Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየመንገድ ላይ አዝማሪዎች

የመንገድ ላይ አዝማሪዎች

ቀን:

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ማስረሻ ምንተስኖትና ጓደኞቹ በየዓመቱ ታኅሣሥ 19 ቀን የሚከበረውን የቅዱስ ገብርኤል በዓል ለመካፈል በሐረር ከተማ ቁልቢ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተዋል፡፡ በዓሉን የሚያከብሩ ምዕመናን በቡድን ተሰብስበው በተለያዩ ድንኳኖች ውስጥ ያርፋሉ፡፡ እሱና ጓደኞቹ ያረፉበት ድንኳን ውስጥ የምሽቱን ብርድ ለመከላከል በሚል ቢራ ይጠጡ ነበር፡፡ ድንገት ድንኳኑ መግቢያ አካባቢ የሰሙት የማሲንቆ ድምፅ ትኩረታቸውን ሳበው፡፡ ማሲንቆ ያነገበ አንድ አዝማሪ ወደ ድንኳኑ ዘልቆ ሲዘፍን ለማመን ተቸግረው እርስ በርስ ይተያዩ ጀመር፡፡ ጥንዶች ፍቅራቸው እንዲዘልቅ መረቀ፡፡ ሌሎችንም እያወደሰና እየሸነቆጠ ገንዘብ እንዲሰጠው የሚገፋፉ ግጥሞችን ማውረዱን ቀጠለ፡፡

አንዳንዶች በሃይማኖት ቦታ ያውም በንግሥ በዓል ላይ እንዴት አዝማሪ ይመጣል ብለው ሲተቹ፣ በሌላ በኩል በአዝማሪው ግጥም የተዝናኑ ተደስተው ገንዘብ የሸለሙም ነበሩ፡፡ ማስረሻ በበኩሉ አዝማሪውን ቢራ እንደጋበዘው ይናገራል፡፡ አዝማሪውም ድንኳኑ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ካደረሰ በኋላ ወደ ቀጣዩ ድንኳን ተሻገረ፡፡ አዝማሪን ባልጠበቀበት ቦታ ካገኘባቸው አጋጣሚዎች ይህን ይጠቅሳል፡፡ አዝማሪዎችን በምሽት መዝናኛዎች፣ በመጻሕፍት ምረቃ፣ በስብሰባ አልያም ሌሎች ዝግጅቶች ማግኘት የተለመደ ሆኗል፡፡

አሁን አሁን ደግሞ አዝማሪዎች የመገበያያ ሕንፃዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎች አንዳንዴም ፀጥ ረጭ ባሉ መንገዶች መገኘት ጀምረዋል፡፡ ጥንዶችን ወይም በቡድን የሚጓዙ ሰዎችን እየተከተሉ ያቀነቅናሉ፡፡ ብቻቸውን የሚጓዙ ግለሰቦችን በዜማ እያጀቡ የሚሄዱበት ድረስም ይሸኛሉ፡፡ ምሽት ላይ ከአንድ መዝናኛ ቦታ ወደ ሌላ ለሚቀይሩ ግለሰቦች በማሲንቋቸው እያጀቡ የተሰጣቸውን ገንዘብ ይቀበላሉ፡፡ መኪናቸውን ካቆሙበት ሥፍራ የሚያነሱ ሰዎች ጉዞ እስከሚጀምሩ፣ በመስኮታቸው በኩል ይዘፍኑላቸዋል፡፡ ለአዝማሪዎቹ ከአሥር ብር ጀምሮ ገንዘብ የሚሰጡ ግለሰቦች እንዳሉ ሁሉ ፊት የሚነሷቸውም ጥቂት አይደሉም፡፡ አዝማሪዎቹም ገንዘብ የሰጣቸውን አወድሰው፣ የነፈጋቸውንም ወቅሰው ወደ ሌላ ሥፍራ ያመራሉ፡፡

በአዝማሪ ቤቶች ወይም ልዩ ልዩ የባህል መዝናኛዎች አዝማሪዎች በቋሚነት የሚሠሩ ሲሆን፣ አንዳንድ አዝማሪዎች ደግሞ ከእነዚህ ቦታዎች ውጪ ያለውንም አማራጭ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡን ሰዎች መካከል መዝናናት ፈልገው ወደ መዝናኛ ቦታ የሚሄዱ ሰዎችን ማዝናናት ተገቢ ቢሆንም፣ መንገድ ላይ ለሚጓዝ ሰው ማቀንቀን የሰዎችን መብት መጋፋት ነው ያሉ ነበሩ፡፡ በተቃራኒ አዝማሪዎቹ ለራሳቸው መድረክ መፍጠራቸውን የሚደግፉም አሉ፡፡

ማስረሻ፣ አዝማሪዎች ገበያ ሊገኝ የሚችልባቸውን ቦታዎች ፈልገው ሥራቸውን እያስፋፉ መምጣታቸውን ከሚስማሙ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ‹‹በገበያው ያለውን ውድድር ለማሸነፍ በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ የሚዘፍኑበትን መንገድ እያመቻቹ ነው፤›› ይላል፡፡

አዝማሪዎች መንገድ ላይ መዝፈናቸው የሰውን ግላዊነት ይነካል ብሎ እንደማያምን ይናገራል፡፡ በተለያየ ጊዜ መንገድ ላይ ያጋጠሙት አዝማሪዎችም እንዳልረበሹት፣ የበለጠ ትኩረት የሚሰጠውም ለግጥሞቻቸው እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ‹‹ሰዎች እንዲኖራቸው የሚፈልጉትን ቁስ ወይም ማንነት እያላበሱ ሲያሞግሱ ገንዘብ የማግኘት ዕድላቸው ይሰፋል፤›› ይላል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት ‹‹አዝማሪ ምን አለ?›› ይባል ነበር፡፡ ስለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በቅኔ ለበስ ግጥሞቻቸው መልዕክት ስለሚያስተላልፉም የሕዝብን የልብ ትርታ ለማድመጥ ሁነኛ መንገድ እንደሆኑም ይታመናል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ እንደ ስኬት ከሚቆጠሩ ነገሮች እንደ ቤት፣ መኪና፣ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ በመጥቀስ አዝማሪዎች ሰዎችን ሲያሞጋግሱ ይደመጣል፡፡

‹‹ባለ ራቫ ፎርና ባለ ፎቅ በሚል ግጥም አሞግሰው በቀላሉ ከሰው ገንዘብ ማግኘት ይችላሉ፤›› የሚለው ማስረሻ፣ በተለይ መንገድ ላይ ሰው ካለው አጭር ጊዜ አንፃር ቶሎ አሞግሰው ገንዘብ ለማግኘት እንደሚጥሩ መታዘቡን ይናገራል፡፡ ከሙገሳ በተጨማሪ ኅብረተሰቡን እንደሚመክሩም ይናገራል፡፡ ካጋጠሙት አዝማሪዎች መካከል ስለመኪና አደጋ መብዛት፣ ስለመጠጥና ዝሙት አደገኛነት ሲናገሩ የሰማቸውን ይጠቅሳል፡፡ በየጊዜው የሰውን የትኩረት አቅጣጫ እንደሚከተሉም ያክላል፡፡

የተለየ ሐሳብ የሰጠችን አያንቱ ወዳጆ ናት፡፡ በአንድ ወቅት 22 አካባቢ ከአንዲት ጓደኛዋ ጋር ሲሄዱ አንድ አዝማሪ እየተከተላቸው መዝፈን ይጀምራል፡፡ ፍላጐት ስላልነበራቸው ፍጥነታቸውን ጨምረው ተራመዱ፡፡ አዝማሪውም ወፈር ያለችውን የአያንቱን ጓደኛ ክብር የሚነኩ ግጥሞች ማውረድ ጀመረ፡፡ በእሷ እምነት፣ ፍላጐት እንደሌላቸው ሲገነዘብ አክብሮ ወደ ሌላ ሰው ማምራት ነበረበት፡፡

አዝማሪዎች፣ ከጓደኞቻቸው ጋር የሚጨዋወቱ ወይም ወደ አንድ ጉዳይ የሚጣደፉ ሰዎችን እየተከተሉ ማወደስ ወይም ማውገዝ ትክክል አይደለም ትላለች፡፡ እዛው 22 አካባቢ ወደ መኪናው ለመግባት የሚጣደፍ ሰውን እየተከተለ የሚዘፍን አዝማሪ በሰውየው ሲመታ ማየቷንም ታስታውሳለች፡፡ ‹‹ሰዎች ስለግል ጉዳያቸው ሊያስቡ ራሳቸውን ማዳመጥ ሊፈልጉ ስለሚችሉ አዝማሪዎች ተፈልገው ካልሆነ ባገኙት ቦታ ባይዘፍኑ ይመረጣል፤›› ትላለች፡፡

አንዳንድ ግጥሞቻቸው ጾታዊ ግንኙነትና ወሲብ ላይ ማተኮራቸውንም አትቀበለውም፡፡ የሰው አካላዊ ሁኔታ ላይ ያተኮሩና ክብር ይነካሉ የምትላቸው ግጥሞች ተገቢ እንዳልሆኑ የምትገልጸው አያንቱ፣ ከማኅበረሰቡ ቁጥብነት አንፃርም ትቃወማቸዋለች፡፡ ‹‹ኢ ሞራላዊና የሥነ ምግባር ጥያቄ የሚያስነሱ›› ከምትላቸው ግጥሞች መካከል በወንድና ሴት መካከል ስላለው ግንኙነት ባልተገባ መንገድ የሚገልጹት ይጠቀሳሉ፡፡ በቡድን ከሚሄዱ ሰዎች መካከል አንዱ ተነጥሎ የተዘለፈበትን አጋጣሚ እንዳስተዋለች ገልጻ፣ ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ለመንቀሳቀስ እንዲሸማቀቁ ማድረግ የለባቸውም ትላለች፡፡

ስሜ አይጠቀስ ብሎ ተሞክሮውን ያካፈለን አዝማሪ ከጐንደር ወደ አዲስ አበባ ከመጣ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ያገኘነው ቦሌ ሸገር ሕንፃ አካባቢ ሲሆን፣ ሰሞነኛው ዝናብ ሥራው ላይ ተጽእኖ እንዳሳደረ ይናገራል፡፡ ፍላጐቱ ታዋቂ የባህል ቤት መሥራት ቢሆንም፣ ሥራ ማግኘት ባለመቻሉ መንገድ ላይ እየተዘዋወረ መዝፈን ጀምሯል፡፡ ‹‹አዲስ አበባ ውስጥ ሁሉም ነገር የሚካሄደው በትውውቅ ነው፤›› ሲል የሚያውቀው ሰው ባለመኖሩ መንገድ ላይ ለመሥራት መገደዱን ይናገራል፡፡

በብዛት ዓርብና ቅዳሜ እንዲሁም በበዓል ሰሞን አመሻሽ ላይ ሥራውን ይጀምራል፡፡ የውጭ ዜጐች፣ በቡድን የሚሄዱ ሰዎችና ጥንዶችን ይመርጣል፡፡ የሰዎችን ፊት በማንበብ ፍላጐት ከሌላቸው ዘወር እንደሚል ይናገራል፡፡ ምሽት ላይ ከመዝናኛ ቤቶች የሚወጡ ሰዎች ሞቅታ ውስጥ ስለሚሆኑ፣ ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደሚሰጡት ይገልጻል፡፡ አንዳንዴ ለረጅም ሰዓት አዘፍነውት ምንም ገንዘብ የማይሰጡ መኖራቸውንም ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡ አሁን በሥራው መጠነኛ ገቢ ቢያገኝም፣ ቋሚ ቦታ ቢሠራ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆን ያምናል፡፡

‹‹ሰዎች ፍቅረኛቸው ወይም ወዳጆቻቸው ፊት አዝማሪ ሲዘፍንላቸው ክብር ተሰምቷቸው ወይም አፍረው ገንዘብ እንዲሰጡ የሚገፋፉ ግጥሞች ይዘወተራሉ፤›› ይላል ስለሥራው ሲገልጽ፡፡ በተለይም ዳያስፖራዎች ቋሚ ደንበኞቹ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ግጥሞቹን ሰዎች በሚያገኝበት ቅጽበት ቢፈጥራቸውም፣ አስቀድሞ የሚያዘጋጃቸውም አሉ፡፡ ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች ውስጥ ሀብት፣ ጀግንነት፣ ውበትና ፍቅርን ይጠቅሳል፡፡

ስለሀብት ሲያነሳ እንደ አላሙዲ፣ ስለውበት ሲገጥም ደግሞ እንደ ቢዮንሴ ይላል፡፡ በጀግንነት ረገድ አፄ ቴዎድሮስ፣ በፍቅር በኩል ደግሞ አብርሃምና ሣራ ይነሳሉ፡፡ ‹‹እነዚህን የመሰሉ ሙገሳዎች ሲሰሙ እጃቸው የሚፈታ ብዙዎች ናቸው፤›› ይላል፡፡ ሙገሳ አበዛለሁ ቢልም፣ ፊት የሚነሱትን ሰዎች ሸንቆጥ እንደሚያደርግም አልሸሸገም፡፡

አስተያየት የሰጠችን ስናፍቅ ካሳ አዝማሪዎች የማኅበረሰቡን የዕለት ከዕለት ሕይወት እንደሚያንፀባርቁ ታምናለች፡፡ ሁሉም ሰው ወደ ባህል መዝናኛዎች ስለማይሄድ አዝማሪዎች በየቦታው መገኘታቸው ተደራሽነታቸውን ያሰፋዋል ትላለች፡፡ ‹‹የፈጠራ ችሎታቸው ያስደንቀኛል፤ ገንዘብ የት እንደሚገኝ አውቀው ሰውን አግባብተው ይሉኝታ አስይዘውም ይጠቀማሉ፤›› ስትል ትገልጻች፡፡

ጥቂት አዝማሪዎች መንገድ ላይ የገጠሟት ሲሆን፣ የእያንዳንዳቸውን ግጥም ሰምታ በጣም ላስደሰቷት ገንዘብ ስትሰጥ፣ ያልጣሟትን አልፋለች፡፡ በእሷ እምነት፣ የአዝማሪዎቹ ዓላማ ገንዘብ ማግኘት ቢሆንም፣ ሁልጊዜ ሰውን ማሞገስ አይጠበቅባቸውም፡፡ ቀልቤን ስበውኛል ካለቻቸው አዝማሪዎች መካከል በአንድ ክልል ስለነበረ ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ ስለኮንዶሚንየም ኑሮና ስለባቡር የዘፈኑትን ታነሳለች፡፡ በቀላሉ ቤት የሚመቱ ቃላት ሲጠቀሙና ቅኔ አዘል ግጥሞች ሲያሰሙ ደስ ይላታል፡፡ ሆኖም የሙዚቃ ችሎታ የሌላቸው መኖራቸውንም ትጠቅሳለች፡፡ መንገድ ላይ የሚዘፍኑት የሚቀጥራቸው ስለሌለ እንደሆነና ጥቂት አዝማሪዎች ገንዘብ ሲያገኙ ተመልክተው እንደገቡበት ትገምታለች፡፡

ከሞላ ጐደል ለአዝማሪዎቹ በጐ አመለካከት ቢኖራትም፣ ከጓደኞቿ በተደጋጋሚ የሰማችውን ትችት ከግምት ማስገባቷ አልቀረም፡፡ አንዳንዶቹ የመጠጥ ችግር እንዳለባቸውና ሰውን እንደማያከብሩ ሰምታለች፡፡ በሌላ በኩል በግሏ ከገጠሟት አዝማሪዎች መካከል የሙሉ ጊዜ ሙዚቀኛ በሆነ ያስባላትን ወጣትም ታስታውሳለች፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ስለኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ሲወሳ የአዝማሪዎች ድርሻም ተያይዞ ይነሳል፡፡ ከማዝናናት ባለፈ በግጥሞቻቸው ይዘት በማኅበረሰቡ የሚፈሩበትም ጊዜ አለ፡፡

በተዘዋወርንባቸው አካባቢዎች እንዳስተዋልነው የመንገድ ላይ አዝማሪዎች እየተበራከቱ ነው፡፡ ሥራቸውን ስለሚያከናውኑበት መንገድ ትክክለኛነት የተለያዩ ሐሳቦች ቢኖሩም፣ ግጥሞቻቸው ወቅቱን ገላጭ ስለመሆናቸው የሚስማሙ አሉ፡፡ መንገድ ላይ መሥራታቸውን እንደ ቢዝነስ አማራጭ የሚወስዱ እንዳሉ ሁሉ፣ የችሎታ ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎችም ይደመጣሉ፡፡

ቺቺኒያ አካባቢ ያገኘነው አዝማሪ አየነው አስተያየቱን በስፋት ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆንም፣ በተለያዩ አዝማሪ ቤቶች መሥራቱን ይናገራል፡፡ ብዙዎቹ ነፃነት እንደማይሰጡትና በሚያሻው መንገድ ለመሥራት ጎዳና እንደመረጠ ያክላል፡፡ በአንዳንድ ዝግጅቶች ላይ እንዲሁም በሠርግ ወቅት መናፈሻዎች ውስጥ እየተዘዋወረም ይሠራል፡፡                 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...