የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የ92ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ባከበሩበት ዕለት የመኖሪያ ቤታቸው በሚገኝበት ግቢ ያስገነቡት ዲጂታል ቤተመጻሕፍትና የሰላም አዳራሽ ተመርቋል፡፡ ጥር 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በቤታቸው በተዘጋጀው መርሐ ግብር የተመረቀው ቤተ መጻሕፍቱ፣ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ጥናት ለሚሠሩ ግለሰቦች አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ለቤተመጻሕፍቱ መጻሕፍት የተገኘው፣ ከኢትዮጵያ እውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከል ሲሆን፣ የድርጅቱ መሥራችና የቦርድ ኃላፊ ኢንጂነር ብርሃነ አባተ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ወደ 500 የሚጠጉ መጻሕፍት በነፃ ሰጥተዋል፡፡ መጻሕፍቱን በፍላሽና በሚሞሪም መውሰድ ይቻላል፡፡ የመርሐ ግብሩ አዘጋጅ ታሪኳ ኢቨንት ኦርጋናይዘር ዋና ሥራ አስኪያጅ ታሪኳ ገብረየስ ለሪፖርተር እንደገለጸችው፣ የሰላም አዳራሹ ሰላምና እርቅን ማዕከል ላደረጉ እንቅስቃሴዎች አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ጦር ኃይሎች አካባቢ የተገነቡት ማዕከሉና ቤተመጻሕፍቱ ወደ ግማሽ ሚሊዮን ብር እንደወጣባቸውና ከምርቃቱ ዕለት በኋላ ለሕዝብ ክፍት እንደሆኑ አክላለች፡፡ ባለፉት ዓመታት በሦስት የተለያዩ መንግሥታት ሥር አገልግሎት የሰጡት አቶ ግርማ፣ ልደታቸው በተከበረበት ዕለት የተለያዩ ሃይማኖቶች መሪዎች፣ ባለሥልጣናትና ወዳጆቻቸው ተገኝተው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ኦርኬስትራ አባላት ተገኝተው ሙዚቃ ያስደመጡ ሲሆን፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ለሕዝብ የሚጠቅም ነገር ማበርከታቸው እንደሚያስመሰግናቸው አንዳንድ እንግዶች ተናግረዋል፡፡