Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየሰማያዊ ፓርቲ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ያስተላለፈው አባላትን የማሰናበት ውሳኔ ውድቅ ተደረገ

የሰማያዊ ፓርቲ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ያስተላለፈው አባላትን የማሰናበት ውሳኔ ውድቅ ተደረገ

ቀን:

‹‹አቶ ዮናታን ተስፋዬ አሁንም የሰማያዊ ፓርቲ አባል ነው›› የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት

የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብን በመተላለፍ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመጠቀም ባሰራጯቸው መጣጥፎች የፓርቲውን ዓላማ፣ ፕሮግራምና ፖሊሲ መጣሳቸውን ገልጾ የፓርቲው ብሔራዊ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ በአራት ሥራ አስፈጻሚና ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ፣ ሰኞ ጥር 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ውድቅ ተደረገ፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት የብሔራዊ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴው ያስተላለፈውን አባላቱን ከፓርቲው አባልነት የማሰናበት ውሳኔ ውድቅ ስለተደረገበት ሁኔታ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአባላቱ ላይ ውሳኔ የተላለፈው ምልዓተ ጉባዔ ሳይሟላ ነው፡፡ ኮሚቴው ሰባት አባላት አሉት፡፡ ከሰባቱ አራቱ እንደፈረሙና ምልዓተ ጉባዔው እንደተሟላ ቢገለጽም፣ የኮሚቴው አባል መሆኑ የተገለጸው አንዱ አባል በውሳኔው እንዳልተሰማማና በቃለ ጉባዔው ላይም እንዳልፈረመ ገልጿል፡፡ በሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ምልዓተ ጉባዔው ሳይሟላና ቃለ ጉባዔ ሳይፈረም የተሰጠው ውሳኔ ተቀባይነት ስለሌለው፣ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ተሰብስቦ የነበረው የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔውን በሙሉ ድምፅ ውድቅ እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

እንደ ሥራ አስፈጻሚው አካልና የፓርቲ መሪነታቸው የፓርቲውን ደንብ ማስከበር እንዳለባቸው የገለጹት ኢንጂነር ይልቃል፣ ውሳኔን የመሻርና ይግባኝ የማለት ጉዳይ ሳይሆን ውሳኔው መተዳደሪያ ደንቡን የተከተለ እንዲሆን የማድረግ አሠራር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይግባኝ የማለትና ውሳኔ የመሻር ሥራ የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ሳይሆን የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚቴ ሥራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በብሔራዊ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴውና በሥራ አስፈጻሚው መካከል አለመግባባትና የመከፋፈል ሁኔታ ስለመኖሩ የተጠየቁት ሊቀመንበሩ፣ ‹‹መከፋፈል የለም፡፡ እስካሁን የሚታይና በተግባር የሆነ ነገር የለም፡፡ የመከፋፈል ፍላጐት ያለው አካል በተለያዩ ድረ ገጾች ሲጽፍ እናያለን፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ምንም ዓይነት ችግር አላየንም፤›› ብለዋል፡፡

ከሰማያዊ ፓርቲ ከጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ አቶ እያስጴድ ተስፋዬ፣ አቶ ዮናስ ከድርና አቶ ጋሻነህ ላቀ መሰናበታቸውን በፊርማቸው ያረጋገጡት የብሔራዊ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ ሃና ዋለልኝ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔን ይቃወማሉ፡፡ የተቃውሞአቸው ምክንያት ደግሞ የፓርቲው አባላት የተሰናበቱት ከሰባት የብሔራዊ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ አባላት አራቱ ተወያይተውና በቃለ ጉባዔው ላይ ተፈራርመው ያስተላለፉት ውሳኔ በመሆኑ ችግር እንደሌለው በመጥቀስ ነው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ሻምበል ካሳሁን ተገኝ፣ አቶ ሐሰን ቡሲርና አቶ ሲሳይ ካሴ በአባላቱ ላይ የቀረበውን የዲሲፕሊን ግድፈት ክስ ተነጋግረውበትና ተማምነውበት በቃለ ጉባዔው ላይ ፈርመው፣ ምልዓተ ጉባዔ በመሙላቱ ውሳኔ ማስተላለፋቸውን በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ ክስ የቀረበባቸው አቶ ዮናስ ከድር፣ አቶ እያስጴድ ተስፋዬና አቶ ጋሻነህ ላቀ ደግሞ ክሱ እንዳልደረሳቸውና መልስ አለመስጠታቸውንም አክለዋል፡፡ በመሆኑ የሥነ ሥርዓት ጉድለት ክስ በቀረበባቸው አራቱ የፓርቲው አባላት ላይ የተላለፈው ውሳኔ ትክክል መሆኑን ሃና ተናግረዋል፡፡

ከአራቱ የብሔራዊ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ አባላት መካከል ግን አቶ ሲሳይ ካሴ  አለመስማማታቸውንና በቃለ ጉባዔው ላይ አለመፈረማቸውን በማረጋገጣቸው፣ ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴው በሙሉ ድምፅ ውሳኔውን ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም አቶ ዮናታን ተስፋዬ የፓርቲው አባል ሲሆን፣ አቶ እያስጴድ ተስፋዬ፣ አቶ ዮናስ ከድርና አቶ ጋሻነህ ላቀ አሁንም የብሔራዊ ምክር ቤት አባል መሆናቸውን ኢንጂነር ይልቃል አስታውቀዋል፡፡

አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከፓርቲው ራሱን ስለማግለሉ በራሱ የፌስቡክ አድራሻ ገልጾ እያለ እንዴት ‹‹አባል ነው›› ሊሉ እንደቻሉ ተጠይቀው እንደገለጹት፣ አቶ ዮናታን አሁን ታስሯል፡፡ ከመታሰሩ በፊት የፓርቲው ምክር ቤት አባልና ሥራ አስፈጻሚ ሆኖ ሲሠራ የግል ሐሳቡን በነፃነት በራሱ አድራሻ ይገልጽ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አንዳንድ አባላትና አስተያየት ሰጪዎች ‹‹እንዴት የራሱን ሐሳብ እንደ ፓርቲው ሐሳብ አድርጎ ያቀርባል?›› የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው ራሱ ደብዳቤ ጽፎ ከሥራ አስፈጻሚና ከሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነቱ እንዲነሳ በጠየቀው መሠረት ከኃላፊነቱ መነሳቱን ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን አቶ ዮናታን ከፓርቲ አባልነቱ አለመልቀቁንና አሁንም አባል መሆኑን ኢንጂነር ይልቃል ተከራክረዋል፡፡ በድረ ገጹ የሚጽፈው ነገር ራሱን እንጂ ሌላ አካልን እንደማይወክል በእንግሊዝኛ ቋንቋ በራሱ አድራሻ በመግለጹ፣ ከፓርቲው እንደለቀቀ ተደርጎ መወራቱ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ መሆኑን ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል፡፡ አቶ ዮናታንን የፓርቲው አባላትም ሆኑ እሳቸው እንደ ጓደኛ፣ የአገር ልጅና  እንደ ታጋይም አሁንም መታሰሩን እንደሚቃወሙና እስከ መጨረሻው ከጎኑ እንደሚቆሙ ኢንጂነር ይልቃል አረጋግጠዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሪፖርተር አቶ ዮናታን ራሱን ከፓርቲው ማግለሉን በተመለከተ በሠራው ዘገባ ፓርቲው አስተያየቱን እንዲገልጽ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልነበር አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...