Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የገንዘብ ጉድለትና ኪሳራ ያስመዘገቡ ማኅበራት አመራሮች የሚጠየቁበት አሠራርና ዕቅድ ተነደፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ በሥሩ የሚገኙ ማኅበራትን አሠራር፣ በተለይም አሁን ሥራ ላይ ያለውን የዕቅድ አፈጻጸምና ስልት በመቀየር በክትትልና ቁጥጥር ማጣት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ጉድለትና ኪሳራ ያስመዘገቡ አመራሮች የሚጠየቁበትን አሠራር ጨምሮ ለ15 ዓመታት የሚዘልቅ አዲስ መሪ ዕቅድ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

ይህ የተገለጸው ኤጀንሲው በአፋር ክልል ርዕሰ ከተማ ሠመራ ላይ ሚያዝያ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው፡፡ በሥራ ላይ የሚገኘው የሥራ ዕቅድ ማኅበራቱ የደረሱበትን የዕድገት ደረጃ የማይመጥን በመሆኑ፣ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ አዲስ መሪ ዕቅድ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን አምኖበታል፡፡ በዚሁም መሠረት አዲስ ዕቅድ አዘጋጅቶ ለመንግሥት እንዳቀረበና የመንግሥትን ውሳኔ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡

   በኤጀንሲው የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ሲቀርብ እንደተጠቀሰው እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም. ድረስ ከ18 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሰባሰቡ ከ84 ሺሕ በላይ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ 384  የኅብረት ሥራ ዩኒየኖችና ሦስት የኅብረት ሥራ ፌዴሬሽኖች ተመሥረተው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ እነዚህ ማኅበራት በግብርና ምርት ማሳደጊያዎች፣ ግብዓቶች አቅርቦትና ስርጭት ላይ፣ በግብርና ምርቶች እሴት ጭማሮ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በገንዘብ ቁጠባና ብድር፣ በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትና በሌሎች የሥራ ዘርፎች ተደራጅተው ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማፍራት እንደቻሉ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ከዚህ የማኅበራቱ ካፒታል ውስጥ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነውን ገንዘብ ለኢንቨስትመንት እንዳዋሉም ተገልጿል፡፡ በዚህም ለ1.5 ሚሊዮን ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል ስለመፍጠራቸውም ሪፖርቱ አጣቅሷል፡፡

   ይህን ያህል ካፒታል የሚያንቀሳቅሱት ማኅበራት፣ አሁን ለሚገኙበት ደረጃ የደረሱበት መንገድ ግን ቅጥ ያጣና የተደበላለቀ በመሆኑ ለአሠራርም ለቁጥጥርም አመቺ እንዳልነበር የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ስሩር ገልጸዋል፡፡ እያንዳንዱ ማኅበር በኢኮኖሚውና በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ የሚያደርገው ተሳትፎ ሰፊ ድርሻ እየያዘ በመምጣቱ፣ የተደበላለቀውን አሠራር ማዘመን ግድ እንደሚል አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም ማኅበራቱ እስከ 2025 ዓ.ም. ድረስ የሚጓዙበት አዲስ ፍኖተ ካርታ እንደተዘጋጀላቸው ይፋ ተደርጓል፡፡ ፍኖተ ካርታው በግብርና ምርት ማቀነባበር፣ በሸማቾች ኅብረት ሥራ እንቅስቃሴ፣ በቁጠባና ብድር፣ በወጪ ንግድ እንዲሁም በተለያዩ የኅብረት ሥራ በሚተገበርባቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተሰማሩ ማኅበራት በአሠራርና በቁጥጥር የት ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚጠበቅባቸው የሚያሳይ ዕቅድ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡

ከዘጠኝ ወራት የኤጀንሲው ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው፣ ማኅበራቱ እንዳለባቸው የታየው ክፍተት የቁጥጥርና የክትትል አሠራር አለመኖር አንዱ ነው፡፡ በዚህ ሪፖርት እንደተመለከተው፣ የሒሳብ ምርምራና የኦዲት ሥራ የተደረገባቸው መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየኖች ያስመዘገቡት የገንዘብ ጉድለት መጠን 15 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ ኪሳራቸው ደግሞ ከ8.5 ሚሊዮን ብር በላይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ክፍተት ለምን ተከሰተ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኡስማን፣ ‹‹ችግሩ በከተማና በገጠር የተለያየ ሆኖ ለችግሩ መፈጠር ግን ለቁጥጥርና ክትትል አመራሮች የሚሰጡት ትኩረት አናሳ በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ማኅበሩ ያለው ቀበሌ ወይ ወረዳ ላይ ሲሆን፣ ተቆጣጣሪው ወይም ኦዲተሩ ግን በከተማ የሚገኝ በመሆኑ፣ ባለሙያው ወርዶ ሊሠራበት የሚችልባቸው የትራንስፖርትና ሌሎች አቅርቦቶች ስለማይመደቡ ሥራውን ለመሥራት አዳጋች በመሆኑ የሚፈጠር ችግር ነው፤›› ይላሉ፡፡

አቶ ኡስማን እንደሚያብራሩት፣ በከተማ ያለው ችግር ለየት ይላል፡፡ ‹‹ለምሳሌ አዲስ አበባ ያለው ችግር ሙሉ በሙሉ የማስፈጸም ችግር ነው፡፡ በሺሕ የሚቆጠሩ ማኅበራት ቢኖሩም እነሱን የሚመጥን ተቋማዊ አደረጃጀትና ባለሙያ የለም፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ እነዚህ ማኅበራት ተገቢው ቁጥጥርና ክትትል እንደማይደረግባቸውም ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያለውን ክፍተት መድፈን እንዲቻል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ከኤጀንሲ ባለፈው ዓመት እንዲደራጅ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ ኤጀንሲው ያዘጋጀው መሪ ዕቅድ የእያንዳንዱን የኅብረት ሥራ ማኅበር ኃላፊ በሕግም በአስተዳደራዊ ጉዳይም ተጠያቂ ስለሚያደርግ እስካሁን የተፈጠረው ችግር እንደሚፈታ አቶ ኡስማን ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች