በአማኑኤል ነጋ
የተወዳጁ ሪፖርተር ጋዜጣ አዘጋጆች ዛሬ ብዕሬን ያነሳሁበት ጉዳይ ጥበብ (ኪነ ጥበብ) ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ይኼውም ድራማ፣ ፊልም፣ ሥነ ግጥም፣ ሥነ ጽሑፍና ሥነ ሥዕል የመሳሰሉት የፈጠራ ውጤቶች ሁሉ በማካተት ነው፡፡ በዚህ መነሻ በአገሪቱ ያሉ ደራሲያን፣ ተዋንያን፣ ሐያሲያንና ሌሎችም ቢስማሙም ባይስማሙም ምልከታዬን አንብበው ምላሻቸውን እንደሚያደርሱ እገምታለሁ፡፡ በጉዳዩ ላይ ሐሳብን ከመስጠት ይልቅ ዝምታን መርጠው ካለፉትም ሂስን እንደተቀበሉት ቆጥሬ፣ ተጨማሪ ግምገማዊ ሒሶችን ለማስፈር እሞክራለሁ፡፡
የጽሑፌ ትኩረት በአገራችን እየተዘሩና እየታጨዱ ያሉ ‹‹በርካታ የኪነ ጥበብ ምርቶች›› ሥነ ጽሑፋዊ አላባዊያንን መፈተሽ አይደለም፡፡ የደራሲያንን የፈጠራ ምጥቀት ወይም የታዳሚዎችን ጥበባዊ ተሳትፎ መገምገም ሊሆን አይችልም፡፡ ይልቁንም አገራችን የጀመረችውን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስፈን ጥረት ጥበብ እንዴት እየመራውና እየገዛው (ሒስ በማድረግም) እንደሆነ መፈተሽ ነው፡፡ ደራሲያንና የጥበብ ሰዎችስ ማኅበራዊ ሒስን፣ አስተምህሮንና ትችትን እንዴት እያስኬዱት እንደሆነ መጠየቅ ይሆናል፡፡
ቧልትና ትርኪምኪ ምን ያደርጋል?
የጥበብ መሠረታዊ ዓላማ ማስተማርና ዳግም መፈጠር ነው፡፡ ማዝናናት ሊኖር የሚችለው ሕይወትና ማንነትን በመሔስ ውስጥ እንደመሆኑ፣ በተለይ በታዳጊው ዓለም ውስጥ ‹‹ወደው አይስቁ›› እያለ በጥበብ ሥራዎች ዜጋው ውስጡን እንዲፈትሽ ካልተደረገ ሳቅ፣ ቧልትና ፌዝ ብቻ አየሩን ከሞሉት ነገር ይበላሻል፡፡ አገርና ቁም ነገርም ፈቀቅ ሊሉ አይችሉም፡፡
የሠለጠነው ዓለም የኪነ ጥበብና የሥነ ጥበብ ሥራዎች ከጥንት ጀምሮ የሚያተኩሩት ማኅበረሰብን መቅረፅ፣ ዕውቀትና ቴክኖሎጂን ማሳደግና የሰው ልጅን የማያባራ ዕቅድ (Ambition) ማሳየት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሆሊውድም ሆነ ቦሊውድ የየአገራችውን ርዕዮተ ዓለም፣ ባህል፣ ሥልጣኔና ዕውቀት ወደ ሌላው ዓለም የማስረፅና የማስተጋባት አትኩሮት ያላቸው መስሏል፡፡
ለሁሉም የአገራችን ወቅታዊ የጥበብ ሥራዎች (በተለይ ሙዚቃ፣ ፊልም፣ ልቦለድና ሥነ ግጥም) ስንመለከት በአብዛኛው የኮሜዲ ዘውግ ተኮር ናቸው፡፡ በተለይ እንደ አሸን እየፈላ ባለው የሲኒማ ኢንዱስትሪ ውስጥ በአብዛኛው በሳሎን ምችት ያለ የቅንጦት ኑሮ፣ ከአገሪቱ ሕዝብ 17 በመቶውን ከተሜ ብቻ የሚወክል ርዕሰ ጉዳይ፣ በአሰልቺ ሳቅና ፈገግታ የሚታለፍ ፍሬ አልባ ጭብጥ የተሞላ ነገር መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡
ገና ከድህነት ቀና በማለት ላይ ባለ አገር ውስጥ እጅግ አስገራሚ ቪላና ፎቅ ቤቶች (በእውነታውም የጥቂቶች ብቻ በሚባሉ)፣ ዘመናዊ የሚባሉ ተሽከርካሪዎች፣ ለብዙዎች ባዕድ የሚባል አመጋገብና አለባበስ ተንበሻብሾ መታየቱ ‹‹የገጽታ ግንባታ›› ዓላማ ቢሰንቅም ከእውነታው (Reality) ውጭ ነው፡፡ በተዋንያን ደረጃ እንኳን ‹‹ቆንጆ›› የሚባሉ የከተማ ልጆች፣ የተለመዱና ቀስ በቀስ ወደ አደባባይ መውጣት የጀመሩ ፊቶች ብቻ እንደያዙት ነው፡፡
ቁም ነገሩ ይኼ አይደለም፡፡ ደራሲያንና ጸሐፍት ስለምን የመሪነት፣ የሐያሲነት፣ የማኅበረሰባዊ ነቃፊነትና አስተማሪነት ሚና መጫወት ተሳናቸው? የሚለው ጥያቄ ሲመዘዝ ጠባቂነት፣ ልመና፣ በሥራ ያለመረዳዳት፣ የፈጠራ ማነስ፣ ምቀኝነት፣ ወዘተ የመሰሉ የኖሩ እንቅፋቶች አሉብን፡፡ ከቦታ ቦታ ቢለያይም በጥናትና በምርምር ሊፈለቀቁ የሚችሉ በርካታ የፀረ ድህነት ትግሉ ማነቆዎች እንዳሉ ጥርጥር የለውም፡፡
‹‹መልካም አስተዳደርን እናረጋግጥ›› ሲባልም መንግሥትንም ሆነ ሕዝብን እግር ከወርች የሚያስሩ ዳራዎች ቀላል አይደሉም፡፡ ሙስና (ጉቦ)፣ ጉቦ ሰጭነት (ሲሾም ያልበላን ማላዘን) አድርባይነት፣ ጠያቂ ያለመሆን፣ ሁሉን ‹‹ለፈጣሪ›› መተው፣ መንግሥትና ሠራተኞቹ አገልጋይ መሆናቸውን አለመቀበል፣ ‹‹ይመለከተኛል›› አለማለት፣ ወዘተ የለውጥ ነቀርሳዎች የትኛው የጥበብ ሰው አወገዘ? ነቀፈ? ወይም አስተማረባቸው? በእርግጥ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚታዩ የዘመድ ሥራዎች፣ ሙስናዎችና የኔትወርክ ሌብነቶችን ለማጋለጥ የሚሞከርበት አለ ቢባልም፣ ጠንካራና ተከታታይ የሚባል ግን አይደለም፡፡
በተጨባጭ እንደምናየው በአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያሉ የሥራ ኃላፊዎች የአቅም ማነስ፣ ራስን የማሳበይና አገልጋይነትን ለመርሳት የመሞከር አዝማሚያ፣ በቅንጦት ተሽከርካሪ፣ ቢሮና ወንበር ለመታየት ብቻ ሳይሆን፣ በብዙ አጃቢ፣ በሁለትና በሦስት ጸሐፊ ለመከበብ መጣር … እውነት ጥበብ ሊነቅፈውና ሊተቸው የሚችለው አይደለም፡፡
በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደቱ ውስጥም ቢሆን ጥበብ እያወገዘች፣ እየተቸችና እያንገዋለለች የምታወጣው ብዙ ድክመት አለ፡፡ የመንግሥትን፣ የፖለቲካ ኃይሎችንም ሆነ የማኅበረሰቡን እንከኖች በመንቀስ ገንቢ በሆነ መንገድና ለሥር ነቀል ለውጥ በሚበጅ መንገድ የማስተማር ድርሻ ለፈጠራው ሰው ካልተሰጠው ለምን ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹ጥበብ የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ ነው›› ሲባል እኮ ሌላ ማለት አይደለም፡፡
የዴሞክራሲያዊ ጉዟችን እንቅፋት የሚባሉት ‹‹ጽንፈኛ›› ተቃውሞና ‹‹ጭፍን›› ድጋፍ በውስጣቸው ጥላቻ፣ አድርባይነትና ውሸት የሞሉባቸው ናቸው፡፡ የመቻቻል መዳከም፣ የብሔራዊ ስሜት መቀዛቀዝ፣ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ያለመጎልበት፣ ይበልጡኑ ልዩነትን የማቀንቀን ልክፍት ሁሉ አስትምህሮን ይፈልጋሉ፡፡ ብዙኃኑን ሳያሳትፍፉ የይስሙላ ማወያየት፣ አቋም ይዞ ያለመታገል፣ ለሕግና ሥርዓት ያለመገዛት፣ አርዓያ ሆኖ አለመገኘት፣ ሥልጣን ወይም ሞት ማለት፣ ወዘተ ሁሉ ከየትም ይምጡ ከየት መነቀፍ ነበረባቸው፡፡
ለአዲሱ ትውልድ በቀደመው ዘመን የነበረውን ትምክህት፣ አፋኝ አስተሳሰብና ሽር ጉድ ከመንገር ይልቅ በተጀመረው ጉዞ ላይ ከፍ ያለ ሥዕል ማስረፅ ይገባ ነበር፡፡ ዴሞክራሲ የሥልጡነንት መገለጫ፣ ፖለቲካም እንደ ኤሌክትሪክ የሚፈራ እንዳልሆነ፣ ለአገር፣ ለባንዲራና ለማንነቱ የሚቆም ዜጋን ጥበብ ካልቀረፀ ማን ይሥራው?
በመሠረቱ ሁሉንም የጥበብ ሥራዎችና ደራሲያንን በጅምላ መውቀስ ባይሆንብኝም፣ ከላይ በተነሱት ነጥቦችና አጠቃላይ የማኅበረሰብ መቅረፅና ማስተማር ላይ ያተኮሩ ሥራዎች እየቀነሱና እየጠፉ ነው፡፡ እርግጥ በጣም ትንንሽ ፊልሞችና ባለፈው ሥርዓት ላይ ያተኮሩ በርካታ ታሪክ ቀመስ መጻሕፍት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሀቅና የመጪው የሥርዓት ቀረፃ ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን ማግኘት ግን እጅግ ፈታኝና የመነመነ ሆኗል፡፡
‹‹እንዲህ ዓይነት ባህልም ሆነ ተሞክሮ በአገራችን በፊትስ ቢሆን መቼ ነበር?›› እንዳይባል ደግሞ ለሐሳብ ነፃነትም ሆነ ለፈጠራና ለጥበብ ሥራ እምብዛም ዕድል በማይሰጡ ሥርዓቶች እንኳን ዕውን ሆኖ ዓይተናል፡፡ ‹‹አልወለድም››፣ ‹‹ኦሮማይ›› (አቤ ጉበኛና በዓሉ ግርማ) ያሉ ልቦለዶች፣ እንደ ‹‹ሀሁ … ፐፑ›› (ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን) ያሉ ቴአትሮች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ አስከፊውን የንጉሣዊ ሥርዓት በማየት ረገድም ‹‹በኮሌጅ ቀን›› ይቀርቡ የነበሩ የነመላኩ ተገኝ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ ተገኝ የሸወርቅ፣ ይልማ ከበደ፣ መሐመድ እድሪስ፣ ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) እና አበበ ወርቄ ግጥሞች የጥበብን አስተማሪነት ብቻ ሳይሆን የለውጥ መንገድን ያመላክታሉ፡፡ የሚመራ ሥርዓትም ሆነ ሕዝብ ካለም በግልጽ ያስተምራሉ፡፡
እንግዲህ በእነዚህ ተሞክሮዎች እየተደመመ ያደገ ሰለሞን ሞገስ የተባለ ጸሐፊ በአንድ መድረክ ላይ ‹‹ስብሐት ለአንተ›› ሲል የተቆጨው ለዚህ ይሆን?
ደሞ አንተን ብሎ ደራሲ አንተን ብሎ ብዕረኛ
ወገኛ!!
ስንቶች ብዕር ጨብጠው ታግለው በክብር ሲሞቱ
ከረሃብ፣ ከድንቁርና ከግፈኛ ሲሟገቱ
እንደ ሻማ ነደው ቀልጠው
ታሪክ ጽፈው ታሪክ ሆነው
እያየነው እያየኸው፡፡
አንተ ግን ጓሮ ለጓሮ
ህሊናህ በሴስ ታውሮ
የወገን ቁጭት የሌለህ
የአገር ፍቅር የጎደለህ
ሺሕ ቅዠቶችን ሰብስበህ
ስንቱን ከስንቱ አወሳስበህ
ደሞ አንተም ጻፍኩ ትላለህ?
ይኼ ነው ይ የአንተ ማሳ?
‹‹ገለባ፣ ተኛ፣ ተነሳ››
አዘንኩ ዓይቼ ሳበቃ
ጥበብ ቆሻሻ ላይ ወድቃ
ኤዲያ! አንተን ብሎ ጸሐፊ
ሴሰኛ ወሬ ቸፍቻፊ!!
ጋኖች አለቁና ዛሬ
ምንቸት ጋን ሆኗል በአገሬ፡፡
(እውነትን ሰቀሏት 2001÷28)
ገበያውና ታዳሚው ጥበብን አይሻም?
አሁን አገራችን ያለችበት ሁኔታ የጦርነት አይደለም፡፡ ፍፁም የለየለት የአፈናና የፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ዘመንም ታልፏል፡፡ ቢያንስ የሕዝቦች ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ማንነት የሚታወቅባትና በእኩልነት የሚደመጥባት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ተዋቅሯል፡፡
ይህ ሁሉ ሆኖም አሁንም ድህነቱ (በየጊዜው የሚመላለሰው ድርቅ ዘንድሮም አለ) ድሪቶ የሚያስለብስ ነው፡፡ ዴሞክራሲውም ይባል መልካም አስተዳደሩ አያኩራራም፡፡ በጠባብነት ውስጥ ውስጡን ጥላቻ የሚነዛ፣ ቢያመቸው ከመተላለቅም ወደኋላ የማይል ኋላቀር በቀለኛ በየሸጡ ተሠልፏል፡፡ ሕግና ሥርዓት ዘነፈ ቢባልም በትምክህትና እኔ አውቅልሃለሁ አዙሪት ሁሉንም ጨፍልቆ በእፍኙ ለማስገባት የሚቋምጥም አይታጣም፡፡ ይህን ዓይነቶቹን የአስተሳሰብ ዝንፈቶች ደግሞ መንግሥት ብቻ ሊፈታው አይችልም፡፡
ይልቁንም ከትምህርት ቤቶችና ከእምነት ተቋማት ባሻገር የጥበብ አውድማዎችና መገናኛ ብዙኃን የጎላ የአስተምህሮ ሚና አላቸው፡፡ በተለይ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ካላቸው የተደራሽነትና የተፈላጊነት ባህሪ አኳያ፣ ሕዝቡንም ሆነ መንግሥትን የማንቃትና የመንቀፍ ብሎም ቅርፅና ትክክለኛ ፈለግ እንዲይዙ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ይህ እውነት ዕውን እንዳይሆን ግን ከደራሲያንና ከፈጠራ ባለሙያዎች የዕውቀት፣ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ባሻገር የሕዝቡ ፍላጎት አለመኖርና የገበያው ሁኔታም መስመር እንደሚያስት የተለያዩ የዘርፉ ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡
ትራጄዲ ቴአትር ወይም ፊልም ላለመሥራት ‹‹የሕዝቡ (ታዳሚው) የኮሜዲ ፍላጎት ጣሪያ ነክቷል፤›› ብለው በየመንደሩ አስቂኝ አባባል የሚፈልጉ ተዋናያንና ‹‹ደራሲያን›› እየበዙ ነው፡፡ መንግሥትን ወይም አሠራሮችን መተቸት ‹‹ያሰቅላል›› ብለው የሚሠጉ ወይም የሚያራግቡ ፈሪዎችና አድርባዮች የጥበቡን መድረክ ሞልተውታል፡፡ ‹‹እንትንሽ፣ እንትንህ፤…›› እያሉ የሰዎችን ጉያ መግለብ እንጂ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ነባርና መጤ እሴቶችን በማስተዋወቅና በመተቸት በኩል የተሳካላቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
እንደ አገር ለዘመናት በገነባናቸው ትምህርት ቤቶች፣ የእምነት ተቋማት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ፍርድ ቤቶች፣ ምክር ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎችና እስር ቤቶች … ውስጥ ምን እውነት አለ? ሕፀፆቻቸው ምንድን ናቸው? ብሎ መፈተሽ የጥበበኛው መሆን አለበት እንጂ ተመልካች፣ አንባቢ ወይም አድማጭ ‹‹አይቀበለኝም›› በሚል ሥጋት ስሙኒና ሽልንግ እያሰበ የሚጠበብ ‹‹ነጋዴ›› አገር አይለውጥም፡፡ ጥበብ የመሪነት ሚናዋን እንድትጫወት ማድረግም አይችልም፡፡
እርግጥ ታዳሚዎች ዕውቀት፣ ክብርና አድናቆት ሊሰጡ የሚገባቸውን የጥበብ ሥራና ጭብጥ ማወቅ አለባቸው፡፡ ምናልባት ማኅበረሰባችን የደረሰበት የግንዛቤ ደረጃም ሆነ ለኪነ ጥበብ የሚሰጠው ዋጋ እንደ ሠለጠነው ዓለም የዳበረ ነው ላይባል ይችላል፡፡ ይሁነንና የሺሕ ዓመታት ታሪክ፣ የተለያዩ ቱባ ባህሎች (Diversified Cultures)፣ በርካታ ቋንቋዎች፣ ለዘመናት የኖረ የነፃነት ኩራት፣ የሃይማኖት፣ የማንነት ዘውግና እሴቶች በከተሙበት አገር ውስጥ ፌዝና ቧልት ብቻ የጥበብ ውጤቶችና ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በዚያ ላይ ገና ከተሸከምነው ችግር አንፃርም ሆነ ልንደርስበት ከምንመኘው የዓለም ተርታ ለመሠለፍ፣ አርቆ መመኘትና ማስተዋል የሚል ጥበበኛን መሸከም የሚችል ታዳሚ መሆን ያስፈልጋል፡፡
አንዳንዶች የአሁኑን ትውልድ ከቀድሞ የአገራችን ትውልድ ያነሰ፣ ደንታቢስ፣ ኃላፊነትን የማይሸከም፣ ኢትዮጵያዊ እሴቱ የነጠፈ፣ በሌላው ዓለም የጭንቅላት ወረራ ቅኝ የተገዛ፣ ወዘተ በማለት ያቀርቡታል፡፡ በዚህ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ለመስማማት ቢከብደኝም፣ ይህ ትውልድ ያሉትን በርካታ በጎ መገለጫዎችን ያህል ቀስ በቀስ ትጥቅ የፈታባቸው የማንነት ክፍተቶች እንዳሉም ይሰማኛል፡፡ ከዚህ አንፃር አንድ ገጣሚ የቋጠራቸውን ጥብቅ ሂሳዊ ስንኞች ላስፍር፡፡
አያቴ አለቱን ፈልፍሎ ቤቱን ሐውልቱን አነፀ
ይኼም ከዘር – ዘር ተላልፎ በደሜ ስለሰረፀ
እኔም የጥንቱን ያዝኩና አለት እፈለፍላለሁ
ሰዋራ ዋሻ ሠርቼ መንገደኞችን እዘርፋለሁ፡፡
ከዚህ አንፃር ትውልድ ከተወቃሽነትም ለመዳን ሆነ ከፍ ያለችን አገር ወደ ሌላ ትውልድ ለማሻገር ለእውነት፣ ለአገራዊ ስሜት፣ ለትክክለኛ ታሪክ፣ ለፍትሕ፣ ለመከባበር፣ ለመቻቻል፣ ለሰላም፣ ለመረዳዳት፣ ወዘተ፣ የሚቀነቀን ጥበብ፣ ዋጋና ክብር ሊያሳድግ ግድ ይለዋል፡፡ ቧልትና ጨዋታ ይጥፋ ባይባልም ኮሜዲና የጓዳ ወሬ ላይ ብቻ ተጥዶ የሚንተከተክከው ጥበባችን አደባባይ ይውጣ መባል አለበት፡፡
በሐሳብ ነፃነት ውስጥ ‹‹በአሠራር›› የተጋረዱ እንቅፋቶች
ከሁላችንም የበላይ የሆነው ሕግና አገራችንም የምትተዳደርበት ሕገ መንግሥት በአንቀፅ 29 ንዑጽ አንቀጽ 1 ላይ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፤›› ወረድ ይልናም ይህ ነፃነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመትና በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል ይላል፡፡
ይህ መሠረታዊ ድንጋጌ በመገናኛ ብዙኃን ውጤቶች ላይም ሆነ በኪነ ጥበብ ሥራዎች ላይ ቅድመ ምርመራና ክልከላን አስወግዷል፡፡ እርግጥ ሥራዎቹ ከሕዝብ ለሕዝብ የሚሠሩ እንደ መሆናቸው ሕግና ሥርዓቱን ተከትለው፣ የዜጎችን ሞራላዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ጠብቀው ሊከወኑ ግድና አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን እገሌን ለማስደሰትም ሆነ ለማስከፋት ተብሎ መጨነቅ የትም አያደርስም፡፡
አንዳንድ የመስኩ ሙያተኞች እንደሚሉት ግን በአገሪቱ የሐሳብ ነፃነት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ቢያገኝም፣ የቅድመ ምርመራ መቀስ ተጥሏል ቢባልም፣ እንደ ጋዜጠኛው ሁሉ የጥበብ ሙያተኛውን የህለና ዕቅድ ምርመራ የሚያደርጉበት ተፅዕኖዎችና ምክንያቶች (Push Factors) አሉ፡፡
አንደኛው ፊልም ቴአትር ተሠርቶ የሚታይበት የፊልም ቤት (መድረክ) ማጣት ነው፡፡ በአገሪቱ ያሉ አብዛኛዎቹ መድረኮች በመንግሥት መዋቅር ሥር በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ በመንግሥት አካላት በኩልም ሒስን የመቀበል ልምዱም ስላልዳበረ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ የግል ሲኒማ ቤቶችም ከፍርኃት የተነሳ ብዙም ፍላጎት አያሳዩም፡፡
ሁለተኛው ለየትኛውም የኪነ ጥበብ ውጤት ቢሆን ስፖንሰርና ደጋፊ ማግኘት ቀላል አለመሆኑ ነው፡፡ በተለይ ከፍተኛውን የኢኮኖሚ ድርሻ በያዙት መንግሥታዊ ድርጅቶች፣ የኢንዶውመንት ኩባንያዎችና ‹‹ልማታዊ ባለሀብቶች›› የመንግሥት ፖሊሲ፣ አሠራርና አካሄድን የሚተች የጥበብ ሥራ መደገፍ በፖለቲካ ተቃውሞ የሚያስፈርጅ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የኅትመት ሥራም ቢሆን የማተሚያ ቤት፣ የማከፋፈያ ሱቅና መሰል ችግሮች እንደሚገጥሙት ልብ ይሏል፡፡
በመሠረቱ የዴሞክራሲ ባህልን ለመገንባት ያለመና የተነሳ መንግሥታዊ ሥርዓት የሐሳብ ነፃነትን፣ ገንቢ የሆነ ሒስንም ሆነ አስተማሪ ትችትን ሊጠላ አይችልም፡፡ ይሁንና በአተገባበርና በአሠራር ሰበብ ግልጽነትና ተጠያቂነትን መድፈቅ፣ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን ማቆርቆዝም ሆነ መንግሥትም ቢሆን ተቆጪ (ሒስ አድራጊ) መሆን እንዳለበት እንዲረሳ ማድረግ ፀረ ዴሞራሲያዊ ድርጊት ነው፡፡ በእርግጥ በሕገ መንግሥት የፀናን ‹‹ነፃነት›› የሚሸራርፉትም ሆኑ የሚንዱት ሰዎች (የመንግሥት አካላት) እንደመሆናቸው መፍትሔው እነኝህ ከሕግና ሥርዓት የወጡ አካላትን መታገል ብቻ ነው፡፡ የመንግሥት ሥውር እጅ የሚመስል የተደራጀ ድርጊት ካለም ማጋለጥና በተቀናጀ መንገድ (በተለይ ጠንካራ ማኅበራት ቢኖሩ) መፋለም ነው መፍትሔው፡፡
መንግሥትም ቢሆን በተለይ አሁን ዴሞክራሲው አልዳበረምና መልካም አስተዳደር አለመስፈን (የግልጽነትና የተጠያቂነት ድክመት) በታየበት ሁኔታ ራሱን ከትችትና ከሒስ ማራቅ፣ ሁሉንም ጉዳይ ‹‹የፖለቲካ ጥላቻ›› አስመስሎ ማቅረብ፣ የሐሳብ ብዝኃነትን አለመቀበልና ከታሪክ አለመማር ላይ ነው የሚጥለው፡፡
ስለዚህ ለእውነተኛ ፈጠራ፣ ለበሰለ ጥብብና በማኅበረሰብ ግንባታ ላይ ለሚያተኩሩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ዕድል መስጠት፣ እንዲህ ዓይነት የጥበብ ሙያተኞችንም ማበረታታት አለበት፡፡ በአድርባይነትና በወለም ዘለም የጥበብ ሥራ አገርና ሕዝብ ይናድ እንደሆነ እንጂ አይገነባም፡፡ የመረጃና የሐሳብ ነፃነት ባልተከበረበትም የዴሞክራሲ መረጋገጥ የሚሉት ጨዋታ እንደሌለም ሊጤን ግድ ይለዋል፡፡ የሐሳብ ነፃነትም ነፃና ትልቅ ማኅበረሰብ ሊገነባ የሚችል ጥርጊያ ነው፡፡
እዚህ ላይ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሰር ዊስተን ቸርችል በአንድ ወቅት ባቀረቡት የምክር ቤት ንግግር የገለጹትን ሐሳብ መጥቀስ እወዳለሁ፡፡ ‹‹Everyone is infavor of free speech. Hardly a day passes without its being extolled but some peoples idea of it is that they are free to say whatever the like, but if anyone says anything back that is an outrage.››
ማጠቃለያ
በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሐሳቤን በአስተያየት ገጽ ላይ ለማስፈር የፈለግኩት በአገራችን የኪነ ጥበበና የሥነ ጥበብ ሥራዎች በቁጥር ቀንሰዋል ከሚል አይደለም፡፡ እጅግ የበዙ ሥራዎች ለ‹‹ገበያ›› እየቀረቡ ነው፡፡ ቢማሩም፣ ባይሠለጥኑም በሰው በሰውም ይሁን በፍላጎት የጥበብ ሥራውን የሚቀላቀሉ (በተለይ ፊልምና ሙዚቃ) ‹‹አርቲስቶች››ም አልፍ አዕላፍ ሆነዋል፡፡ እሰየው ያስብላል፡፡
ጥበብ ግን የመሪነት፣ የአስተማሪነት፣ የማኅበራዊና ሥርዓታዊ ሒስ አድራጊነት ሚናዋን ትጫወት ነው መነሻና መድረሻዬ፡፡ ከቀደምቶቹ ሙዚቀኞች፣ ተዋንያን፣ ደራሲዎች፣ ጋዜጠኞችና ሠዓሊዎች፣ ወዘተ የግንባር ቀደምቶቹን ስም የምንጠራው እኮ በተግባር ባሳዩዋቸው የጥበብ ሥራዎች ነው፡፡ በረሃብና በጦርነት በከፈሉት ኪነ ጥበባዊ ዋጋ የሕዝቡን ልብ በመግዛታቸው ነው፡፡ የሚሞገሰውን አሞግሰው፣ የሚተቸውን ነቅፈው አንገታቸውን ቀና አድርገው በመሄዳቸውም ነው፡፡ በአንዴ ዘመናዊ መኪናና በገነቡት ቤት ቢሆንማ አንዳቸውም ስማቸው አይነሳም፡፡ ጥበብ አገር የመምራት ሚናዋን ትወጣ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡