[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]
- ምን ፈለግሽ?
- ከሰዓት አልኖርም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን ሲባል?
- ጥምቀት ነዋ፡፡
- ጥምቀት ነገ አይደል እንዴ?
- ዛሬ ከተራ ነዋ፡፡
- ከተራ ምንድን ነው?
- ታቦት የሚወጣበት ቀን ነዋ፡፡
- ስለዚህ ታቦት ሲወጣ፣ አንቺ ከሥራ መውጣት አማረሽ?
- ክቡር ሚኒስትር ምን ነካዎት?
- ንገሪኝ አንቺ የመሥሪያ ቤታችን ታቦት ነሽ ወይ?
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ታቦት ይወጣል ብለሽ አንቺም ከሥራ የምትወጪው?
- ታቦቱን እሸኘዋለኋ፡፡
- ሞክሪውና እኔም ከሥራ እሸኝሻለሁ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በዚህማ ቀልድ የለም፡፡
- እንዴት?
- እርስዎ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ እንደማይቀልዱ እኔም በሃይማኖቴ አልቀልድማ፡፡
- እና ሥራ ጥለሽ ነው የምትሄጂው?
- እርስዎ ሥራ ጥለው ስብሰባ ይሄዳሉ አይደል እንዴ?
- ስብሰባ ሥራ አይደለም ያለሽ ማን ነው?
- ሕዝቡ ነዋ፡፡
- እንዴት?
- ተሰብስበው መፍትሔ ካላመጡ፣ ስብሰባ በራሱ ማድረጉ መፍትሔ አያመጣማ፡፡
- ለማንኛውም ያልተጠየቅሽውን አታውሪ፡፡
[አንድ የባንክ ባለሙያ ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለላቸው]
- ምንድን እየተሠራ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሥራ ነዋ፡፡
- እኮ ምን ዓይነት ሥራ?
- ምን እያወራህ ነው?
- ለምን አንደኛውኑ አትዘጉንም?
- ማንን ነው የምንዘጋው?
- የግል ባንኮችን ነዋ፡፡
- ኢኮኖሚውን ያለ ግል ዘርፉ ማካሄድ እኮ በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ ነው፡፡
- ከዚህ በላይ እንዴት በአንድ እጅ ታጨበጭቡ ታዲያ?
- አልገባኝም?
- ይኸው በንግድ ባንክ ብቻ ማጨብጨብ ከጀመራችሁ እኮ ሰነባበታችሁ፡፡
- ቅኔ እያወራህ ነው?
- ምን ቅኔ ነው እውነታ ነው እንጂ፡፡
- የምን እውነታ?
- ሰሞኑን ከግል ባንኮች የወጣው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ አልሰሙም?
- ኧረ አልሰማሁም፡፡
- ወደ 4.5 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በሁለት ሳምንታት ከግል ባንኮች ወጥቷል፡፡
- ሰው ብሩን በካዝና ማስቀመጥ ጀመረ እንዴ?
- የለም ንግድ ባንክ የሚሉት ካዝና ውስጥ ከቶት ነው እንጂ፡፡
- ምነው ዛሬ አሽሙር አበዛህ?
- ወድጄ አይደለም፣ አካሄዳችሁ ስላልገባኝ ነው፡፡
- የምን አካሄድ?
- ክቡር ሚኒስትር ይህ ገንዘብ በአንዴ ከግል ባንኮች ለምን እንደወጣ ያውቃሉ?
- አላውቅም፡፡
- ንግድ ባንክ ኤልሲ ለሚፈልግ ደንበኛ ሁሉ እሰጣለሁ በማለቱ ነዋ፡፡
- እኔ እኮ የማይገባኝ አንድ ነገር ነው፡፡
- ምንድን ነው የማይገባዎት?
- በየሚዲያው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ እየተባለ ሲወራ ታግሰን ዝም አልን፡፡
- እውነት ነዋ፡፡
- አሁን ደግሞ ኤልሲ ለከፈተ እንሰጣለን ሲባል ደግሞ አገር ተተራመሰ ትላላችሁ፡፡
- በእርግጥ ተተራምሷላ፡፡
- ምን ተሻለ ታዲያ?
- በተጠና አካሄድ ውሳኔዎችን ማከናወን ነዋ፡፡
- እንዴት ማለት?
- ክቡር ሚኒስትር የፋይናንስ ዘርፉ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ ይጠይቃል፡፡
- እሱማ ልክ ነው፡፡
- እናንተ ግን እሱን እያደረጋችሁ አይደለም፡፡
- እንዴት አይደለም?
- የውድድሩ ሜዳ ፍትሐዊ አይደለም፡፡
- ለምንድን ነው ፍትሐዊ ያልሆነው?
- ሁሉም ነገር በንግድ ባንክ በኩል ነዋ የሚፈጸመው፡፡
- ሁሉም ነገር ስትል?
- ዶላር ቢመጣ የሚሰጠው ለእሱ ነው፡፡
- እ…
- ኮንዶሚኒየም ቤት ሲሠራ በእሱ በኩል ነው፡፡
- ሌላስ?
- እኛ ቦንድ እንገዛለን፣ እሱ አይገዛም፡፡
- እ…
- ብቻውን ጡንቻውን እያፈረጠማችሁት ነው፡፡
- እሱ ልጃችን ነዋ፡፡
- እኛ የእንጀራ ልጆች ነን?
[አንድ ባለሀብት ክቡር ሚኒስትሩ ጋ ደወለ]
- እንኳን አደረሰዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምኑ?
- ለጥምቀት በዓል ነዋ፡፡
- እኔ እኮ እንዲህ ዓይነት በዓል ብዙም አላከብርም፡፡
- ለምን እንደማያከብሩት ገባኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምንድን ነው የማላከብረው?
- ለእርስዎ ሁሌ ጥምቀት ነዋ፡፡
- እንዴት ማለት?
- የጥምቀት በዓል መገለጫው እኮ መወራወሩ ነው፡፡
- ድንጋይ ውርወራ አለበት እንዴ?
- የለም የለም፣ ሎሚ መወራወሩን ነው የምልዎት፡፡
- ሎሚ ለምንድን ነው የሚወረወረው?
- ወንዱ ሴቷን ወድጄሻለሁ ለማለት ሎሚ ይወረውራል፡፡
- ሴቷስ ምን ትወረውራለች?
- ሴቷማ ከወደደችው ልቧን ትወረውራለች፡፡
- እና ይኼ ባህል አሁንም አለ?
- ባህሉ እንኳን አለ የሚወረወረው ነገር ግን ጨምሯል፡፡
- ሎሚ መወርወር ቀርቶ ብርቱኳን ተጀመረ?
- ክቡር ሚኒስትር ምን ነካዎት?
- እንዴት?
- በዕድገቱ ሳቢያ ሎሚ ወደ ቪትስ ተቀይሯል፡፡
- እሱስ ልክ ብለሃል፤ አገሪቷ እኮ ተመንድጋለች፡፡
- ለማንኛውም እንኳን አደረስዎት፡፡
- በነገራችን ላይ አንድ ነገር ከንክኖኛል፡፡
- ምን ከነከንዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ለእርስዎ ሁሌ ጥምቀት ነው ያልከኝ ነዋ፡፡
- አይ እርስዎ ሁሌም ይወራወራሉ ብዬ ነዋ፡፡
- ከማን ጋር ነው የምወራወረው?
- ከባለሀብቶች ጋር ነዋ፡፡
- ምንድን ነው የምወራወረው?
- እነሱ ቪላ ሲወረውሩልዎት፡፡
- እ…
- እርስዎ ደግሞ መሬት ይወረውራሉ፡፡
- ኧረ ሰው እንዳይሰማህ?
- ችግሩ ሰው መስማቱ አይደለም፡፡
- ታዲያ ምንድን ነው ችግሩ?
- የሚሰማው ሰው ራሱ ይወራወራል ወይስ አይወራወርም? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡
- ለማንኛውም ምን ፈልገህ ነው?
- ልጠይቅዎት ነዋ፡፡
- ምንድን ነው የምትጠይቀኝ?
- ምን ልወርውርልዎት?
- ቪትስ እንደማልልህ ታውቃለህ?
- እሷንማ ብወረውርልዎት መቼ ይቀልቧታል?
- እንዴት?
- ሽል ነዋ የሚሉኝ፡፡
- ለነገሩስ እውነትህን ነው፡፡
- ስለዚህ ምን ልወርውር?
- ቪላ ወይ ቪ-8 ነዋ፡፡
- እርስዎስ ምን ይወረውሩልኛል?
- ምን ልወርውርልህ?
- መሬት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሹፌራቸው ጋር እየሄዱ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር ያው ነገ አልኖርም፡፡
- ለምን ሲባል?
- ጥምቀት ነዋ፡፡
- ቢሆንስ ታዲያ?
- ክቡር ሚኒስትር ትልቅ በዓል እኮ ነው፡፡
- ትልቅ በዓል?
- አዎ፣ ይኸው ዩኔስኮ ራሱ ሊመዘግበው እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
- አሁን አንድ ኒዮሊብራል ተቋም መመዝገቡ ነው ትልቅ የሚያስብለው?
- ክቡር ሚኒስትር ፖለቲካ ብዙም አይገባኝም፡፡
- በዓሉ መመዝገብ ካለበት ለምን ልማታዊ በሆኑ የአገራችን ተቋማት አይመዘገብም?
- አልገባኝም፣ የት መመዝገብ ይችላል?
- ለምሳሌ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት፡፡
- እ…
- እንዲያውም በአገራችን ባሉ ልማታዊ ተቋማት መመዝገቡ የውጭ ምንዛሪ ያድንልናል፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ለኒዮሊብራሎቹ ተቋማት ለምዝገባ የሚከፈለው ገንዘብ በዶላር ነዋ፡፡
- ኧረ ዩኔስኮ በገንዘብ አይመስለኝም የሚመዘግበው፡፡
- እሱን እንኳን ተወው፡፡
- እንዴት?
- የአገራችን ኩባንያዎች የጥራት ሠርተፊኬት እያሉ የሚያግበሰብሱትን እየከፈሉ አይደል እንዴ የሚያመጡት?
- እሱን አላውቅም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስማ እንዲያውም ይኼ ኒዮሊብራል ተቋም መመዝገብ ያለበት ትልቅ ሕዝባዊ በዓል አለን፡፡
- የምን ሕዝባዊ በዓል?
- ብሔር ብሔረሰቦች!
[ክቡር ሚኒስትሩ ሊከፍቱት ላሰቡት የሞባይል ቤት ዲስፕሌይ የሠራላቸው ባለሙያ ደወለ]
- በሰጡኝ ትዕዛዝ መሠረት ሥራዬን ጨርሻለሁ፡፡
- ዋጋ ቀንስልኛ?
- ነጋዴ ዋጋ ይጨምራል እንጂ መቼ ይቀንሳል?
- ለምን አይቀንስም?
- ከእናንተ ነዋ የምንማረው?
- እኛ ምን አስተማርናችሁ?
- ይኸው የነዳጅ ዋጋ ቀንሶ እናንተ መቼ ትቀንሳላችሁ?
- እ…
- እንዲያውም መንግሥት ነዳጅ ላይ እንትን ሆኗል ነው የሚባለው፡፡
- ምን?
- ኪራይ ሰብሳቢ!
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
- ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ከተማ ውስጥ ጥሩ የሚባለው ሞል ላይ አንድ ሱቅ ፈልግልኝ፡፡
- የምን ሱቅ?
- የሞባይል መሸጫ የሚሆን፡፡
- ለማን ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ለእኔ ነዋ፡፡
- እ…
- አገሪቷ ስታድግ የበይ ተመልካች መሆን የለብንም፡፡
- እና?
- በቃ አሪፍ ሱቅ መክፈት አለብኝ፡፡
- ኪራዩን ማን ይከፍለዋል፡፡
- መሥሪያ ቤቱ ነዋ፡፡
- እንደዛ ከሆነማ ስምዎት ይቀየራል፡፡
- እንዴት?
- ክቡር ሚኒስትር ቀርቶ …
- ማን ልባል?
- ክቡር ነጋዴ!