Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዩክሬን መኪኖችን ለመገጣጠም ሲገነባ የነበረው ፋብሪካ ሕገወጥ ተብሎ ፈረሰ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዩክሬን ሠራሽ አውቶሞቢሎችን በአገር ውስጥ ለመገጣጠም የተቋቋመው ኒማ ሞተርስ የመኪና መገጣጠምና መለዋወጫ ኩባንያ፣ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ውስጥ አወልያ ትምህርት ቤት አካባቢ እያስገነባው የነበረው ፋብሪካ ሕገወጥ ተብሎ በአስተዳደሩ ፈረሰ፡፡

ኩባንያው የኢንቨስትመንት ፈቃድ ይዞ የግል ይዞታው በነበረው 7,500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ግንባታ ሲያካሂድ እንደነበር ይገልጻል፡፡ ሆኖም የክፍለ ከተማው አስተዳደርም ሆነ ወረዳው ሕገወጥ ግንባታ በማለት እየተገነባ የነበረውን ፋብሪካ በግሬደር ያፈረሱት ሰኞ ጥቅምት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ ሪፖርተርን ጨምሮ የሌሎች መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ይካሄድ የነበረውን የማፍረስ ተግባር በቦታው በመገኘት ለመዘገብ ያደረጉት ጥረትና ጥያቄ፣ የማፍረስ ሒደቱን እንዲቆጣጠር በኮማንደር ወጋየሁ ሶርሳ በተመደበው የፀጥታ ኃይል ክልከላ ተደርጎበታል፡፡ ኮማንደሩ እንዳስታወቁት፣ ጉዳዩ ሚዲያ እንዲዘግበው የሚፈለግ ባለመሆኑ የግልም ሆነ የመንግሥት እንዲሁም የክፍለ ከተማው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሳይቀር አልተጠሩም፡፡ በመሆኑም ጋዜጠኞች ከቦታው እንዲገለሉ አድርገዋል፡፡

 ከአዲስ አበባ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ፣ ኩባንያው በሕገወጥ መንገድ ከሌሎች ጋር ተጠግቶ ሲሠራ ነበር ይላል፡፡ ግንባታውም ፈቃድ የሌለው በመሆኑ ሊፈርስ መቻሉ ተገልጿል፡፡ ይህንን ተከትሎ ኩባንያው ከፍትሕ አካላት ዕግድ አውጥቶ የማፍረስ ተግባሩ እንዲቆምለት በመሯሯጥ ላይ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ስለጉዳዩ የሚያውቀው ነገር ስለመኖሩ ተጠይቆ ጉዳዩን እያጣራ እንደሆነ ገልጿል፡፡

‹‹ዛፖሪዚያ አውቶሞቢል ቢዩልዲንግ ፕላንት›› ወይም በአጭር አጠራሩ ‹‹ዛዝ›› በሚል ስያሜው የሚታወቀው የዩክሬኑ መኪና አምራች፣ ከኒማ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከተባለው አገር በቀል ኩባንያ ጋር በጋራ በመሆንና የእኩል ድርሻ በመያዝ፣ በኢትዮጵያ የገጣጠማቸውን መኪኖች ለገበያ ማቅረብ መጀመሩን በመግለጽ መግለጫ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ኩባንያው ከአንድ ዓመት በፊት የአገር ውስጥ አጋሩ ከሆነው ኒማ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር ባደረገው የእሽሙር ስምምነት መሠረት፣ ዩክሬን ሠራሽ መኪኖችን የሚገጣጥም ፋብሪካ በመገንባት ለገበያ ማቅረብ እንደሚጀምር የኩባንያው ኃላፊዎች አስታውቀው ነበር፡፡

የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ያኮቭ ዜለንዚያኮቭ በወቅቱ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በኒማ አግሮ ኢንዱስትሪና በዛዝ ኩባንያዎች በጋራ የተመሠረተው ኒማ ሞተርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ 35 መኪኖችን ተገጣጥመዋል፡፡ የዩክሬኑ ኩባንያ በቀን 25 መኪኖችን ለመገጣጠም ዕቅድ እንዳለው የገለጹት ደግሞ የኩባንያው የገበያና የሽያጭ ክፍል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ታምራት ናቸው፡፡ ሥራ አስኪያጁ ዜለንዚያኮቭ በዚህ ዓመት ብቻ 100 ያህል ተሽከርካሪዎች ለመገጣጠም ዝግጅት መደረጉን በመግለጽ፣ የኩባንያው ዕቅድ እንደሚሳካ ያላቸውን ተስፋ አስታውቀው ነበር፡፡

የኒማ ሞተርስ ባለቤቶች የ57 ሚሊዮን ብር ካፒታል ኢንቨስትመንት ጀምረው፣ በአሁኑ ወቅት እያካሄዱዋቸው ባሉት ማስፋፍያዎች ጠቅላላ ኢንቨስትመንቱን ወደ 100 ሚሊዮን ብር ከፍ እንደሚያደርጉትም ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ100 ያላነሱ ሠራተኞችንም መቅጠራቸውንም አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፣ የአውሮፓ ሥሪት የሆኑት መኪኖች እዚህ መገጣጠም መጀመራቸው ብቻም ሳይሆን በጄኔራል ሞተርስና በዴው ሞተርስ የሚመረቱ መኪኖችን ውስጣዊና ውጫዊ ይዘቶች ያሟሉ ተሽከርካሪዎችን ለኢትዮጵያ ገበያ ማቅረብ መጀመሩም፣ ለአገሪቱ የአውቶሞቶቭ ኢንዲስትሪ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው፡፡ ኩባንያው በአገር ውስጥ ለሚገጣጥማቸው መኪኖች በዚያው በመገጣጠሚያ ፋብሪካው የድኅረ ሽያጭ አገልግሎት አብሮ እንደሚሰጥም አቶ ዳንኤል ገልጸዋል፡፡

አራት ሞዴሎችን የሚገጣጥመው ኒማ ሞተርስ፣ ቻንስ፣ ቪዳ፣ ፎርዛና ሴንስ የተባሉትን የዛዝ ኩባንያ ምርት የሆኑትን ሴዳንና ሐችባክ መኪኖች አገር ውስጥ እየገጣጠመ የሚገኝ ሲሆን፣ ከ315 ሺሕ እስከ 480 ሺሕ ብር ድረስ ወይም ከ16 ሺሕ እስከ 24 ሺሕ ዶላር በሚገመት ዋጋ ለገበያ ሊቀርቡ እንደሚችሉ የኒማ ሞተርስ ድረ ገጽ ላይ የተለቀቁ የዋጋ መግለጫዎች ይጠቁማሉ፡፡

የዩክሬኑ መኪና አምራች ዛዝ የተመሠረተው እ.ኤ.አ. በ1923 እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ዛዝ ወደ ቤት አውቶሞቢል አምራችነት ከመቀየሩ በፊት የግብርና ማሽነሪዎችን ለማምረት የተመሠረተ ተቋም እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከጊዜ በኋላ በሶቪየት ኅብረት መንግሥት ተወርሶ እ.ኤ.አ. እስከ 1929 ድረስ የግብርና ማሽነሪዎች አምራችነቱ ቀጥሎ ነበር፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ. ከ1954 ጀምሮ አነስተኛ የቤት መኪኖችን ‹‹ሞስኮቪች 401›› በሚል ስያሜ ለገበያ ማቅረብ ከጀመረ በኋላም የአውሮፓን የመኪና ገበያ ከ25 እስከ 40 በመቶ ድርሻ መቆጣጠር ችሎ እንደነበርም ይነገርለታል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች