Friday, April 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ ተግባራት ይወገዱ!

በመንግሥትም ሆነ በግል ድርጅቶች ወይም በተለያዩ ተቋማት ሥራዎች አዋጭ ሆነው ውጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ፣ በጥናት ላይ የተመሠረቱና ከስህተት የፀዱ መሆን አለባቸው፡፡ ማንኛውም ሥራ በመርህ እንጂ በገጠመኝ መከናወን ስለሌለበት፣ በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ ተግባራት መወገድ አለባቸው፡፡ ማናቸውም ተግባራት አዋጭ ሆነው ውጤት ሲፈለግ፣ ለስህተት የማያጋልጡና ዋጋ የማያስከፍሉ አሠራሮች መስፈን አለባቸው፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚስተዋለው በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ ተግባራት ለስህተት ከመዳረጋቸውም በላይ፣ በአገር ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ሲያደርሱ ይታያሉ፡፡ መርህ ወደ ጎን እየተገፋ ገጠመኝ ስለሚበዛ፣ ችግሮች ሲፈጠሩ ርብርብ የሚደረገው እንደ አምቡላንስ በመሯሯጥ ወይም እንደ ድንገተኛ እሳት አጥፊ በመተራመስ ነው፡፡ አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን እያነሳን እንመልከት፡፡

በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ድንገት ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ የሚያቀርብ መሆኑን በማስታወቁ፣ የውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎች ከተለያዩ የግል ባንኮች 4.5 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወደ ንግድ ባንክ አስተላልፈዋል፡፡ ይህ ድንገተኛና ያልተጠበቀ ክስተት የግል ባንኮችን ከፍተኛ ሥጋት ላይ ጥሏል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ በጥናት ላይ ያልተመሠረተ ግብታዊ እንቅስቃሴ የግል ባንኮችን መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ድንገት ሲያፈልስባቸው፣ ደንበኞቻቸው ደግሞ ወደ ትልቁ ተፎካካሪያቸው ሲሄዱባቸው፣ የቀረቡላቸውን የብድር ጥያቄዎች እንደገና ወደ መመርመር ሲገቡ፣ ላልተጠበቁ ወጪ ሲጋለጡና የተለያዩ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ሲደርሱባቸው የምትጎዳው አገር ነች፡፡ በአገሪቱ ከሚገኙ 16 የግል ባንኮች መካከል አንዱ ብቻ ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ድንገት ሲወሰድበት ከፍትሐዊነትም ሆነ ከጤናማ ፉክክር አንፃር አሳሳቢ ነው፡፡

አገሪቱ በነፃ ገበያ ሥርዓት እየተመራች ነው እየተባለና ባንኮችም የውድድሩ ሜዳ ተስተካክሎላቸው ጤናማ ፉክክር ማድረግ ሲገባቸው፣ ንፋሽ አመጣሽ በሆነ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ምክንያት መጎሳቆል የለባቸውም፡፡ የተከናወነው ድርጊት በጥናት ላይ የተመሠረተ ቢሆን ኖሮ ንግድ ባንክ ያቀረበው የውጭ ምንዛሪ ቀድሞ መታወቅ ሲኖርበት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ደግሞ የግል ባንኮች መረጃው እንዲደርሳቸው በማድረግ፣ የውጭ ምንዛሪውን የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸትና በመሳሰሉት ዘዴዎች ትርምስ እንዳይፈጠር ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ጤናማ ፉክክር እንዳይኖር የሚያደርግ ተግባር በመፈጸሙ፣ ብሔራዊ ባንክ እሳት የማጥፋት ሥራ ውስጥ ነው የገባው፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከግል ባንኮች ኃላፊዎች ጋር አደረገው በተባለው ምክክር ከእያንዳንዱ ከሚሰጡት ብድር ለቦንድ ግዥ የሚያውሉትን 27 በመቶ ክፍያ እንዲያዘገዩ፣ የገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ደግሞ ለቦንድ ግዥ ያዋሉትን ገንዘብ በማስያዝ፣ ከብሔራዊ ባንክ በሦስት ወራት ክፍያ የሚያገኙትን ብድር አቆይተው እንዲከፍሉ ቃል መገባቱ ተሰምቷል፡፡ አፈጻጸሙ እንዴት ይሆናል የሚለው ደግሞ ወደፊት እንደሚታይ ተገልጿል፡፡ ሲጀመር በጥናት ላይ ያልተመሠረተው አካሄድ ችግር ቢፈጠር ምን ይደረጋል ለሚል ጥያቄ ተጠባባቂ ዕቅድ አልያዘም፡፡ የግል ባንኮች ጫጫታ ውስጥ ሲገቡ ደግሞ አፈጻጸሙ ወደፊት ይታያል ተብሎ ቃል ተገብቷል፡፡ በዚህ መሀል ባንኮቹ ኪሳራ ቢያጋጥማቸው፣ ሠራተኞች ቢቀንሱ፣ ቅርንጫፎችን ቢዘጉ፣ ወዘተ ዓይነት ችግሮች ባለመታየታቸው ከመርህ ይልቅ ገጠመኝ ጎልቶ ታይቷል፡፡ 

ከዚህ መራር አጋጣሚ ውስጥ ወጥተን በተለያዩ ሥፍራዎች የሚከናወኑ ተግባራትን ስንቃኝ የአምቡላንስ ዓይነት ሩጫ ነው የሚታየው፡፡ ዕቅዶች መሠረታዊ በሆኑ ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ ተመሥርተው ሳይወጡ ይቀርና ውጤቱ ሲበላሽ ይታያል፡፡ ወይም ደግሞ ዕቅዶች ከመጠን በላይ ተለጥጠው ወጥተው ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ሳይጣጣሙ ይቀሩና በአፈጻጸም ድክመቶች ተመካኝቶ ውድቀት ይመዘገባል፡፡ ነገር ግን ሥራዎች አዋጭ የሆኑ ጥናቶች ተካሂደውባቸው፣ ደካማና ጠንካራ ጎኖች ተፈትሸውባቸውና መተማመን ላይ ሲደረስባቸው ለአፈጻጸም ምቹ ስለሚሆኑ ውጤታቸውም አመርቂ ይሆናል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ተግባራዊ ተደርገው ውጤታቸው ከተበላሹት መካከል እነ ውኃ ማቆር፣ ውጤት ተኮር፣ ቢፒአር፣ ወዘተ የሚረሱ አይደሉም፡፡ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የአገር ሀብት የበሉ የመከኑ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

በሚገባ ጥናት የሚደረግባቸውና  አዋጭ የሆኑት ግን የፕሮጀክቶች ጤናማ አካሄዶች፣ የምርት ወይም የአገልግሎት የተብራሩ ዝርዝሮች፣ ጥርት ያሉ የሒሳብ መግለጫዎች፣ ግልጽ የሆኑ አሠራሮች፣ የአመራሩን ብቃትና ተነሳሽነት፣ የገበያ ጥናት፣ በሚገባ የተዘጋጀ የፋይናንስ ዳታ፣ የሕግ ማዕቀፎች፣ የታክስ ግዴታዎችና አጠቃላይ የፖሊሲ አቅጣጨዎችን በጥራት ያመላክታሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነት ቀጥተኛ መንገድ ማንኛውም ሥራ ገና ከጅምሩ ተዓማኒነት ሲኖረው፣ ከሙስና የፀዳ ሲሆን፣ ግልጽነት የተላበሰና ተጠያቂነትን ያካተተ ሲደረግ መተማመን ይፈጠራል፡፡ በሒደት ላይ እያለም እንከኖች ሲያጋጥሙ ለማረምና ለማስተካከል ቀላል ይሆናል፡፡ በተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ በመሆኑም ውጤቱ አስተማማኝ ነው፡፡ ከገጠመኝ ይልቅ ለመርህ ስለሚቀርብ ለአገር ልማትና ዕድገት ተመራጭ ነው፡፡

አሠራሮች ከልማዳዊ ድርጊት ይልቅ በተግባር የተፈተኑና አሳማኝ ሲሆኑ፣ ችግሮችን ለመፍታትና የተሻሉ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማስፈን ይረዳሉ፡፡ በግምት ወይም በነሲብ የሚፈጸሙ ተግባራት ግን አገርንና ሕዝብን ይጎዳሉ፡፡ የአገር ሀብት ያወድማሉ፡፡ የሕዝብን ተስፋ ያጨልማሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነት ችግሮች ምክንያት የሚፈጠሩ ድንገተኛ ክስተቶችን ለማስተካከል የሚደረገው መሯሯጥ የበለጠ ወጪ፣ ጊዜና የሰው ኃይል ያባክናል፡፡ በየቦታው በግምት የሚሠሩና አገርን ዋጋ የሚያስከፍሉ ድርጊቶች በአስቸኳይ ይቁሙ፡፡ ሳይንሳዊ በሆነ ጥናት ላይ ያልተመሠረቱና ከዘመኑ ጋር የማይሄዱ ክስተቶች አገር አይበጥብጡ፡፡ ለአገር ዕድገት የሚተጉ ዜጎችንም ተስፋ አያስቆርጡ፡፡ በመሆኑም በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ ድርጊቶች ይወገዱ!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...