Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርበፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ የሚታየውን የተካረረ ችግር ለመፍታት ምን ታስቧል?

በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ የሚታየውን የተካረረ ችግር ለመፍታት ምን ታስቧል?

ቀን:

በአሳምነው ጎርፉ

ፌዴራሊዝም አሁን ባለችው ዓለም ቢያንስ ሁለት ምዕተ ዓመት ዕድሜን ያስቆጠረ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በአፍረካ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ጎልቶ ሲወጣ የታየው ግን ቢያንስ ከአራት አሥርት ዓመታት ወዲህ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ እነ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካና ኢትዮጵያን ለአብነት ማንሳትም ይቻላል፡፡  በእርግጥ መንግሥታዊ አወቃቀርና ርዕዮተ ዓለም የሚምታቱበት አጋጣሚ ብዙ በመሆኑ ቀላል ቁጥር የሌላቸው ወገኖች ፌዴራሊዝምን እንደ አንድ ፖለቲካዊ ርዕዮት ሲመለከቱት ይስተዋላል፡፡ ፌዴራሊዝም ግን ርዕዮተ ዓለም አይደለም፡፡ ፌዴራሊዝም የመንግሥት አደረጃጀት ሥርዓት ማለት ብቻ ነው፡፡ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች በፌዴራል ደረጃ ዕውቅና ያለው መንግሥት የሚመሠርቱበትና በዚያም መንግሥት የሚተዳደሩበት ሥርዓት ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ አባል የሆነ እያንዳንዱ ክልል በማዕከላዊው ፌዴራል መንግሥት መርሆዎች ላይ ተመሥርቶ እንደ የራሱ ልዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ታሪካዊ ሁኔታዎች እንደየ ባህርይው ሁኔታ የሚያደራጅበት ሥርዓትም ነው፡፡ እንግዲህ በዓለም ላይ 30 በሚደርሱ አገሮች ከ2.5 ቢሊዮን በላይ ሕዝቦች በዚህ ሥርዓት እየተዳደሩ መገኘታቸው ለዚህ ነው፡፡

     የፌዴራሊዝም ጽንሰ ሐሳብ ዓላማ በብዝኃነት ውስጥ አንድነትን፣ ልማትና ዕድገትን በዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም አሠራር አማካይነት ማምጣት ነው፡፡  በእርግጥ ፌዴራሊዝም ካለ ዴሞክራሲ የተሳካ አተገባበር ሊገጥመው እንደሚችል ዕሙን ነው፡፡ በተለይ ብዝኃነት ያላቸውን ሕዝቦች አንድ ለማድረግ ከዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም የተሻለ ሥርዓት የለም፡፡ ሁሉም ሕዝቦች በአገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሕይወት ውስጥ የመሳተፍ እኩል ዕድል የሚያገኙበት ሥርዓት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በረከት ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ በዋናነት ብሔር ተኮርና ዘውጌያዊ ፌዴራሊዝም ብዙ ጊዜ ወደ መደነቃቀፍ የሚያዘነብለውም ለዚህ ነው፡፡ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ከባዶ ሜዳ ዝም ብሎ የሚበቅል ሳይሆን የብዙ ባለድርሻ አካላት ተዋናይነት ያለበት፣ ሌላው ቀርቶ ሕዝብና መንግሥት ብቻ ሳይሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና በውጭ አገሮች የሚኖሩ ዜጐች (ዳያስፖራዎች) እጅ እየተጠናከረ የሚሄድበት መሆን አለበት፡፡ ሥርዓቱን በመገንባት ሒደት የተሳካላቸው ኢኮኖሚዎች (አገሮች) ታሪክና ዳራ የሚያስገነዝበው ይህንኑ ነው፡፡  ያልተሳካላቸው አገሮች ልምድም የውድቀታቸው ምንጭ የሚነሳው አሳታፊ ያልሆነና አድሎአዊ ወይም በጥቂቶች ውሳኔ ብቻ የመጫን፣ ብሎም ለዘረኝነትና ለከፋፍለህ ግዛው የተጋለጠ ፌዴራሊዝም ለመተግበር በመሞከራቸው ብቻ ነው፡፡ ደቡብ ሱዳንና ናይጄሪያን ለአብነት መውሰድ ይቻላል፡፡ እኛም ቢሆን ከአውሮፓውያን የፌዴራል ሥርዓት ስኬትና ከአፍሪካዊያን አንዳንድ አገሮች ውድቀት በቂ ትምህርት ካልወሰድን፣ ብሎም እኛን ካጋጠመን ያተገባበር መደነቃቀፍ ካልተማርን ወደ ውድቀት ሊወስደን እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልገናል፣  ይገባልም፡፡ 

- Advertisement -

      በተደጋጋሚ እየታየ እንዳለው በአገራችን አተገባበሩ ገና ለጋ ዕድሜ ላይ ያለ ቢሆንም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የፌዴራል ሥርዓቱ አተገባበርን የተመለከቱ ውዝግቦች ተደጋግመው እየተወሱ ነው፡፡ አንዳንዶች ፌዴራሊዝም የሕዝቦችን እኩልነት አረጋግጧል፡፡ ለአገራችን ፈጣን ዕድገትና ዴሞክራሲ ግንባታም ቀላል የማይባል እገዛ እያደረገልን ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የፌዴራሊዝምን በጎነትን ሳይክዱ ብሔር ተኮር መሆኑ፣ አንድነትን ለማላላትና ዘውጌነትን ለማባባስ ዳርጎናል፣ አገራዊ ብሔርተኝነትም ተዳክሟል እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ይህን በደጋፊና በተቺ ቁጥር ወይም በጥናት ሚዛን ማረጋገጥ ባይቻልም፣ በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል ግን ለ27 ዓመታት ከተጓዝንበት መንገድ ፈቀቅ ያለ የማሻሻያ ዕርምጃ ሲወስድ አልተደመጠም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ይህ በተነሳው ሁከትና ኢሕአዴግ በጀመረው ተሃድሶም ላይ  በኢትዮጵያ በየጊዜው ለሚነሱ ግጭቶችና የፀጥታ ችግሮች መነሻዎቹ፣ ሕገ መንግሥቱና ወይም የፌዴራል ሥርዓቱ እንደሆነ ደጋግሞ ሲነሳ አንደነበረም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በየዋህነት ወይም በግብዝነት፣ በስህተት ወይም በሌላ ሥውር ዓላማ ሰበብ የፌዴራሊዝሙን ይዘት በማዛባት ወደ ሌላ ግብ ለመምራት ቢመስልም የመለያየቱ ተግዳሮት ግን ከፍተኛ እየሆነ ነው፡፡ 

ያለ ጥርጥር ሥርዓቱ በተለይ በአፈጻጸም ረገድ በሕዝቦች መካከል ፀንቶ የቆየውን የአብሮ መኖር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ሁኔታዎችን የማጠናከሩን ያህል ጉድለቶች እንዳሉበትም ራሱ ገዥው ፓርቲ አምኗል አለ፡፡ ስለሆነም በቀጣዩ ጊዜ ሕዝብን ከሕዝብ ለማለያየት ሆን ተብሎ የሚታቀደው ሴራ  በማክሸፍ፣ ሥርዓቱን ለጠንካራ አገር ግንባታ የማዋል ጉዳይ ልዩ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል፡፡ ማሻሻያው ማተኮር ያለበትም በቀዳሚነት በውስጥም ሆነ በውጭ በተጨባጭ  አደናቃፊዎች አንዱ፣ ብሔር የራሱን ክልል ብቻ ይዞ በሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ላይ በሩን ዘግቶ ‹‹አትድረሱብኝ›› የሚል አቋም እንዲኖረው ለማድረግ  እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው መፈተሽ አለበት፡፡ ከዚህ በወረደ ደረጃ ሴቶችን ‹‹የሌላ ብሔር ወንድ ለምን አገባሽ፡፡ መፍታት አለብሽ? የራስሽ ብሔር ወንድ እያለልሽ ከሌላ ጋር መጋባት የለብሽም፤›› የሚል ማስፈራሪያ እየሰጠ የኖረውን አገራዊ ሐውልት ለመናድ የሚባዝነው ጠባብም ቁጥሩ ትንሽ እንዳልሆነ ታውቆ፣ በየደረጃው ማስተካከያና ሕዝብን ያሳተፈ ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ችግርም ከአገር ውስጥ አልፎ በስደት እስካለው ኢትዮጵያዊ ድረስ የተጋባ መሆኑም ዘወትር የሚያሳዝን የጥፋት መንገድ ነው፡፡

     በተለይ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የአደጋውን ጫፍ መረዳት እንደተቻለው፣ አሁንም ‹‹ወደ ክልሌ ለምን መጣችሁ? ለምን ቤት ሠራችሁ? ለምን ሠርታችሁ ትኖራላችሁ? ለምን ከምርታችን ትቃመሳላችሁ (ትቀራመታላችሁ) የሚባልበት ሁኔታ በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ አለ፡፡ ብዙ ሰውን እየገረመ ያለው እውነት ደግሞ አሁንም ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተመረጡና ኢሕአዴግም ከታደሰ በኋላም ችግሩ አለመወገዱ ሲታይ፣ የገባንበትን አዘቅት ለማየት ያስችላል፡፡ በተለይ በየአካባቢው ለውጡን እያፋጠኑልን ያሉ የግል ባለሀብቱን እንቅስቃሴዎችን የኢኮኖሚ መስተጋብሮች ለማደናቀፍ የሚደረገው ሙከራ በሰከነ መንገድ በጥናት ከተመለሰ፣ ሥራ አጥነትንና ድህነትን እያባባሰ ሌላ ቀውስ የሚጋብዝብን ነው፡፡ በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ ጥቂት ጥገኛ ባለሥልጣናትና የበታች አመራሮች፣ እንዲሁም ከውድድር ይልቅ በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚሯሯጡ ባለሀብት ተብዎች ወጣቱን በስሜት እየቀሰቀሱ ችግር ሲፈጥሩ ታይተዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ያሰፈረውን ዜጐች በአገሪቱ የትኛውም ክልል ተዘዋውረው ሠርተው የመኖር መብት ያላቸው የመሆኑን የበላይ ሕግ ጥሰው፣ የክልላቸውን በር በሌሎች ዜጐች ላይ የመከርቸም መብት ያላቸው እስኪመስሉ ድረስ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎችም ሆነ የፌዴራሊዝሙን ራዕይ ወደ ቅዠት ለመለወጥ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መኖራቸው ታይቷል፡፡ አሁንም ይህ ድርጊት ስለመቆሙ ዋስትና የለም፡፡ ይህ እየታወቀ ሕዝብና መንግሥት በቂ ትግል አለማድረጋቸው ደግሞ አሁንም መፈተሽ ያለበት ነው፡፡

     በመሠረቱ ይህ የተዛባ አካሄድ የፌዴራሊዝሙን ትርጓሜና አሠራር ከርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ ጋር ያጋጫል፡፡ ፌዴራሊዝም የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት ነው፡፡ ዘረኝነት ግን ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ ይህ አገር የሚያፈራርስ አስተሳሰብ በማንኛውም መንገድ ካልተቀጨ በስተቀር አሁንም የተዳፈነ ቢመስልም፣ ወደ ደቡብ አፍሪካው ዓይነት የዘር ጥላቻ (Xenophobia) መሸጋገሩ እንደማይቀር ዋስትና የለንም፡፡ ድርጊቱ ያሳሰበው መንግሥትና ገዥው ፓርቲም ወደ ቀልቡ ተመልሶ በማሰብ የመረጣቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር የአንድነትና አገራዊ ብሔርተኝነት አቀንቃኝ ለማድረግ የሞከረ መምሰሉ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡ ግን ይህንንም ጅምር ብዙኃኑ አመራርና ሕዝቡ ካልደገፈውና ለተግባራዊነቱ መፋለም ካልቻለ፣ ንግግርን ብቻ የአገራዊ አንድነት መልህቅ አድርጎ መቁጠር ሞኝነት ከመሆን አይዘልም፡፡ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በግጭትና በመለያያት መንፈስ ሲናጋ የከረመውን የሕዝብ ስሜት ለማቃናት ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ፡፡ በአንድ በኩል በየክልሉ እየተዛዋወሩ፣ በሌላ በኩል ጎረቤት አገሮችን እየጎበኙ የተቀደደውን ሲሰፉ መሰንበታቸው ከዚሁ የሚነሳ ነው፡፡ አሁንም  ስለፌዴራሊዚም ፋይዳና የተካረረ ዘውጌያዊነት የጥፋት መንገድ ላይ፣ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተሰጠውና በቀጣይም የሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫና ማጠናከርያ ኮንፈረንስና ስብሰባ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ባሳተፈ መንገድ ሊከናወን ይገባልም የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው፡፡

በመሠረቱ በአንድ አገር ውስጥ ሕዝቡ ከገጠር ወደ ከተማም ሆነ፣ ከከተማ ወደ ገጠር ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት አለው፡፡ በእኛም አገር ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ይሁንና ግን በአሁኑ ወቅት አይደለም ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ይቅርና በአንድ ክልል ውስጥም ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው ለመንቀሳቀስ የከበደ ጉዳይ ሆኗል፡፡ አሁን አነሰም በዛም ሰው እየፈለሰና እየተመመ ያለው ወደ አገሪቱ ዋና ከተማ ነው፡፡ በቀጣይም ቢሆን መፍትሔው ዜጐች ከገጠር አካባቢ መኖሪያቸው ወደ ክልል ከተሞች ወይም ወደ አዲስ አበባ እንዳይሄዱ ማድረግ አይደለም፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች ተዘዋውረው መኖር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መሆኑን እናውቃለን፣ እናምናለን፣ እናከብራለን፡፡ ይህን መጠበቅ ያለባቸው ደግሞ ሕዝብና መንግሥት ናቸው፡፡

አገራችን ጥንታዊ ነች፡፡ ሕዝቦቿም አብረው፣ ተጋብተውና ተዋልደው ለዘመናት የኖሩ ናቸው፡፡ ስለሆነም ምንም እንኳን ፌዴራሊዝም በአገሪቱ እየተራመደ ቢሆንም፣ ዜጎች የተወለዱበትን ወይም የኖሩበትን አካባቢ ለቅቀው ወደ ከተማም ሆነ ወደ ገጠር  የሚሄዱና በሄዱበት ቦታ ለስድስት ወራትና ከዚያ በላይ ከኖሩ ‹‹የነዋሪነት ደረጃ›› (Residency Status) ሊያገኙ ይገባቸዋል፡፡ ከሕገ መንግሥቱም በላይ ታሪካዊ ዳራችን ይህ እንዲሆን የሚያስገድድ ነው፡፡ አይደለም በአፍሪካ በአውሮፓና አሜሪካ ሞልተው የተረፉ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል በሕጋዊ መንገድ አድራሻቸው ታውቆ የሚመዘገቡበት፣ መታወቂያ የሚያገኙበት፣ ‹‹መኖሪያ አልባ›› ተብለውም ቢሆን ለቁጥጥር በሚያመች ሁኔታ መኖር አለባቸው፡፡ አገሬው በአገሩ ኮርቶና ተማምኖ እንዲኖር መደረግም አለበት፡፡ አሁን ፈተና እየሆነ ያለው በዘርና በመደብ ልዩነት ስም አንዱ አሳዳጅ ሌላው ተሳዳጅ እየሆነ ሕዝባዊ ዋስትና የማጣት መሆኑንም አጢነን ለለውጥ መነሳት ያስፈልጋል፡፡

በአሁኑ እውነታ በእኛ አገር ያለው ሁኔታ ከገጠሮች ወደ ከተሞች የሚፈልሱ ዜጐች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ይህን በኢኮኖሚ ፍላጎትም ይባል በፖለቲካ ግፊት የሚፈጠር ክስተት ተገቢና አስፈላጊ በሆነ ሥርዓት ለመምራት መንቀሳቀስ የግድ የሚል ነው፡፡ በተለይ በፀጥታ ችግር የሚከሰትን መደነቃቀፍም ሆነ ለመኖር የሚያውክ ድርጊት ለማስቆም መቆጣጠርያ ሁነኛ ዘዴ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ቁም ነገር የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልንና አብሮነትን ለማሳደግ፣ ማኅበራዊ ተቋማትንና እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ሕዝባዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ሕዝቡን በየቀበሌው፣ በየወረዳው ወይም በተለያዩ አደረጃጀቶች እርስ በርሱ የሚተዋወቅበትን ሥርዓት መዘርጋትና በዚያም አማካይነት መጠቀም ተገቢ የመሆኑ እውነታ ጎልቶ እየታየ  ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ እንደታየው ፀጥታና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ዋነኛው የመፍትሔው ባለቤት ችግሩ የተነሳበት ክልል መሆኑን ነው፡፡ ከሰላማዊ መግባባትና ዕርቅ አንስቶ በሕገወጦች ላይ ከሕጉ አንፃር እስከ ከፍተኛ ዕርምጃ አወሳሰድ ድረስ ክልሉ ባለው ኃይልና የሕግ ሥርዓት መጠቀም መቻል አለበት፡፡ ችግሩ ከአቅሙ በላይ ሲሆን ከአጐራባች ክልሎች ድጋፍ ሊጠይቅና ሊያገኝ ይችላል፡፡ ችግሩ ከእነዚህ ሁሉ በላይ ከሆነ የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነቱን ይወስዳል፡፡ በተጨባጭ እየታያ እንዳለው ግን ክልሎች ኃላፊነታቸውን ሳይወጡ እጃቸውን አጣጥፈው  (አንዳንዴም ሁከቱ እንዲነሳ የሚፈልጉ መስለው) ይቀመጡና የፌዴራል መንግሥት ሁሉንም እንዲያደርግ በመጠበቅ ላይ ናቸው፡፡ ከዚያም በኋላ ጣልቃ ተገባብን ወይም ከፍተኛ ኃይል አጠቃቀም ታይቷል የሚል ትችት ይከተላል፡፡ እዚህ ላይ ነገሮች ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ማደረግ ያስፈልጋል፡፡ በተመሳሳይ በክልሎች በኩል የአፈታት አቅም ችግር ካለም ከወዲሁ (አስቀድሞ) ማሰብና ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ቀደም የሕዝብ ለሕዝብ ግኝኙነት ችግር ያጋጠመባቸው ክልሎች፣  የቤንሻንጉልና ኦሮሚያ (በተደጋጋሚ) በአማራና በሌሎች ሕዝቦች ላይ፣ በአማራ ክልልም በትግራይ ተወላጆች ላይ፣ በሶማሌ ክልልም በኦሮሞ ተወላጆች ላይ፣ በአንዳንድ የደቡብ ክልል ዞኖችም በሌላው ሕዝብ ላይ የተስተዋሉ የመግፋትና ባዕድ የማድረግ ድርጊቶች ለምንና እንዴት እንደተከሰቱ በመፈትሽ ዘላቂ ለውጥ ማምጣትና ቁስሉን ማሻር ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ  ችግሩ እየተፈጠረ ያለው በየራሱ ክልል ውስጥ ስለሆነ እያንዳንዱ ክልል የየራሱን ችግር በየራሱ መንግሥት አማካይነት የመፍታት አቅም ሊኖረው ይገባል፡፡ የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ዕርምጃ ደግሞ ሕግና ሥርዓትን ከማስከበርም በላይ ዘላቂ የአገራዊ አንድነት ግንባታ ላይ ማተኮር አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ደጋግመው እንደተናገሩት አገራችን ምንም ሀብት ሳታጣ አንዱ የሌላውን በማውደምና በመዝረፍ ለመኖር ሊመኝ አይችልም፡፡ ይልቁንም ሁሉም የተባባረና እየተወዳዳረ በፍትሐዊነት አግባብ ሁሉም ሕይወቱ ሊቀየር ይገባል፡፡ አገርም ልትቀየር ትችላለች፡፡ ይህን ዓለም አቀፍ እውነት በመዘንጋት እርስ በርስ መገፋፋት ግን ካለጥርጥር ለትውልድ ቂም በቀል መቆየትና አገራዊ ውድቀትን ማስከተል እንጂ፣ ሌላ ፋይዳ ሊያስገኝ አይችልም በፌዴራል ሥርዓትም እየተሳበበ ሊቀጠል አይገባውም የሚሉ ወገኖች በእጅጉ መብዛታቸው ሊጤን ይገባዋል፡፡

በእርግጥ አሁን የፖሊሲና ጥልቅ መዋቅራዊ ዕርምጃ ባያውጀውም  መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን ችግሮቹን በዘዴና በብልኃት፣ በትዕግሥትና በማስተዋል ይዞ ለመራመድ ለአብነት ያህል የተጠቂነት ስሜት የፈጠረውን እስረኞችን የመፍታት ዕርምጃና የማይነካ የሚመስለውን የአመራር ማቀያየር ተግዳሮት ታይቷል፡፡ በሙስና ላይና ሕዝብን ለማፈናቀል በሚዳክረው ላይ ግን የዕርምት ዕርምጃ አለመታየቱ በአፋጣኝ  ሊታሰብበት የሚገባው ነው፡፡ እውነት ለመናገር እስካሁንም መንግሥት ችግሩን ተገንዝቦ ዕርምት ያላደረገው በቸልተኝነት አይመስለንም፣ ሊሆንም አይችልም፡፡ የሚሆነው በኖረው በሬ በማረስ ለመዝለቅ የሚፈልገው ነባሩ አመራር ኃይል እየጎተተው እንደሆነ ትርጥር የለውም፡፡ ያ አካሄድ ግን በሒደት የአገሪቱን ህልውና፣ የሕዝቡን ሕይወትና ንብረት፣ የፌዴራል ሥርዓቱን መጠበቅና በብዙ የሕይወት መስዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲ ሰላምና ልማት የሚያደናቅፍና የሚጎዳ ነበር፡፡

       አሁንም በተለይ አዲሱ መንግሥት ይህን ወደር የሌለው ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን በጥንቃቄ ማጤን አለበት፡፡ የለውጥ መዘውር ውስጥ በመግባትም ፌዴራላዊ ሥርዓቱንና የሕዝቦችን አንድነት ይበልጥ አጣጥሞ ለማስቀጠል የማያዳግም ዕርምጃ ለመውሰድ፣ ችግሩን ከሥር ከመሠረቱ ደጋግሞ መመርመር አለበት፡፡ የመንግሥት ዕርምጃ እንደ ልጆች ጨዋታ የቀለለ ባለመሆኑ ታሪካዊ ኃላፊነትን በትጋትና በመደማማጥ መተግበርም ያስፈልጋል፡፡ በሁሉም መስክ ቢሆን የሕዝብ ፍላጎትንና ዓለም አቀፉን ነባራዊ ሁኔታ በመፈተሽ የመፍትሔ አማራጮችን በዝርዝር ማየት ለነገ የማይባል ተግባር መሆን አለበት፡፡ የሚያጋጥሙ የውስጥና የውጭ ችግሮች  ለመፍታት የተሻለው ዘዴ (አማራጭ) የቱ እንደሆነ ለይቶ በቁርጠኝነት መወሰንም የአመራሩ ድርሻ መሆን አለበት፡፡ በተለመደ አባባል እንደሚታወቀው ‹‹የበሽታው መድኃኒት ያለው እዚያው በሽታው ውስጥ ነው፤›› እንደሚባለው፣ በሽታውን ማግኘት (ማወቅ) ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ውስጥ ክፉኛ እያቆጠቆጠ የመጣውን የተካረረ ዘውጌነት ለማዳከም በመንግሥት ደረጃ የታሰበውን የለውጥ ዕርምጃ መመርመርና ለተግባራዊነቱም ተግቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ይገባልም፡፡ ለዚህ ደግሞ የማሻሻያ ዕርምጃ መውሰድ ተከታይ ተግባር መሆን ይገባዋል፡፡ ይህ ሲሆን እየተገነባ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓትም ሆነ የሕዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና አብሮነት መልሶ ችቦው ይለኮሳል፡፡ አገርም በፈጣኑ የለውጥ መዘውር ውስጥ ተገባለች፡፡ ጠላቶቻችንም አርፈው መቀመጥ ይጀምራሉ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

             

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...