ያልተፈለገ እርግዝናን በተወሰነ መጠን መቀነስ ቢቻልም አመርቂ ለውጥ ማስመዝገብ የሚቻለው ወንዶችም የበኩላቸውን ሲወጡ መሆኑን በቤተሰብ ምጣኔና በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ የሚሠራውና መቀመጫውን በሰሜን ካሮላይና ያደረገው ላለፉት 15 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ ሲሠራ የቆየው አይፓስ ጥር 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ፡፡
‹‹ያልተፈለገ እርግዝናን የመከላከል ኃላፊነት የሴቶች ብቻ አይደለም፡፡ ጥቂት የማይባሉ ያልተፈለጉ እርግዝናዎች በአስገድዶ መደፈር የሚፈጠሩ ናቸው፤›› በማለት መሰል አጋጣሚዎችም በባለትዳሮች መካከል ሲፈጠሩና የችግሩ መንስኤ ሲሆኑ እንደሚታይ በኢትዮጵያ የአይፓስ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳባ ኪዳነማርያም ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብና በአዲስ አበባ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ አጠቃላይ የሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ ያልተፈለገ እርግዝናን አስቀድሞ በመከላከል፣ የተለያዩ የወረደ መከላከያ መድኃኒቶችን በማቅረብ፣ ስለ ሥነ ተዋልዶ ጤና የሚያስተምሩ መድረኮችን በመፍጠርና ያልተፈለገ እርግዝና ሲከሰት ጽንሱን ለማውረድ ሲሉ ሕገወጥ ጽንስ አስወራጆች ጋር እንዳይሄዱ እገዛ ማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በአሜሪካ አገር ካሮላይና ግዛት በ1965 ዓ.ም. እንደተቋቋመ የሚነገርለት አይፓስ የሴቶችን ፆታዊና የተዋልዶ መብት ለማስከበር እንዲሁም ጽንስ ከማስወረድ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ አደጋዎችን መቀነስ ቀዳሚ ዓላማው ነው፡፡ በአሁን ሰዓት በተለያዩ የዓለም አገሮች ቅርንጫፉን ከፍቶ በመሥራት ላይ ሲሆን ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ቢሮውን ከፍቶ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ የሚስተዋሉትን ችግሮች በተለያዩ መንገዶች ለመቅረፍ የሚሠራው ድርጅቱ ለባለድርሻ አካላት ሥልጠናዎች ከመስጠት ጀምሮ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ አገር በቀል ተቋሞችን በገንዘብ ይረዳል፡፡ በአሥር ዓመታት ጊዜ ውስጥም ድጋፍ አድርጓል፡፡ በዚህም ከ3 ሚሊዮን የሚበልጡ እናቶችን ለመድረስ ችለዋል፡፡