በኢትዮጵያ ታሪክ ፈረስ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ለነገሥታትና መኳንንቱ የክብራቸውም የጀግንነታቸውም መገለጫ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ነገሥታቱ ለፈረስ ካላቸው ወዳጅነት የተነሳ ስማቸውንና ማንነታቸውን በፈረሶቻቸው ቅፅል ስም ሲጠሩም ኖረዋል፡፡
አባ ታጠቅ ካሳ ለአፄ ቴዎድሮስ፣ አባ በዝብዝ ካሳ ለአፄ ዮሐንስ፣ አባ ዳኘው ለአፄ ሚኒልክ እንዲሁም አባ ጠቅል ለአፄ ኃይለሥላሴ ከተሰጡት መካከል የሚጠቀሱ ስያሜዎች ናቸው፡፡ ፈረስ ነክ ስፖርቶችም በኢትዮጵያ ሲዘወተሩ የዓመታት ጊዜ ታሪክ አላቸው፡፡ የፈረስ ጉግስና የፈረስ ሽርጥ ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ ስፖርት ቀደምቶቹ ነገሥታትና መኳንንቶቻቸው በጅሌዎቻቸውና በወታደሮቻቸው መካከል የሚደረገውን የፈረስ ጉግስና የፈረስ ሽርጥ ጨዋታ አጥብቀው ሲወዱት ኖሯል፡፡
በምንገኝበት ዘመንም በተለይ በአውሮፓና በሌሎችም ታላላቅ አገሮች የፈረስ ስፖርት ከሚወደዱና ከሚዘወተሩ ስፖርቶች በግንባር ቀደምትነት እየተጠቀሰ ይገኛል፡፡ ለዚህም በአሜሪካ የሚካሄደው ዓመታዊው ‹‹የኬንታኪ ደርቢ›› ውድድር አንዱና ዋናው ነው፡፡ በተመሳሳይም በእንግሊዝና ዱባይ በስፋት የሚዘወተር ስፖርት ከሆነም ሰነባብቷል፡፡ ስፖርቱ ምንም እንኳ በተደራጀና በተጠና መልኩም ባይሆን በኢትዮጵያ ቀድሞ ወደነበረበትና ከዚህም አልፎ በተሻለ አደረጃጀት ተወዳጅነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መታየት ጀምረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአገሪቱ ዘጠኝ ክለቦች ተቋቁመው የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማካናወን ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን ይገልጻል፡፡ ከእነዚህ የፈረስ ስፖርት ክለቦች አጭር የምሥረታ ዕድሜ እንዳለው የሚነገርለት የቤካ ፈርዳ ራንች የፈረስ ስፖርት ክለብ አንዱ ነው፡፡ የክለቡ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደግሞ አቶ ፀጋሁን ተሰማ ይባላሉ፡፡ በዋናነት በተለያዩ ጥናትና ምርምር የሥራ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ ፀጋሁን ከልጅነታቸው ጀምሮ የፈረስ ስፖርት አዘውታሪ መሆናቸውን ሳይቀር ይናገራሉ፡፡
በዚህ ሳይገደቡ በኢትዮጵያ ቀደምት ታሪክ ያለውን ይህንኑ የፈረስ ስፖርት በዘመናዊ መልኩ ለማደራጀት በመንቀሳቀስ ላይ ስለመሆናቸው ጭምር ያስረዳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅትም ከኦሮሚያ ክልል በሱሉልታ ወረዳ ጉራራ ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ በተረከቡት አራት ሔክታር መሬት ላይ ዘመናዊ የፈረስ ስፖርት ማዘውተሪያ አጠናቀው ባለፈው እሑድ ጥር 8 ቀን 2008 ዓ.ም. የመጀመሪያውን ዘመናዊ የፈረስ ዝላይ ውድድር አከናውነዋል፡፡ በሁለት ምድብ ማለትም በወጣቶችና አዋቂዎች ተከፍሎ በተካሔደው የቤካ ፈርዳ ራንች የፈረስ ዝላይ ውድድር 58 የአገር ውስጥና የውጭ ዝርያ ያላቸው ፈረሶች ተካፋይ እንደነበሩም አቶ ፀጋሁን ገልጸዋል፡፡
የፈረስ ስፖርት በተቀረው ዓለም ውድ ከሚባሉ ስፖርቶች አንዱ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ በዚያ ደረጃ እንዳልሆነ አቶ ፀጋሁን ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከፈረስ ጋር የተቆራኘ ልዩ ታሪክ ያላቸው በመሆናቸው ነው ይላሉ፡፡ ይህ የቆየውና ተወዳጁ ባህል በአሁን ወቅት እየተዳከመ የመጣበት ሁኔታ ሰለመኖሩ ግን አልሸሸጉም፡፡ በመሆኑ ይህን ታሪክ ማስቀጠል የሚቻለው ለወጣቱ ትውልድ ስለፈረስ ስፖርትና በኢትዮጵያ የነበረውን መልክና ይዘት በቂ የግንዛቤ ማስጨበጢያ ሥራ መሥራት ሲቻል እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ፀጋሁን፣ ቤካ ፈርዳ ራንች በዋናነት የተቋቋመው ለዚሁ ሲባል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል ዘሚካኤልም ይህንኑ ይጋራሉ፡፡ ‹‹ታሪካዊው የኢትዮጵያ የፈረስ ስፖርት ወደ ቀድሞ ስሙና ዝናው እንዲመለስ ከተፈለገ እንደ ቤካ ፈራዳ ራንች ሁሉ ሌሎች የግል ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ መምጣት ይኖርባቸዋል፤›› ይላሉ፡፡