Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ፀጉር ስንጠቃ!

እነሆ መንገድ። ከቦሌ ድልድይ በጎሮ ሰሚት ልንጓዝ ነው። ‹‹የመገናኛና ገርጂ ታክሲ ናፋቂዎች እዚህ ጋ ሠልፍ ያዙ፤›› ይላል ወጠምሻው ተራ አስከባሪ። ‹‹በጉልበት ነው በፀባይ?›› ምሬት የሚታይበት ጎልማሳ ሳምሶናይቱን ጭብጥ አድርጎ ይዞ ይመልሳል። ‹‹ምርጫው የእናንተ ነው አባት። ያልተሠለፈ እሪ እንቧ እያለ ወድቆ ቢነሳ ዓይኔ እያየ አይሳፈራትም፤›› ተራ አስከባሪው የሥልጣኑን ጥግ ያበስራል። ‹‹እንዴ? እንዴት እንዴት ነው የሚናገረው? ከብት መሰልንህ እንዳሻህ የምታግደን?›› ደርበብ ያሉ ወይዘሮ ተጨመሩበት። ‹‹እንግዲህ ሰው ነን ካላችሁ መሠለፍ አዲስ ነገር አይደለም። ምናለበት የበላኋትን ከምታተኑዋት በቀላሉ እዚህ ጋ ብትሰመሩ?›› ግራና ቀኙን አወዛውዞ የሐሳብ መስመር አሰመረ። ‹‹ሃሎ! ትለምናቸዋልህ እንዴ?›› ብሎ ባልደረባው እየነጠረ አጉረጥርጦ መጣ።

‹‹ምዕመናን ሠልፍ ማለት እኮ ዘርዘር ብሎ የመቆም ተቃራኒ ሥርዓት ነው። አሁን ስለ ሥርዓት ለእናንተ ይነገራል? ለእኛም ሥራ ይቀላል፡፡ ለእናንተም ፍትጊያው ይቀንሳል። አለቀ! ነው ሰላማዊ ሠልፍ የጠራናችሁ መስሏችሁ ነው?›› ብሎ ብቻውን ሲስቅ ጎልማሳው፣ ‹‹መንገድ በሞላበት አገር መጓጓዣ ማጣት ካሠለፈን በላይ ምን ሰላማዊ ሠልፍ ያሻናል?›› ብሎ ሲያበቃ ግንባር ቀደም ሠልፈኛ ለመሆን ቦታ ያዘ። ከአሥር የማንበልጥ ሰዎች ተከትለነው ተጠጋጋን። ‹‹በተናጠል ዓይን አንገባ ብለናል። እስኪ ሰብሰብ በሉ ጓዶች?›› ይላል ከኋላዬ የቆመ ሠልፈኛ። የጎልማሳውን ናር ናር ማለት ያዩት ወይዘሮዋ ደግሞ፣ ‹‹አንተስ ብትሆን ከእነሱ ጋር ከመመላለስ መኖርን በተራ ካደረገው፣ ‘ሲስተም’ ጋር አትነጋገርም?›› ሲሉት ‹‹ሲስተም ቢኖርማ ቀድሞውን ይህ እንደሚመጣ ተንብዩ መፍትሔ የሚያበጅ ይጠፋ ነበር?›› አላቸው። ‹‹በል ተወው…›› ብለው ዝም ሲሉ ከእሳቸው ጀርባ ፀጉሯን የማሻሸት ሱስ የያዘት ዘንካታ፣ ‹‹ሂ ኢዝ ራይት…›› ብላ አስተያየት ሰጠች። መባዛት ሳያንሰን ያለአስተርጓሚ መግባባት ያልቻልንበት ጎዳና ገጽ አንድ መሆኑ ነው። አካሄዳችንን ያሳምረው ብለናል!

ወዲያው ከተፍ ያለች ጃጉዋር ሰበሰበችን። የሠልፉም መስመር ወደ ሐሳባዊነቱ ተመለሰ። ከቅ ሌላ ሠልፈኛ እየተጋጋ ሲቃረብ እያየን እኛ ተንቀሳቅሰን። ወያላው ዓይኑን ከዘንካታዋ ፀጉር ላይ መለስ ቀለስ እያደረገ፣ ‹‹ምናለበት ግን አንተ ሰውዬ በዚህ መኪና ተበድረህልኝ ፀጉር ቤት ብከፍትና ፀጉር ብሰነጥቅ?›› ይለዋል። ‹‹አቤት ሰው! እማማ እኛ እኮ ሰው ሲያልፍለት አንወድም፤›› ብሎ ደግሞ ወዲያው የሚመረኮዝባት መቀመጫ ላይ ወደተሰየሙት ወይዘሮ ዞረ። ‹‹እሱ እንኳን ሰው ሲያልፍበትም አንወድ፤›› አሉት ኑቁዋ ወይዘሮ። ‹‹ጉድ ፈላ! ሰው ሲያልፍበትም ሲያልፍለትም ካልወደድን ታዲያ ምንድነው የምንወድለት?›› ሲላቸው ‹‹እንጃ! እንኳን የኅብረተሰብ ሳይንስ ላውቅ ኑሮዬም አልገባኝ አደራህን ተወኝ፤›› ብለው ፊት ነሱት። ‹‹ዝም በሉት። እሱ እንደሚለው ሊብሬዬን አስይዤ ገንዘብ ብበደርለት ሠርቶ መለወጥ መቼ ያስባል?›› ሾፌሩ ተራውን ያናግራቸው ጀመር።

‹‹ታዲያ ምንድነው የሚያስበው?›› ለሾፌሩ ጆሮ የሰጡ ይመስላሉ። ‹‹ፀጉር መሰንጠቅ ሲል አይሰሙትም? ወደን አይደለም እኮ ቀርቃሪ የሆንነው፤›› ብሎ ሾፌሩ መኩራራት ሊጀምር ሲል፣ ‹‹ቀርቃሪነቱን እንኳ ለጊዜው ተወው። በመልክና በቁመት አንመሳሰል እንጂ ኪሳችን እኮ አንድ ነው፡፡ እንተዋወቃለን ልጄ፤›› ከንፈር መጠጡ ወይዘሮዋ። ‹‹እንዴት እማማ? ኪሳችን አንድ ቢሆን ኖሮ ዛሬ በአገራችን ከዘጠና ሚሊዮን በላይ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ መገፋፋት ነበረበት እኮ፤›› ሲላቸው የፊቱን ትቶ ወደኋላው እየዞረ፣ ‹‹አሁን ተመልሶልኛል። እኔ መጀመሪያም እንዲያ ያልኩት የሰፊው ሕዝብ ወገን መስለኸኝ ነው፤›› ብለው ዝም አሉ። ‹‹የጠባቡ ሕዝብ ወገን የሚባሉ ደግሞ መጡ?›› ሲላቸው ከጎናቸው የተቀመጠ ወጣት፣ ‹‹ያውስ ያሉ፣ የነበሩ፣ ወደፊትም የሚኖሩ ናቸዋ። ይኼን ሳታውቅ ነው መታወቂያ ያወጣኸው?›› ብለው በኃፍረት አሽኮረመሙት። ተሽኮርማሚው ባይበዛ ኖሮ በወይዘሮዋ አገላለጽ የጠባቡ ሕዝብ ወገን ከትውልድ ትውልድ ይቀጥል ነበር? ወይስ ዱላ የሚያቀብል
ሌባ እስኪገለጥ ነው የምንጠብቀው? ምን ይታወቃል የእኛ ነገር!

ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመችው ዘንካታ ቦርሳዋን ስትጎረጉር ሳንቲም ፍለጋ መስሎናል። መጨረሻ ወንበር ከተየሰሙት ጓደኛሞች አንደኛው አስግጎ በዓይኑ አብሯት ይበረብራል። ‹‹ኧረ ሰው ይታዘበኛል በል፤›› ይለዋል ወዳጁ። ‹‹እባክህ ፖሊስ አይታዘበኝ እንጂ ሰውማ ታዝቦ ታዝቦ ይረሳል፤›› ይመልሳል አባ ደፋር። ይኼን ጊዜ ቆንጅት ሽቶ አውጥታ ፀጉሯና አንገቷ ሥር ነሰነሰችው። መዓዛው ታክሲዋን አወደው። መሀል መቀመጫ አጠገቤ የተቀመጠው ባለሳምሶናይቱ ጎልማሳ በተርታ አስነጠሰው። ‹‹ይማርህ! ይማርህ! ሳይለንት ሙድ አድርገነው ነው እነጂ እኛንም ይማረን፤›› ልጅቷ ቦርሳ ላይ ዓይኑ ሲንከራተት የነበረው ወጣት ነው። ‹‹ያኑርህ እንዳልል እንዴት ብዬ!›› አለ ጎልማሳው እየሳቀ። ‹‹ለምን?›› አሉ ወይዘሮዋ ተጠማዘው።

‹‹እንኳን ለሽቶ ለቃሪያና ለቲማቲም እጅ ያጠረው ወገኔ ባልጠገበ አንጀቱ በጎን የፍሳሽ ቱቦ ሽታ በጎን እንዲህ ያለ ግሩም መዓዛ እየሰነፈጠው ሲያስነጥስ እየዋለ፣ ያኑርህስ ብለው እንጥሻው ካላባራለት ምን ዋጋ . . . ኸ  ኸ  . .  እንጥሼ!  . . . ምን ዋጋ አለው…›› ብሎ ወደኔ ዞረና ሶፍት  ጠየቀ። ‹‹አይዞን! ለቃሪያና ለቲማቲሙስ አላነስንም ነበር። ለመቀባባቱና ለመጊያጊያጡ አልተርፍ ብሎን እንጂ…›› ብላ ከቆንጂት አጠገብ የተሰየመች አስተዋይ ተናገረች። ‹‹ቢተርፈንስ? የክት የሚያስለብስ ሆነ እንዴ ጊዜው? እንኳን ተኳኩለን ፊታችን ታጥበን ወጥተንም ፈለጣውን አልቻልነውም። ቆይ ግን አገር በፈለጣ ነው እንዴ የምትገነባው?›› ሲል ከወዲያ ጥግ መጨረሻ ወንበር ላይ፣ ‹‹ታዲያ ያለማገር ቤት ይቆማል እንዴ?›› ብለው ወይዘሮዋ ያልገባቸው መስለው ተሳፋሪውን አስፈገጉት። ማን እንጨት ማን ባለምሳር እንደሆነ አልገባንም እንጂ ስለእንጨት ፈለጣ እንዳላወራን መቼም ገብቶናል። የዝንብ ጠንጋራ እንለያለን እንኳን ይህቺን ኧረ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ጎሮ ደርሰን የአሠላለፍ ለውጥ አድርገናል። ጋቢና ሁለት ጓደኛማቾች እንስቶች ተሳፍረዋል። ወይዘሮዋ ወርደው በምትካቸው ተጫዋች አዛውንት ተሳፍረዋል። ታክሲዋ ከቆመችበት ልትንቀሳቀስ ስትል አንድ ልጅ እግር እየሮጠ መጣ። ‹‹ጋሼ የሁለት መለኪያ ካቲካላ ሒሳብ አልከፈሉም ተብለዋል?›› አላቸው የወይዘሮዋን ቦታ የተኩትን አዛውንት። ‹‹ሂድ ዝም ብለህ። ለባለቤቱ ነገሬዋለሁ። ነገ እከፍላለሁ፤›› አሉት በማባበል ዓይነት። ‹‹ሁሌ ነገ እያሉ አከሰሩኝ እኮ? እኔ እኮ ነኝ የምጠየቀው፤›› ልጁ ተነጫነጨ። ‹‹ሂድ ብያለሁ። ነገ አልኩህ በቃ።›› አባታዊ ቁጣ ተቆጡ። ‹‹እኮ ነገ መቼ ነው?›› ልጁ ኪሳራ የበዛበት ይመስላል። ‹‹ዋ ኋላ! አንድ ቀን ልክፈልህ ነገ ልስጥህ? በል መልስልኝ እኮ?›› አዛውንቱ ማምለጫቸውን ሠሩ። ‹‹ኧረ ዝጋው በቃ!›› ሾፌሩ ትዕግሥት አጣ። ልጁ እየተነጫነጨ ወደኋላ ቀረ።

አዛውንቱ የምንተ ዕፍረታቸውን፣ ‹‹አሁን እስኪ ከፍለህ አጠጣኝ አላልኩት። ነገ ስለው ነገ ብለዋል እንደ ማለት ከራሱ አውጥቶ እየከፈለ ዕዳ ልግባ?›› አጠገባቸው ወደ ተቀመጠው ወጣት ዞረው ፍረደኝ አሉት። ‹‹እርስዎስ በዚህ ዕድሜዎ ሲሆን ባይጠጡ፣ ከጠጡም ቢከፍሉ ምን አለበት?›› አላቸው። ‹‹የሚከፍለን ሳይኖር ከየት አምጥተን ነው የምንከፍለው? ከመንግሥት እስከ ግለሰብ ሥራ አሠርቶ በሰዓቱ የላብህን የሚከፍልህ አለ እንዴ? በዱቤ ማሠራት ከተጀመረ ደግሞ እኛም በዱቤ እየበላን በዱቤ እየጠጣን በዱቤ መኖር ነው። ምን አባቱ! የኖርነውን ያህል አንኖር?›› እያሉ ብቻቸውን ሲያወሩ ጎልማሳው ወደኔ ጠጋ ብሎ ወያላውን እየጠቆመኝ፣ ‹‹እኛም ነገ እንክፈል እንዴ?›› ብሎኝ ከት ብሎ ሳቀ። ‘እነሆ ዕዳ የማይፈራ ትውልድ ተነሳ’ የተባለው ዕውነት ይሆን እንዴ?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ደህና ይዞ ቆይቶ በመለያያችን ሾፌራችን ያክለፈልፈናል። ‹‹ምነው ረጋ በል እንጂ!›› አዛውንቱ ይጮኸሉ። ‹‹መውረጃችን ሲደርስ ነፍሳችንን ሰቀልካት እኮ?›› ሲሉት ደግመው ሾፌሩ በግንባር መስታወቱ አጮልቆ እየተመለከተ፣ ‹‹አንዳንዴማ ማደፍረስ ምን ይለናል? ካልተሰበሩ እኮ የት ልጠገን የለም። ካልደፈረሰም አይጠራም፤›› አላቸው በኩራት። ‹‹እና በእኛ ነፍስ ነው አደፍርሰህ የምታጠራው? ብቻህን አትሰበርም?›› አሉት አዛውንቱ የምር ተበሳጭተው። ‹‹ለየብቻ አልታመምን። ሸክሙ የጋራ፤›› ይላል ወጣቱ በጎን። ‹‹ወግድ! ቅኔ ዘርፋችሁ ሙታችኋል በነፍስ እየቀለዳችሁ፤›› ሲሉ አዛውንቱ መጨረሻ ወንበር ከተየሰሙት አንዱ፣ ‹‹በነፍስ ተይዘን በዱቤ መኖር ከጀመርን ወዲያ? ከዚህ በላይ ምን ይምጣ?›› አላቸው። ‹‹ኧረ ተወኝ!›› ብለው እጃቸውን አወናጭፈው ዝም ሲሉ ጋቢና የተቀመጡት ሴቶች ተጋብዘው ስለታደሙበት የልደት በዓል በአድናቆት ሲወያዩ ሰማን።

‹‹አንቺ አዲስ ሞዴል ‘ሃዩንዳይ’ እኮ ነው ቁጭ ያደረገላት። የቤቱ ማማር። ‘ኦ ማይ ጋድ!’ በቃ ገነት? ምን ትፈልጊያለሽ እሷን ብትሆኝ ከዚያ ሌላ?›› ሲባባሉ፣ ‹‹እግዚኦ የአንዱ ልደት ለሌላው ሞት። የአንዱ ለቅሶ ለሌላው ሐሴት። ዓለም ግን አትገርምም?›› እያለ አላስቀምጠኝ አለ ጎልማሳው። ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመችው ቀዘባ ሰምታው ኖሮ፣ ‹‹እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም። የሁሉም ነገር ቁልፉ ይዞ መገኘቱ ላይ ነው። ቢኖርህ ዛሬ ያልከውን አትልም ነበር፤›› አለችው ኮስተር ብላ። አዛውንቱ ቀበል አድርገው፣ ‹‹አይ ልጄ አያያዙን ካላወቁበት ገንዘብ ወረተኛ ነው። ይመጣል ይሄዳል። ይኼን አጠባበቅ ካልቻልሽበት (ኪሳቸውን እየተመተሙ) ኖሮሽም ኑሮ በዱቤ ነው፤›› ብለው ዘለው ወረዱ። ፀጉር ስንሰነጥቅ ጉዞው ተገባዶ ነበር ለካ? መልካም ሰንበት!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት