የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ (ኢቋባአ) ባለፉት ሦስት ዓመታት ከአሥር በሚበልጡ ብሔረሰቦች ቋንቋዎችና ባህሎች ላይ ትኩረት አድርጎ ያሳተማቸው 13 መጻሕፍት ተመረቁ፡፡ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ተጽፈው ለኅትመት የበቁት እነዚህ መጻሕፍት የተመረቁት አካዴሚው ዓመታዊ የምርምር ቀኑን ‹‹የቋንቋዎችና ባህሎች ጥናት ለሁለንተናዊ የአገር ዕድገት›› በሚል መሪ ቃል ጥር 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ባከበረበት ሥነ ሥርዓት ላይ ነው፡፡
በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ በሚገኘው እሽቱ ጮሌ አዳራሽ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ ከተመረቁት መጻሕፍት መካከል የስልጤ፣ የደራሼ፣ የአላባ፣ የሲዳማና የሳሆ ባህሎችንና ቋንቋዎችን የሚተርኩ ይገኙበታል፡፡
መጻሕፍቱን በጋራ የመረቁት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ የአገር መከላከያ ሚኒስትር ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ሦስት የዩኒቨርሲቲው ምሁራን በኅትመቶቹ ላይ ዳሰሳ ያደረጉ ሲሆን፣ ጥናቶቹ የተካሄደባቸው ዞኖችና ወረዳዎች ተወካዮችም የየራሳቸውን አስተያየት አንፀባርቀዋል፡፡
ዶ/ር አድማሱ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ሰዓት ትኩረታቸውን ሙሉ ለሙሉ በጥናትና ምርምር ላይ ብቻ ያደረጉ ከስምንት ያላነሱ ተቋማት እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ እነዚህም ተቋማት ከአገሪቱ የልማት ግቦች ጋር የተጣጣሙ አገራዊ ጉዳዮችን የምርመራቸው አጀንዳ በማድረግ ለፖሊሲ አውጪ፣ ለተርጓሚውና ለፈጻሚው የመንግሥት አካል ግብዓት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
ከጥናትና ምርምር ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ ተጠቃሽ ነው፡፡ አካዴሚው በአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለትምህርትና ማስተማሪያነት እንዲያገለግሉ የተመረጡ ቋንቋዎችን አቅም በማሳደግና በማብቃት ይንቀሳቀሳል፡፡ የአካዳሚው ተመራማሪዎችም የምርምርን ሳይንስ የተከተለ፤ የአገሪቱን የልማት ግብ ታሳቢ ያደረገ፤ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ጥናትና ምርምር እንዲያካሂዱ ዩኒቨርሲቲው ያበረታታል፡፡
የአገር መከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ፣ ቋንቋዎች በሁሉም የማኅበራዊ ግንኙነት መስኮች በትምህርት፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በንግድ፣ በኢንዱስትሪ፤ በብዙኃን መገናኛ፣ በአስተዳደርና በመሳሰሉት መስኮች የመግባቢያ ቋንቋዎች ለመሆን ከሚጠበቁበት ዕድገት ደረጃ እንዲደርሱ ጥረት ማድረግ ከአካዴሚው የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ባህሎችና ቋንቋዎች የአገሪቱ ዜጎች የታሪክ ትስስር፣ የማንነት መገለጫ፣ በልዩነት ላይ የአንድነት መሠረት፣ የመቻቻል፣ የሰላምና የዕድገት ማረጋገጫ በመሆናቸው ጥናት በማካሄድ እንዲጠበቁና እንዲበለጽጉ ጥረት ማድረግ መንግሥት ከሁሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር እንደሆነም አክለዋል፡፡
አስተያየት ከሰጡ የብሔረሰብ ተወካዮች መካከል የስልጤ ዞን አስተዳደሪ ሕዝቡ ባህሉ፣ ቋንቋውና ታሪኩ ሲዳብሩለት ስለ አገሩ የሚኖረው ስሜትና አገሩን ለማልማት የሚፈጥረው መነሳሳት ታላቅ ነው ብለዋል፡፡
አቶ መሰለ ማሞ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የደራሼ ወረዳ የባህል፣ ቱሪዝምና መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ ‹‹በራስ ቋንቋ አካባቢን መግለጽ የዕውቀት መሠረት ነው፡፡ ሕዝብም ይህንን የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ለብሔረሰብም ክብርና የማንነት መገለጫ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ለጃዝ ሙዚቃ መሠረት ነው ተብሎ የሚታመንበት፣ በሌላው የአፍሪካ አካባቢ የሌለና በኢትዮጵያ ደራሼ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ባለሰባት ኖታ፣ እንዲሁም ድርቅ የማይበግረው ‹‹ታርካ›› የተባለው ባህላዊ አገር በቀል የውኃ ማቆር ዘዴ ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት እንዲካሄድበትም ጠቁመዋል፡፡
አቶ ደስታ ስብሐት የኢሮብ ወረዳ ተወካይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢሮብ ብሔረሰብ ቋንቋን ለማሳደግና ለማልማት ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱ ትምህርት በቅድሚያ የተጀመረው በ1837 ዓ.ም. በአሊቴና መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ብዙ ጥናቶችና ምርምሮች ማካሄድ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር ወንድወሰን ተስፋዬ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ ዋና ጸሐፊ ‹‹ፈጣን የባህልና ቋንቋ ወረራ አደጋ ውስጥ እንገኛለን፡፡ እነዚህን አደጋዎች መከላከል የምንችለው ቋንቋዎቻችንና ባህሎቻችን በሳይንሳዊ መንገድ ተጠንተውና ተሰንደው ለሕዝብ አገልግሎት ላይ ሲውሉና አገራችን ለተያያዘችው ልማት አስተዋጽኦ ማድረግ ሲቻል ነው፤›› ብለዋል፡፡
አካዴሚው ካስመረቃቸው መጻሕፍት ሌላ የኮሞ፣ የአሌ፣ የሃላባ፣ የዶቢና ዲራይተታ ቋንቋዎች ፊደል ቀርጿል፡፡ በካፊኖኖ፣ በኤርቦሬ፣ በአሪና በሸኪኖኖ ድምፅ ልሳን እንዲሁም በስልጤ፣ በኦሮሞ፣ በኮንሶና ዳውሮ ባህል ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን አካሂደዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የሐላባ ታሪካዊ ጥናት እያከናወነ ሲሆን፣ የአማርኛ፣ የኦሮምኛና ትግሪኛ መዛግብተ ቃላት የክለሳና የማስፋፋት ሥራ ሠርቷል፡፡ የሐሮ፣ የባይሶ፣ የሐመር፣ የቀቤና የሳሆ፣ የሲዳማ፣ የዲሜና የኮረቴ መዛገበ ቃላት አዘጋጅቷል፡፡ የግእዝ መጻሕፍት (ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ፣ መዝሙረ ክርስቶስና መጽሐፈ ባሕርይ) ወደ አማርኛ ተተርጉሟል፡፡
ኢቋባአ ቀደም ባሉት ዓመታት የነበረው አደረጃጀት በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ሥር የኢትዮጵያ የቋንቋ መርሐ ልሳን (አካዴሚ)፣ ከ1964 እስከ 1967 ዓ.ም. ‹‹የአማርኛ መርሐ ልሳን (አካዴሚ)፣ ከ1967 እስከ ፈረሰበት1989 ዓ.ም. ደግሞ በባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ በሚል ተግባሩን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ከ1989 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ‹‹የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል›› በሚል ስያሜ ደረጃው ዝቅ ብሎ እስከ 2002 ዓ.ም. ከቆየ በኋላ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማካተት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚነት ሥራውን መቀጠሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡