Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፍትሕ ሚኒስቴር የሚወጡ ሕጐች የጥራት ችግር እንዳለባቸው አመነ

ፍትሕ ሚኒስቴር የሚወጡ ሕጐች የጥራት ችግር እንዳለባቸው አመነ

ቀን:

– የጠበቆች ፈቃድ አሰጣጥን እንዲመረምር መመርያ ተሰጠው

ፍትሕ ሚኒስቴር በአገሪቱ ውስጥ እየወጡ ያሉ ሕጐች የጥራት ችግር እንዳለባቸው ለፓርላማው አመነ፡፡ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ የበጀት ዓመቱን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ታኅሳስ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት፣ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል ለፓርላማ የሚቀርቡ ረቂቅ አዋጆች ጥራት ማነስ አንዱ ነው፡፡

የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ ለፓርላማው የሚቀርቡ አዋጆች በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል አልፈው የሚመጡ ቢሆንም፣ ፓርላማው ለአብነት ያህል በቅርቡ የተመለከተው የውጭ ሥራ ሥምሪት አዋጅ ላይ ከ20 በላይ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ ማድረጉን አውስተዋል፡፡ አንዳንድ ደንቦችና መመርያዎችም ከአዋጅ በላይ የሚሆኑበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው በሰጡት ምላሽ ሕጐች በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል ፀድቀው ወደ ፓርላማ ከመላካቸው ቀደም ብሎ፣ ፍትሕ ሚኒስቴር አይቶዋቸው እንዲያልፉ መደረግ የጀመረው ከ2007 ዓ.ም. በኋላ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹የጥራት ችግሮች መኖራቸው እውነት ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ፍትሕ ሚኒስቴርም የአቅም ችግር አለበት፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ ጋር በሕግ ማርቀቅ ሥራ ላይ የመተባበር ሥራ ጀምረናል፤›› ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው፣ ላለፉት ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡት የአስተዳደር ሕግ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ፣ እንዲሁም የንግድ ሕግ በማሻሻል ረገድ አሁንም የተሠራ ሥራ አለመኖሩ ትክክል አይደለም ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ‹‹በሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሐ ግብር ረገድ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ሪፖርት ተገቢ አይደለም፡፡ ምንም የተሠራ ሥራ የለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ አጽንኦት ይስጥበት፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ የአስተዳደር ሕግ ረቂቅ መዘጋጀቱን ነገር ግን የፖሊሲ ጉዳዮች ሳይለይ የተዘጋጀ በመሆኑ፣ ይህንን ፖሊሲ የማዘጋጀት ኃላፊነት ፍትሕ ሚኒስቴር ወስዶ መሥራቱን አስረድተዋል፡፡ የሚቀረው በክላስተር ደረጃ ረቂቁ እንዲታይ፣ ቀጥሎም ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት መምራት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የንግድ ሕጉን በተመለከተ እስከ ዛሬ የንግድ ሕጉን የማሻሻል ሥራ እየተሠራ ነው ይባል የነበረው ስህተት መሆኑን፣ ሥራው የተጀመረው በ2007 ዓ.ም. እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ሥራው ከተጀመረ በኋላ በንግድ ሕጉ አምስቱም መጽሐፎች የፖሊሲ ጉዳዮች ተለይተው የማሻሻያ ሥራውም በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ ረቂቅ ከተጠናቀቀ አንድ ዓመት እንዳለፈውና ረቂቁ 421 አንቀጾችን ከነማብራሪያዎቹ የያዘ እንደሆነ፣ የሚቀረው ነገር ባለድርሻዎችን ማወያየትና ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት መላክ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት የአምስት ዓመት የድርጊት መርሐ ግብር ለማዘጋጀት እስካሁን አለመቻሉን፣ ምክንያቱ ደግሞ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተወከሉ ባለድርሻዎች በተለያዩ ምክንያቶች በመልቀቃቸው ሌሎች ተተክተው ሥራ እስኪጀምሩ ጊዜ መውሰድን አስመልክቶ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ አቶ ተስፋዬ ዳባ፣ እንዲሁም ሚኒስቴሩን የሚከታተለው የሕግና ፍትሕ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተቀባይነት የሌለው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በሰጠው አስተያየት የዜጐችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ ባለመሆኑ በትኩረት እንዲሠራ አሳስቧል፡፡ በሌላ በኩል በሚኒስቴሩ ሪፖርት መሠረት በስድስት ወራት ውስጥ 177 ቅሬታ ከቀረበባቸው ጠበቆች ውስጥ 101 ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸው፣ የጥብቅና ፈቃድ አሰጣጡ ችግር ያለበት መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ ሚኒስቴሩ ራሱን እንዲመለከት መመርያ ተሰጥቶታል፡፡

ለጠበቆች የዲሲፕሊን ጉባዔ ቀርበው ውሳኔ የተሰጠባቸው 70 እንደሆኑና በሥነ ምግባር ችግር 17፣ ፈቃድ ባለማሳደስ 21፣ ለጊዜው የታገዱ 24፣ ጥፋተኛ ተብለው የታገዱ ስምንት መሆናቸውን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...