Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትና የካርድ አገልግሎት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአንድ ካርድ በሁሉም ባንኮች የኤቲኤም አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል የተባለው የኢት ስዊች አክሲዮን ማኅበር ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችለውን የሙከራ ሥራዎች መጀመሩ ተገለጸ፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ያሉት 18ቱም የንግድ ባንኮችና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለአክሲዮን ሆነው ያቋቋሙት ኢት ስዊች ከተያዘለት የጊዜ ገደብ የዘገየ ቢሆንም፣ የኤቲኤም አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ባንኮችን በኔትዎርክ በማስተሳሰር የሙከራ ሥራዎችን እያደረገ ነው፡፡

የአንድ ባንክ ደንበኛ በሁሉም ባንኮች ኤቲኤሞች ላይ መጠቀም የሚያስችለው ይህ አገልግሎት፣ የሙከራ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ ከጥቂት ወራት በኋላ ወደ መደበኛ ሥራ ይሸጋገራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢት ስዊች ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ በቀለ ገልጸዋል፡፡

ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትን አንድ ዕርምጃ ያራምዳል የተባለው ይህ አገልግሎት፣ ባንኮች ኤቲኤም ማሽን በመግዛት ብቻ የኢት ስዊች አክሲዮን ማኅበርን ስዊች በመጠቀም የካርድ ባንኪንግ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችላቸው ጭምር ነው ተብሏል፡፡ እስካሁን የኤቲኤም አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ባንኮች የራሳቸውን ስዊች በመግዛት ሲጠቀሙ የቆዩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ኢት ስዊች ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ግን በተለይ እስካሁን የኤቲኤም አገልግሎት ያልጀመሩ ባንኮች ስዊች መግዛት ሳያስፈልጋቸው በቀጥታ በኢት ስዊች ሶሉዊሽንን ስዊች ስርቨር መጠቀም የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡

አንድ ባንክ የኤቲኤም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልገው ስዊች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የካርድ ባንኪንግ አገልግሎትን በቀላሉ ሊያስፋፉ ይችላሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በዚሁ ምክንያት አንዳንድ ባንኮች ኤቲኤም ማሽኖችን ገዝተው በኢት ስዊች ለመጠቀም የኢት ስዊችን ሥራ መጀመር እየተጠባበቁ ነበር፡፡

የኢት ስዊችን ሥራ መጀመር ይጠባበቁ ከነበሩ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ የ50 ኤቲኤሞችን ተከላ እያጠናቀቀ ነው፡፡ ባንኩ በ50 ኤቲኤሞች ወደ ሥራ የሚገባ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከኢት ስዊች ጋር በማገናኘት የሙከራ ሥራ እያካሄደ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሌሎች እንደ ቡና፣ ዓባይና አንበሳ ያሉ ባንኮችም የኤቲኤም አገልግሎት ለመጀመር ተዘጋጅተዋል፡፡  

ከዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ጋር ተያይዞ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ባንኮች የኤቲኤም አገልግሎታቸውን ለማስፋት እየተዘጋጁና፣ እስካሁን የኤቲኤም አገልግሎት ያልጀመሩትም ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችላቸውን መሠረተ ልማት እያሟሉ መሆኑ ታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኤቲኤም አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ባንኮች በመላ አገሪቱ ከ2,400 በላይ የኤቲኤም ማሽኖችን ተክለዋል፡፡ ከየባንኮቹ ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ አሁን ባሉት ኤቲኤሞች የካርድ ባንኪንግ አገልግሎት እያገኙ ያሉ ደንበኞች ከሦስት ሚሊዮን በላይ ይሆናሉ፡፡

አገልግሎት ላይ ካሉት የኤቲኤም ማሽኖች ውስጥ ከ1,100 በላይ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተከላቸው ሲሆን፣ ቀሪዎቹ የግል ባንኮች ናቸው፡፡

የካርድ ባንኪንግ አገልግሎት በመጀመር ቀዳሚ ከሆኑት የግል ባንኮች መካከል አንዱ ዳሸን ባንክ ደግሞ ከ110 በላይ የኤቲኤም ማሽኖች ያሉት ሲሆን፣ ከ400 ሺሕ በላይ የካርድ ባንኪንግ ተጠቃሚ ደንበኞች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ፕሪምየም ስዊች ሶሉዊሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሚል ስያሜ የተቋቋመውና በጥምረት የካርድ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ስድስት የግል ባንካች ደግሞ በአጠቃላይ 480 በላይ ኤቲኤሞችን ተክለው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

በስድስቱም ተጣማሪ ባንኮች የኤቲኤም አገልግሎት የሚሰጠው የፕሪሚየም ስዊች ደንበኞች በጠቅላላው ከአንድ ሚሊዮን በላይ መድረሳቸው ታውቋል፡፡

ፕሪሚየም ስዊች ሶሉዊሽን በመጀመሪያ አዋሽ፣ ኅብረትና ንብ ባንክ ያቋቋሙት ቢሆንም ከእነርሱ በኋላ ብርሃን፣ አዲስ ኢንተርናሽናል የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንኮች ተቀላቅለውታል፡፡

እነዚህ የካርድ አገልግሎትን በጋራ ለመስጠት የተጣመሩት ባንኮች ካሉዋቸው ኤቲኤሞች ስድስቱም ባንኮች እያንዳንዳቸው ከ50 እስከ 100 ኤቲኤም ማሽን ግዥ በመፈጸም ላይ ናቸው፡፡ ይህም ተጨማሪ ባንኮቹ በጋራ የሚጠቀሙባቸውን ኤቲኤሞች ከአንድ ሺሕ በላይ ያደርሰዋል፡፡

በተናጠል በየራሳቸው ስዊች የካርድ ባንክ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት አቢሲኒያና ወጋገን ባንኮች፣ በጥቅሉ 300 በላይ ኤቲኤሞች አሏቸው፡፡ የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አስማረ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከዚህ በኋላ የኤሌክትሮኒክስ ባንኪንግ ትኩረት የሚሰጠውና እየተስፋፋ የሚሄድ ይሆናል፡፡ አቢሲኒያ ባንክም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡ የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙም፣ ባንካቸው ይህንን አገልግሎት እንደሚያሰፋና ተጨማሪ አገልግሎት እንደሚጀምር ይገልጻሉ፡፡ ቅርንጫፍ ከመክፈት ይልቅ እንደ የኤሌክትሮኒክስ ባንኪንግ ያሉ አገልግሎቶች ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉም የጠቀሱት አቶ ሙሉጌታ፣ በተለይ በከተማ አካባቢ የካርድ ባንኪንግ አገልግሎት እየተለመደና እየተፈለገ መምጣቱ በዘርፉ ብዙ መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡

      አቢሲኒያ ባንክ በአሁኑ ወቅት 85 የኤቲኤም ማሽኖችን አገልግሎት ላይ ያዋለ ሲሆን፣ በቀጣዩ አምስት ዓመት የኤቲኤም ማሽኖቹን ቁጥር 500 ለማድረስ ማቀዱንም አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሌሎቹም የግል ባንኮች በተመሳሳይ መንገድ የኤቲኤም ማሽኖቻቸውን ቁጥር ለማሳደግ ግዥ በመፈጸም ላይ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹም ባንኮች አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስችላቸውን መሠረተ ልማት እየገነቡ ነው፡፡

ይህንን አሠራር ለማሳደግ ባንኮች የየራሳቸው ዕቅድ የያዙ መሆኑን ያነጋገርናቸው የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ የኤቲኤም ማሽኖችን ከመጨመር ጐን ለጐን አገልግሎቱንም ለማስፋት የተጀመሩ ዝግጅቶች እንዳሉም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ኤቲኤም ገንዘብ ማውጫ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም የኤቲኤም አገልግሎት ገንዘብ ማውጣት ብቻ ባለመሆኑ ተጨማሪ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ይደረጋል ተብሏል፡፡  

እንዲህ ዓይነቱን አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅት እያደረጉ ካሉ ባንኮች መካከል አንዱ ዳሸን ባንክ ነው፡፡ እንደ ዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት ገለጻ፣ በካርድ አገልግሎት ባንካቸው ያለውን ጥንካሬ የበለጠ ለማሳደግ በኤቲኤም ገንዘብ የመላክ አገልግሎት በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል፡፡

ሌሎች ባንኮችም ተመሳሳይ ውጥን እንዳላቸው እየተነገረ ነው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ገንዘቦች መመንዘሪያ ኤቲኤም ማሽኖችን መትከሉም ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለአገልግሎት እየተዘጋጁ ካሉ ባንኮች መካከል ግን አንዳንዶቹ የኤቲኤም አገልግሎት ለመጀመር የዘገዩት ሁሉም ባንኮች በጋራ ባቋቋሙት ኢት ስዊች ኩባንያ በኩል አገልግሎቱን ለመጀመር በማሰብ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው፣ የኢት ስዊች አገልግሎት ቢዘገይም በቅርቡ ሥራ ይጀምራል፡፡ ይህም አገልግሎት ሲጀመር የካርድ አገልግሎትን በከፍተኛ ደረዳ ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኢት ስዊች ሥራ መጀመር በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ባንኮች በሙሉ በአንድ ካርድ እንዲጠቀሙ ማስቻሉ፣ እየተወዳደሩም መተባበር እንደሚቻል ያሳያል ተብሏል፡፡ የአንድ ባንክ ደንበኛ በየትኛውም ባንክ ኤቲኤም ለመጠቀም የሚያስችለውን ዕድል ስለሚፈጥር በከፍተኛ መጠን ደንበኞችን እንደሚያድግ ተገልጿል፡፡ ኢት ስዊች የሁሉንም ባንኮች ኤቲኤሞች በማስተሳሰር ከሚሰጠው ሌላ፣ ተጨማሪ የካርድ አገልግሎቶችን ተግባራዊ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች