[ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ሚኒስትር ይደውላሉ]
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ደህና ነኝ፤ ለጥብቅ ጉዳይ ነው የፈለኩህ?
- የምን ጥብቅ ጉዳይ ነው?
- መቼም ያንን የሚገርም ዜና ሰምተሃል?
- የቱን ዜና?
- ሊፈቱ መሆኑን ነዋ?
- የቀሩት የፖለቲካ እስረኞች ሊፈቱ ነው እንዴ?
- የምን የፖለቲካ እስረኛ ነው የምታወራው?
- ታዲያ ማን ነው የሚፈታው?
- ባለሀብቱ ሊፈቱ ነው፡፡
- እሱንማ ሰምቻለሁ ግን ወሬው ምን ያህል እርግጠኛ ነው?
- እንግዲህ አለቃችን ካሉ ይፈታሉ ማለት ነው፡፡
- እኔ ግን በእርግጠኝነት ማውራት የሚቻል አይመስለኝም፡፡
- ቃሌ ፊርማዬ ነው ስላሉ፣ በዚህ እንግዲህ እንገመግማቸዋለና?
- እርስዎ ግን ይኼን ያህል ምን አስጨነቅዎት?
- ምነው ምነው የእሳቸውን ውለታ ረሳኸው እንዴ?
- የምን ውለታ?
- ለአገር በለው ለፓርቲያችን ምን ያላደረጉት ውለታ አለ?
- አሁን እሱን ውለታ ቆጥረው ነው እንዲህ የተቆረቆሩላቸው?
- ስማ ለእኔም ቢሆን እኮ አባት ናቸው፡፡
- ማለት?
- ስታመም ሐኪሜ፣ ቤት ባይኖረኝ ቤቴ፣ ልብስ ባጣ ልብሴ፣ የምበላው ባጣ ምግቤ ብቻ ሁሉ ነገሬ ናቸው፡፡
- ምንም አልገባኝም?
- አሁን እውነት ስናወራ መንግሥት የሚሰጠን ደመወዝ አይደለም ለወር ለቀን ትበቃለች እንዴ?
- ምን እያሉ ነው?
- እንደዚህ አንቀባረው የሚያኖሩኝ እሳቸው ናቸው፡፡
- አሁን ምን ይደረግ ነው የሚሉት?
- እንደዚህ ዓይነት የአገር ባለውለታ ሲመጣ ተራ አቀባበል አይደረግም፡፡
- የምን አቀባበል ነው?
- አለቃችን ዜጎቻችንን ማክበር አለብን ሲሉ አልሰማህም?
- ማክበር ካለብዎት ሁሉንም ነዋ ማክበር ያለብዎት?
- ስነግርህ አይገባህም እንዴ? እሳቸው የተለዩ የአገር ባለውለታ ናቸው እኮ ነው የምልህ?
- ታዲያ ምን ይደረግ ነው የሚሉት?
- ወደ አገራቸው ሲገቡ የንጉሥ አቀባበል ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
- ምን ዓይነት አቀባበል?
- ልክ ጀግኖች አትሌቶቻችንን ስንቀበል እንደምናደርገው ዓይነት አቀባበል ነዋ፡፡
- ምን? ምን?
- በቃ መንገድ ተዘግቶ…
- ሥራ ፈተዋል ልበል ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት ማለት?
- መጨነቅ ያለብዎት ሕዝብን ስለማገልገል ነው ወይስ ለአንድ ባለሀብት አቀባበል ስለማድረግ?
- ይኼ የዜግነት ግዴታችን መስሎኝ?
- ሌሎች እስረኞች ተፈተው አገራቸው ሲገቡ መቼ አቀባበል አድርገውላቸው ያውቃሉ?
- እኔ ቢዚ ስለነበርኩ ነዋ፡፡
- ለማንኛውም አሁን ስለዚህ አቀባበል የተጨነቁት ለምን እንደሆነ አውቃለሁ፡፡
- ለምንድነው?
- ለተቆራጭዎ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ለሚስታቸው ስልክ ደወሉላቸው]
- የት ነው ያለሽው?
- ቤት ነኝ፡፡
- አሁን ምርጥ ሥራ አግኝቼልሻለሁ፡፡
- ሥራውን ሁላ ገድላችሁት ደግሞ የምን ሥራ ነው የምትሰጠኝ?
- ዝም ብለሽ ብቻ ስሚኝ፡፡
- ሁሉን ነገር ደፍናችሁት ምን አለ ብለህ ነው?
- እኔ በተደፈነ ነገር ውስጥ ቀዳዳ ማግኘት የምችል ሰው መሆኔን ረሳሽው?
- ምን እያልከኝ ነው?
- አንድ ጥሩ ዝግ የምንዘጋበት ፕሮጀክት አግኝቼ ነው፡፡
- የምን ፕሮጀክት ነው?
- ባለፈው ከአውሮፓ ያስመጣሽው ከፍተኛ ጥራት ያለው ጨርቅ አለ አይደል?
- የትኛው ጨርቅ?
- ሚኒስትሮች ሱፍ ሲገዙ ከእኔ እንዲገዙኝ ብለሽ ነበር ያስመጣሽው?
- ምን ዋጋው ከፍተኛ ስለሆነ የሚገዛኝ አጥቼ አስቀምጬዋለሁ፡፡
- አሁን ጨርቁን የምትጠቀሚበት አጋጣሚ ተገኝቷል፡፡
- የምን አጋጣሚ?
- ወዳጃችን እኮ በቅርቡ አገር ቤት ይገባሉ፡፡
- የትኛው ወዳጃችን?
- ባለሀብቱ ናቸዋ፡፡
- ቢገቡስ ታዲያ?
- ወደ አገር ቤት ሲመለሱ ደማቅ አቀባበል ልናደርግላቸው እያሰብን ነው፡፡
- ምን እያልከኝ ነው ታዲያ?
- በቃ ወዳጅ ነኝ የሚል ሁሉ አንድ ዓይነት ሱፍ እንዲለብስ እናደርጋለን፡፡
- ይኼን ጭንቅላትህን እኮ ለአገሪቷ ብትጠቀምበት፣ አሁን የትና የት በደረሰች ነበር፡፡
- ከራስ በላይ ንፋስ ነው እባክሽ?
- እሱስ ልክ ብለሃል፡፡
- ለሱፉ አላባሽ ደግሞ ብለሽ ያመጣሻቸው የጣሊያን ጫማዎች አሉ አይደል?
- አዎን አሉ፡፡
- እነሱንም በዚህ አጋጣሚ መቸብቸብ ነው፡፡
- ያልገባኝ ግን ለሰውዬው ሚዜ ልትሆኗቸው ነው እንዴ?
- አሁን ያልተጠየቅሽውን አትዘባርቂ?
- ይቅርታ እሺ፡፡
- ባለፈው ማተሚያ ቤቱ አፉን ከፍቶ ቁጭ ብሏል ብለሽኝ ነበር አይደል?
- ሥራ ጠፍቷል፡፡
- ለባለሀብቱ አቀባበል የሚሆኑ ፖስተሮችን አትመሽ በየቦታው ትሰቅያለሽ፡፡
- የምን ፖስተር ነው?
- እንኳን ለአገርዎ በሰላም አበቃዎ የሚል ነዋ፡፡
- እንዲህ ዓይነት ፖስተር ማን ያሳትማል ብለህ ነው?
- እኛ ካሳተምን ሌላው መከተሉ አይቀርም፡፡
- እኔማ ደስ ይለኛል፡፡
- ከእኛ የሚጠበቀው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡
- ምንድነው እሱ?
- ፈር መቅደድ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር ሰሞኑን ጠፍተዋል፡፡
- እንዴት አልጠፋ?
- ምን ገጠመዎት?
- በስተርጅና ትምህርት ቤት ገብቼ ነዋ፡፡
- የምን ትምህርት ነው?
- ቤትህ ቴሌቪዥን የለህም እንዴ?
- ኧረ አለኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ታዲያ ምን ስታይ ነው የምታመሸው?
- ፊልም፣ ኳስ፣ አንዳንዴም ቢቢሲና ሲኤንኤን አያለሁ፡፡
- የአገር ውስጥ ቻናል አታይም?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ብታይ ኖሮ ሰሞኑን ሌክቸር ስወስድ ታይ ነበር፡፡
- የምን ሌክቸር ነው?
- በቃ ምንም የማላውቅ እስኪመስለኝ ድረስ ነበር ስማር የነበረው፡፡
- ማን ነው የሚያስተምርዎት?
- አለቃችን ለሚኒስትሮች ሰሞኑን ትምህርት ሲሰጡ ነበር፡፡
- ለነገሩ በእሱ ስብሰባ ላይ ብዙ ሰዎች ጥያቄ ሲያነሱ ነበር፡፡
- የምን ጥያቄ?
- አለቃችሁ የነገሯችሁን ነገሮች ሳታውቁ እንዴት ሚኒስትር ልትሆኑ ቻላችሁ እያሉ ነዋ፡፡
- አንተ የእኔን ቦታ ትፈልገዋለህ እንዴ?
- ኧረ እኔ ሳልሆን ሕዝቡ ይኼን ሳያውቁ እንዴት ሚኒስትር ሆኑ እያለ ነው፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- አንድ መሪ ምን ዓይነት ችሎታ ሊኖረው እንደሚገባ፣ ስለጊዜ አጠቃቀሙ፣ ስለትጋት ምናምን በአግባቡ ሳያውቅ እንዴት መሪ ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ ነው ሕዝቡ የጠየቀው፡፡
- ሌላስ ምን ይላል?
- ባለሥልጣናቱ የሕዝብ አገልጋይ ሳይሆኑ በሕዝቡ ተገልጋይ መሆናቸው ተጋለጠ እየተባለ ነው፡፡
- የእኛ ሕዝብ ሁሌም ነገር ማወሳሰብ ይወዳል፡፡
- ደግሞ ከፓርላማ ጋር ሥራ ተቆጣጥራችሁ ትረካከባላችሁ ተብሏል አሉ፡፡
- ምን ችግር አለው?
- በሚቀጥለው ዓመት ከፓርላማው ጋር የሥራ ኮንትራት ልትፈራረሙ ነው ተብሏል፡፡
- ስንትና ስንት ውል የምፈራረምና በፊርማዬ የታወቅኩ ሚኒስትር አይደለሁ እንዴ?
- ይህችኛዋ ግን ትንሽ የምታስቸግር ይመስለኛል፡፡
- እኔን ብዙ አታውቀኝም ማለት ነው? እኔ እኮ በቢሊዮን ገንዘብ የሚያወጡ ፕሮጀክቶችን የተፈራረምኩ ሰው ነኝ፡፡
- ታዲያ የቢሊዮን ገንዘብ ፕሮጀክቶቹ አንዳቸውም ተግባራዊ መሆን አልቻሉም፡፡
- ቀስ እያሉ ይሠራሉ፣ ምን ፕሮጀክት ማራዘም እኮ የተለመደ ነው፡፡
- ለማንኛውም ይኼን ኮንትራት የሚፈርሙ ከሆነ፣ በዚያው አንድ ነገር መከታተል አይርሱ?
- ምን?
- የሥራ ማስታወቂያ!
[ክቡር ሚኒስትር ለአንድ ደላላ ወዳጃቸው ይደውላሉ]
- ስማ መቼም ሰሞኑን የአለቃችንን ሌክቸር ሰምተኸዋል?
- በፓወር ፖይንት አልነበር እንዴ ፕረዘንቴሽኑ?
- አሁን የፕረዘንቴሽኑን ሶፍት ኮፒ አግኝቻለሁ፡፡
- ምን ያደርግልዎታል?
- ለሁለታችንም ይጠቅመናል፡፡
- ምኑ ነው የሚጠቅመን?
- እስከዛሬ ስንፈልገው የነበረው ይኼንን ነበር፡፡
- ምንም አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ስማ አንድ መሪ ምን እንደሚያስፈልገው በግልጽ የተዘረዘረበት ነው፡፡
- ታዲያ ይኼ ለመሪ እንጂ ለእኔ ምን ይጠቅማል?
- አንተም በተሰማራህበት ዘርፍ መሪ መሆን ትችላለህ፡፡
- በድለላ?
- አዎን፣ እንዴት ጊዜህን መጠቀም እንዳለብህ? ጊዜ ሳያልፍብን እንዴት ሥራ መሥራት እንዳለብን? ብቻ በአጠቃላይ አንድ ላይ ለምንሠራው ሥራ ብዙ የሚጠቅመን ነገር አለ፡፡
- ካሉ እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስማ እያንዳንዱ ሥራ መሠራት ያለበት በፎርሙላ ነው፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- አሁን አለቃችን ለመሪነት ፎርሙላ አውጥተውልናል፡፡
- ይኼ ታዲያ ለእኔ ምን ያደርግልኛል?
- ለእኛም ሥራ ፎርሙላ ማውጣት አለብን፡፡
- የምን ፎርሙላ?
- የሙስና!