የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠትና በሕግ ጉዳዮች ለመተባበር የሚያስችለውን ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ለአሜሪካ ሊልክ ነው፡፡
የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የወንጀል ተግባራት አገራዊ ከመሆን ይልቅ ዓለም አቀፋዊ ባህሪና ገጽታ እየያዙ በመምጣታቸው ስምምነቶችን ከአገሮች ጋር በመፍጠር መተባበር ያስፈልጋል፡፡
ይህንን መሠረት በማድረግም በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል የተዘጋጀው የስምምነት ሰነድ ለአሜሪካ መንግሥት እንዲደርስ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መላኩን ጠቁመዋል፡፡
የወንጀል ተግባራት ዓለም አቀፋዊ ገጽታንና ባህሪን እየተላበሱ በመሆኑ የአገርን ጥቅምና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ከአገሮች ጋር ስምምነቶችን በመፈራረም ትብብርን መፍጠር እንደሚያስፈልግ፣ ይህም ዓለም አቀፋዊ አሠራር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ወንጀለኞችን አሳልፎ ከመስጠት ባሻገር በሲቪልና በንግድ ጉዳዮች ረገድም ትብብር ለማድረግ ስምምነቱን በመፍጠር፣ የአገርንና የሕዝብን ጥቅም ማስከበር ኃላፊነትንም እንደሚያካትት አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ያለው ከአሜሪካ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጋር መሆኑንም አክለዋል፡፡
የስምምነት ሰነዱ ለሳዑዲ ዓረቢያና ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ተልዕኮ አገሮቹም በስምምነት ሰነዱ ላይ አስተያየት መስጠታቸውን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ደግሞ በወንጀልና በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች የፍትሕ ትብብር ለማድረግ ረቂቅ ሰነድ ተልኮ ከአገሪቱ መንግሥት አስተያየት መሰጠቱን አውስተዋል፡፡
‹‹በምንልካቸው የስምምነት ሰነዶች ላይ አስተያየቶች ይኖራሉ፡፡ አስተያየቶቹን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው በማይሰጡና የእኛን ጥቅም በሚያስከብር መንገድ የእነሱንም ጥቅም በሚጠብቅ መንገድ መሆኑን አረጋግጠን፣ ስምምነቱ ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው ይደረጋል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ልታቀርብ እንደተሰናዳችው የፍትሕ ትብብር ጥያቄ ሌሎች አገሮችም ለኢትዮጵያ እንደሚያቀርቡ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥም ከሰባት አገሮች ለቀረቡ የወንጀል ትብብር ጥያቄዎች ምላሽ መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡