Tuesday, March 28, 2023

ደቡብ ሱዳናውያን ከአፍሪካ ኅብረት ምን ይጠብቃሉ?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የደቡብ ሱዳን አማፂ ቡድኖች ለበርካታ አሠርት ዓመታት ባደረጉት የነፃነት ትግል፣ አገራቸውን አዲሲቷ አፍሪካዊት አገር ሆና እንድትመዘገብ አድርገው ነበር፡፡ ሆኖም ከሰሜን ሱዳን ያገኙትን የግዛት ነፃነት ከአንድ ዓመት በላይ አላጣጣሙትም፡፡ ከሰሜኑ የሱዳን ክፍል በይደር የቆየው የድንበርና የሀብት ክፍፍል ሌላ ጦርነት ቢቀሰቅስም፣ ከአንድ ዓመት በኋላ በውስጣቸው የተከሰተውን የእርስ በርስ ግጭት ያህል ቀውስ ያስከተለ አልነበረም፡፡

በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ምክትላቸው በነበሩት ዶ/ር ሪክ ማቻር መካከል የተፈጠረው ልዩነት፣ ፓርቲው (የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ድርጅት) እና የሚመራው መንግሥት ለሁለት እንዲሰነጠቅ ካደረገ በኋላ የአገሪቱ ሚኒስትሮችና ወታደራዊ ኃይሉ ለሁለት ተከፍለው አሳሪና ታሳሪ ሆነዋል፡፡ በአማፂነት ከተሠለፉት ዶ/ር ማቻር ጋር አብረዋል ተብለው የተጠረጠሩ የተወሰኑ ባለሥልጣናት ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ የአገሪቷ የፀጥታ ኃይልም ወደ እርስ በርስ ውጊያ መግባቱ አይዘነጋም፡፡

በቅርብ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የእርስ በርስ ጦርነቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት የሆነ ሲሆን፣ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ወደ አጎራባች አገሮች ተሰዷል፡፡ ኢትዮጵያ ከ700 ሺሕ በላይ የሚሆኑትን አስጠልላለች፡፡

የእርስ በርስ ግጭቱ ቀስ በቀስ የብሔር መልክ እየያዘ የመጣ ሲሆን፣ በዲንካና በንዌር ብሔሮች መካከል ግጭቱ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የዲንካ ብሔረሰብ ተወላጅ ሲሆኑ፣ በአማፂነት የተሠለፉት የቀድሞ ምክትላቸው ዶ/ር ማቻር ከኑዌር ናቸው፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) አስተባባሪነት አምባሳደር ሥዩም መስፍን በልዩ ልዑክነት የመሩት የሰላም ድርድር ላለፉት ሦስት ዓመታት ሁኔታው ረገብ እንዲል አስተዋጽኦ ያደረገ ቢሆንም፣ መሪዎቹ ለሚፈጽሙዋቸው ስምምነቶች ተገዢ ባለመሆናቸው ተግባራዊነቱ ጥያቄ ውስጥ እየገባ ቆይቷል፡፡ አምባሳደር ሥዩም ባለፈው ዓመት በተመድ የአፍሪካ ኮሚሽን በተካሄደው የጋራ ሁለገብ ኮንፈረንስ ላይ እንዳሉት፣ የደቡብ ሱዳን ሰላም የደፈረሰው በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች መሪዎች ነበር፡፡

በአገሪቱ የተለየ ፍላጎት ያላቸው እንደ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ኖርዌይ (ትሮይካ በመባል ይታወቃሉ) እና ቻይና ከድርድሩ ጀርባ የነበሩ ቢሆንም፣ የሰላም ድርድሩ የሚፈለገውን ያህል ሰላም በተፈለገው ጊዜ ለደቡብ ሱዳናውያን ያስገኘ አልነበረም፡፡ በሶማሊያ እንዳደረገችው ሁሉ በደቡብ ሱዳን መረጋጋት ለመፍጠር ባደረገችው ጥረት ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ምሥጋና ሲቸራት የነበረችው ኢትዮጵያም፣ የተጠበቀውን ውጤት አላመጣችም ተብላ እስከመተቸት ደርሳለች፡፡

ከአፍሪካ ኅብረትና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጀት ተጨማሪ ሸምጋዮች ተጨምረውበት፣ የተቀናጀ የሰላም ማስፈን ሒደቱ መልኩን ቀይሮ ላለፈው አንድ ዓመት ተካሂዷል፡፡ እጅግ አጨቃጫቂ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የሥልጣን ክፍፍል፣ የመንግሥት መዋቅርና የወታደሩ ተዋፅኦን በተመለከተ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በጦርነቱ የተፈጸሙ ጥፋቶችንም ለማጣራት ገለልተኛ አጣሪ ቡድን እንዲቋቋም ተስማምተው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች አማፂያንንም የሚያሳትፍ የጋራ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

ከአፍሪካ ኅብረት ምን ይጠበቃል?

በሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ለተከሰተው ቀውስ የመጨረሻ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ የተጠበቀው የጋራ የሽግግር መንግሥት በይፋ የሚቋቋምበት ጊዜ ጥር 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲሆን፣ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና የደቡብ ሱዳን ሕዝብ በጉጉት የሚጠብቁት ዕለት ሆኗል፡፡ ብዙዎች ለአገሪቱ የሽግግር መንግሥት መመሥረት፣ የጋራ አጣሪና መርማሪ ኮሚሽን በሙሉ አቅም ወደ ሥራ መግባት ለደቡብ ሱዳን መረጋጋት የመጨረሻ መፍትሔ አድርገው የሚመለከቱት ሲሆን፣ አንዳንድ የአፍሪካ የሲቪክ ማኅበረሰብ አባላት ግን የእነዚህ ሁለት ተቋማት ሥራ ብቻውን የአገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት በቂ እንዳልሆነ ያምናሉ፡፡

እንዲህ ዓይነት አቋም ካላቸው የሲቪክ ማኅበረሰብ አመራሮች መካከል፣ ተመሳሳይ የእርስ በርስ ግጭት ከገጠማቸው የአፍሪካ አገሮች ልምድ ያካፈሉ የኡጋንዳ፣ የኬንያ፣ የደቡብ አፍሪካና የዚምባብዌ ተወካዮች ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

ሰኞ ጥር 9 ቀን 2008 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ በክራይስስ አክሽን አስተባባሪነት በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በኦክስፋም ኢንተርናል አዘጋጅነት ለሦስት ቀናት በቦሌ አምባሳደር ሆቴል በጉዳዩ ላይ ምክክር መደረጉ ተገልጿል፡፡ አንዳንድ የመፍትሔ ሐሳቦች በአፍሪካ ኅብረት ተሰብሳቢዎች ይቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ግምት ውስጥ እንዲያስገባቸው ከቀረቡ የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል፣ ኅብረቱ የሚመራው የጋራ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም የሚለው ይገኝበታል፡፡

የዓለም አቀፍ የዳኞች ኮሚሽን የአፍሪካ ዳይሬክተር አርኖልድ ቱንጋ የመሩት ይኼው በዝግ የተካሄደው የውይይት መድረክ ታዋቂ የሕግ ባለሙያዎች ሐሳባቸውን ያቀረቡበት ነበር፡፡ በውይይቱ መጠናቀቅ ላይ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከአፍሪካ ኅብረት መሪዎችና ከፖሊሲ አውጪዎች ይጠበቃል ያሉትን የመፍትሔ ሐሳብ አብራርተዋል፡፡

አርኖልድ ቱንጋ በተደረገው የውይይት መድረክ የቀረቡ የመፍትሔ ሐሳቦችና ድምዳሜዎች ለጋዜጠኞች አቅርበው፣ በደቡብ ሱዳን የጋራ የሽግግር መንግሥት መመሥረቱ ወሳኝ ጉዳይ ቢሆንም በድኅረ ግጭት የፍትሕ ሽግግር ሥራ ካልተሠራ ዘላቂ መረጋጋትና አስተማማኝ ሰላም እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም የአፍሪካ ኅብረት በበላይነት የሚመራው የጋራ ፍርድ ቤት (Hibrid Court) እንዲቋቋምና ለተፈጸሙ በደሎች ሕጋዊ እልባት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ ይህ የሕግ ተቋም በሽግግር ላይ ያለችው ደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖችና በአፍሪካ ኅብረት አመራሮች መካከል አገናኝ ድልድይ እንዲሆን፣ እንዲሁም በአፍሪካ (ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ) አገሮች የተገኘውን ልምድ ቀምሮ ተጠያቂነቱ ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ ብቻ የሆነና ለሕዝቡ ብቻ የቆመ እንዲሆን በማጠቃለያ ሐሳባቸው ተናግረዋል፡፡

ለዚህም በደቡብ አፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ፋውንዴሽን ዳይሬክተር ያስሚን ሱካ፣ ‹‹ዘላቂ ፍትሕና አስተማማኝ ሰላም›› በሚል ርዕስ የቀረበው ጥናት፣ የደቡብ ሱዳን የሕግ ማኅበረሰብ ዳይሬክተር በሆኑት ዴቪድ ዳንግ የቀረበው ጥናት፣ እንዲሁም የኬንያ የእውነት አፈላላጊና የብሔራዊ ዕርቅ ኮሚሽን “Justice and Reconciliation, Comparative Experiences of Kenya and Sierra Leone” በሚል ርዕስ የቀረበውን ጥናታዊ ምርምር ኅብረቱ ግምት ውስጥ እንዲያስገባ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

ኬንያዊቷ ኩሪ ሙሩንጉ ጉዳዩን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ በደቡብ ሱዳን ከሚመሠረተው የጋራ የሽግግር መንግሥት ጎን ለጎን የፍትሕ ሥራ ካልተሠራ የሚፈልገው መረጋጋት አይገኝም ብለዋል፡፡ እሳቸው የኬንያ የብሔራዊ ዕርቅ ኮሚሽን ምክትል ኃላፊ የነበሩ ሲሆን፣ ከኬንያ ቀውስ ያገኙት ልምድና ተሞክሮ መሠረት አድርገው ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ በደቡብ ሱዳን የሌሎች የአጎራባች አገሮች ልምድ በመቀመር የፍትሕና የዳኝነት ሥራ እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡ ለዚህም የአፍሪካ ኅብረት ጉዳዩን በበላይነት በመምራት ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ቀደም ሲል ለፈረሙት ሁለገብ ስምምነት ተገዢ ሆነው፣ የጋራ የሽግግር መንግሥት ያቋቁማሉ የሚል ተስፋ በብዙዎች የሚጠበቅ ሲሆን፣ በቅርቡ ስብሰባውን በአዲስ አበባ የሚያካሂደው የአፍሪካ ኅብረት የደቡብ ሱዳንን ጉዳይ ከዋናዎቹ አጀንዳዎች መካከል ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የአፍሪካ ሲቪል ማኅበረሰቦች ጥምረት በየዓመቱ የኅብረቱ መሪዎች ትኩረት ሊሰጡዋቸው ይገባሉ የሚሉዋቸውን ጉዳዮች ተወያይተው የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ዘንድሮ የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ችላ እንዳይባልና ያለበቂ ጥንቃቄ የተጀመረው መልካም ሒደት የሚፈለገውን ውጤቱ ሳያመጣ እንዳይቀር የሚያሳስብ ይመስላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -