይከታተሉ ነበር፡፡ ችግር ካለ ወዲያውኑ ያርሟቸዋል፡፡ ያበረታቷቸዋል፡፡ ትክክለኛውንም አቅጣጫ ያስይዟቸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በየትምህርት ቤቱ የወላጆች ቀን እጅግ በደመቀ ሁኔታ ይከበር እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይኼም በዓል የልጆቹን የፈጠራ ችሎታ ከማሳደጉም በላይ ወላጆች ከመምህራን ጋር ተገናኝተው ስለ ልጆቻቸው የትምህርት ውጤት የሚወያዩበት አጋጣሚ መፈጠሩንም አይዘነጋም፡፡ በአሁኑ ሥርዓት የሚታየው ሥልጠና ግን ወይም መምህር የሚሆኑት በትምህርት ውጤታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ብቻ ናቸው፡፡ የትምህርቱም የጥራት ችግር ከዚህ ይጀምራል፡፡ መምህር መሆን ያለበት በትምህርቱ ውጤት፣ በባህሪው የተመረጠና ለማስተማር ፍላጎት ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡   

ሪፖርተር፡- አሁን ያለውን የትምህርትን ተደራሽነት እንዴት ያዩታል?

አቶ ዓምደ ሥላሴ፡- ኢትዮጵያ ትምህርትን ለሁሉም ለማዳረስ በአሁኑ ጊዜ እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ከሆኑት አገሮች ጋር እኩል እየሄደች መሆኑን ያሳያል፡፡ በዚህም መሠረት ከሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕፃናት የትምህርት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በመማር ማስተማሩ ወይም በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ ያለው ችግር በግልጽ ታውቋል፡፡ ችግሩም የጥራት ጉዳይ ነው፡፡ ችግሩ በውል ከታወቀ መፍትሔውን መሻት ወይም ማግኘት ቀላል ነው፡፡ ይህንን ለማስተካከል ወይም ለማሟላት ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር እንቅስቃሴውን አጠናክሮ መቀጠል ነው፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር ይኼን ያህል ዩኒቨርሲቲዎች አቋቁመናል እያልን የምንኩራራና ዩኒቨርሲቲዎች በብዛት በመቋቋማቸው ብቻ የምንረካ ከሆነ የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሠለፍ እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴ ላይ ጥላ ያጠላበታል የሚል ሥጋት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመናዊ ትምህርትን በአገሪቱ ውስጥ ለማስፋፋት ያደረጉትን ጥረት የሚያሳይ፣ እንዲሁም በፕሮጀክት አደረጃጀት ላይ ትኩረት ያደረጉ ጽሑፎች አዘጋጅተዋል ይባላል፡፡ እስቲ በዚህ ዙሪያ የሚሉን ነገር ይኖር ይሆን?

አቶ ዓምደ ሥላሴ፡- ወደ ጽሑፎቹ ከማግባቴ በፊት አፄ ምኒልክ ስለ ትምህርት ጠቃሚነት የነበራቸው እምነትና ፍላጎት ከአገር አልፎ ዓለም አቀፍ ዕውቅና የተቸረው ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በአፄ ምኒልክ አስተሳሰብ ትምህርት በነፃና በግዴታ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ አሁን በዓለም ላይ ያለውና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በነፃና በግዴታ መሆን አለበት የሚለው አስተሳሰብ ከአፄ ምኒልክ እሳቤ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለ አፄ ምኒልክ የትምህርት እሳቤ ይኼን ያህል ካልኩ፣ ስለመጻሕፍቱ ትንሽ እላለሁ፡፡ በአፄ ምኒልክ ዙሪያ ያዘጋጀሁት ጽሑፍ ‹‹ግሮውዝ ኤ ሞደርን ኤዲዩኬሽን ኢን ኢትዮጵያ ኢኒሺየትድ ባይ ኢምፐረር ሚኒሊክ II ኤ ሴንቸሪ ኤጎ›› የሚል ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ደግሞ ‹‹ፕራክቲካል ሃንድ ቡክ ፕሮጀክት ዴቭሎፕመንት ኤንድ አምፕሊንቴሽን  ‹‹ዊዝ ስፔሻል ፎከስ ኦን ፕሮከዩርመንት ኦፍ ኢንተርናሽናሊ ፈንድ ፕሮጀክት›› የሚሉ ናቸው፡፡ ፕሮጀክት አዘገጃጀት ላይ ያተኮረው ጽሑፍ በትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት ለዓለም ባንክ ቀርቦ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ የትኩረት አቅጣጫውም በመንግሥት በጀት፣ በብድርና በዕርዳታ የሚሠራ አንድ የልማት ፕሮጀክት እንዴት እንደሚዘጋጅ፣ ወደ ትግበራ ሲገባ ደግሞ ምን ዓይነት ክትትል እንደሚያስፈልገው ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ ለተጠቃሚው እንዴት እንደሚተላለፍ የሚያብራራ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- የፕሮጀክት አዘገጃጀት እንዴት ሊዋጣልዎ ቻለ?

አቶ ዓምደ ሥላሴ፡- በትምህርቱ ሥርዓት ውስጥ በነበርኩበት ዘመን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አዘጋጅና እጽፍ ነበር፡፡ የጻፍኳቸውም ዶክሜንቶች የሚያንፀባርቁት በመንግሥት በጀት ወይም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች እንዴት እንደሚዘጋጁና አፈጻጸማቸው ምን መልክ መያዝ እንደሚገባው የሚያስረዳ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ዑጋንዳ ላቀደችው የልማት ሥራ ማከናወኛ ከዓለም ባንክና ከአፍሪካ ልማት ባንክ ብድር ጠየቀች፡፡ ብድሩም የሚሰጣት ኢትዮጵያ እንደሠራቸው ዓይነት ፕሮጀክት ቀርፆ ማምጣት ከቻልሽ ነው የሚል ቅድመ ሁኔታ ተሰጣት፡፡ በዚህም የተነሳ ፕሮጅክቱ እኔ እንድሠራላቸው በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ጥያቄ ቀረበልኝ፡፡ እኔም ጥያቄውን ተቀብዬ ወደ ዑጋንዳ አቀናሁ፡፡ የሚሠራውን ልማት አስመልክቶ ጥሩ ፕሮጀክት አዘጋጅቻለሁ፡፡ ፕሮጀክቱም በዓለም ባንክና በአፍሪካ ልማት ባንክ ተቀባይነት አግኝቶ የጠየቁት ብድር ተፈቀደላቸው፡፡  

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ያለውን የኢትዮጵያ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ ዓምደ ሥላሴ፡- በተለይ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የኢትዮጵያ አንድነት ከሞላ ጎደል ነው የምሰማው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በጤና ምክንያት ነው፡፡ የቻልኩትን ያህል እንደሰማሁት ከሆነ ብሔረሰብና የኢትዮጵያ አንድነትን አስመልክቶ እየታየ ያለው የተሳሳተ አስተሳሰብ በአገሪቱ ላይ ችግር አስከትሏል፡፡ ውዥንብሩም እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡ ይህም አስተሳሰብ ለማረም ዜጎች ሁሉ የአቅማቸውን ያህል ቢታገሉ እመኛለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነትና ብሔረሰብ መሆን ሁለቱም የሚጋጭ ወይም አንዱ አንዱን የሚያጠፋ አይመስለኝም፡፡ አንድ አባባል አለ፡፡ ይኼውም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ይባላል፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትጵያዊነትና ብሔረሰብነት የሚቃረኑ አይደሉም፡፡ ሕገ መንግሥቱ በተረቀቀበት ጊዜ ምናልባት በግልጽ ያልታዩ ነገሮች ፌዴራሊዝም በቋንቋ ላይ ብቻ እንደተመሠረተ ተወስዶ መተርጎሙ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ እሳቤ ነበር ሕዝቡን እያወናበደና ብዙ ችግር የፈጠረው፡፡ ግን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ብሔር ክልል ውስጥ ሠርቶ ለመኖር፣ እዚያ ካለው ብሔር ጋር እኩል ነፃነት እንዲያግኝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያዊነት በሁሉም ቦታ ተቀባይነትና መብትም መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የትምህርቱ የጥራት ጉድለት የኢኮኖሚው ማሽቆልቆልና በሁሉም ነገር ወደ ኋላ እየጎተትን ያለው መንስዔው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው ክልል የመኖርና የመሥራት መብቱ በአግባቡ ስላልተጠበቀለት ነው፡፡ ይህንን ችግር ለማረም ለማስተካከል የሚያደርገው ጥረት እንዲበረታታና ዳር እንዲደርስ እመኛለሁ፡፡      

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በእንጦጦ ተራራማ ቦታዎች በአደራ በመንግሥት በተረከበው 1,300 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል...

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...