በመሀል አዲስ አበባ በመልሶ ማልማት ፕሮግራም 360 ሔክታር መሬት ላይ ባረፉ መንደሮች የሚገኙ ነዋሪዎች ሊነሱ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተነሺዎች ጋር መወያየት ጀምሯል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ መካከለኛውን የአዲስ አበባ ክፍል ከጎስቋላ መንደሮች ነፃ ለማድረግ አቅዷል፡፡ በዚህ መሠረት ከተያዘው በጀት ዓመት ጀምሮ 1,430 ሔክታር መሬት በመልሶ ማልማት እንደሚለማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡ ከዚህ ውስጥ በ2008 ዓ.ም. 360 ሔክታር መሬት ላይ ያረፉ ጎስቋላ መንደሮችን ለማልማት ዕቅድ ተይዟል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት አቶ ዘብረ ያይሎም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአካባቢ ልማት ጥናት የተሠራላቸው ፕሮጀክቶች የሚያርፉበት 360 ሔክታር መሬት የሚለማ በመሆኑ በዚህ ቦታ ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎችም ይነሳሉ፡፡
እነዚህ ቦታዎች የሚገኙት በየካ፣ በአራዳ፣ በጉለሌ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍላተ ከተሞች ውስጥ ነው፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ በዚህ ዓመት 68 ሔክታር መሬት ላይ የሚኖሩ 1,427 ነዋሪዎች ይነሳሉ፡፡
የየካ ክፍለ ከተማ መልሶ ማልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ሙላት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በየካ ክፍለ ከተማ ከካዛንችስ መናኸሪያ እስከ አዋሬ ድረስ ከመለስ ፋውንዴሽን ጀርባ ያለው 50 ሔክታር መሬት በመልሶ ማልማት ፕሮግራም ታቅፏል፡፡
ከዚህ ባሻገርም በመገናኛ አካባቢ ከኃይሌ ገብረ ሥላሴ ሕንፃ ጀርባ (ማራቶን ሕንፃ) እስከ ሾላ ገበያ፣ በመቀጠልም እስከ ለም ሆቴል ድረስ ያለው ሦስት ማዕዘን ቅርፅ ያለው 17 ሔክታር መሬት በዚሁ ፕሮግራም ታቅፏል፡፡
‹‹መረጃ በማጠናቀርና ተነሺዎችን በማወያየት ላይ ነን፤›› በማለት አቶ ዓለማየሁ ገልጸዋል፡፡ በአራዳ ክፍለ ከተማ የሠራተኛ ሠፈርና የአሮጌው ቄራ ያልተነሱ አካባቢዎችን ጨምሮ በአምስቱም ክፍላተ ከተሞች ተመሳሳይ ሥራ እየተሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር አዲስ ባወጣው ዕቅድ ነዋሪዎችን በማስፋፊያ አካባቢዎች ከማስፈር ይልቅ፣ በመሀል ከተማ ማስፈር ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡
ከ54 ሺሕ ሔክታር የአዲስ አበባ ይዞታ 60 በመቶው መልሶ መልማት ያለበት ሲሆን፣ ቀሪው 40 በመቶ የማስፋፊያ ክልል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በማስፋፊያ አካባቢዎች የሚገኙ ቦታዎች በማለቅ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚያካሂደውን የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ወደ መሀል ለማድረግ ማቀዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመልሶ ልማትና በወሰን ማስከበር ለሚነሱ 23,000 ተነሺዎች 6.2 ቢሊዮን ብር ካሳ ለመክፈልና 404 ሔክታር ምትክ ቦታ ለመስጠት ዕቅድ መያዙን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡